>

ይሄ የካፒታሊዝም ፒራሚድ ነው – በየትኛው ገበታ እርከን ላይ ነህ/ሽ? (አሰፋ ሃይሉ)

ይሄ የካፒታሊዝም ፒራሚድ ነው – በየትኛው ገበታ እርከን ላይ ነህ/ሽ?
አሰፋ ሃይሉ
  * «በአድራሻችን ይምጡና ይጎብኙን – በደስታ እንደሚመለሱ እናረጋግጥልዎታለን! ዓላማችን – ደንበኞቻችንን ማስደሰት ነው!»
                      – ቀኝ ዘመሞች!!!
እንደመታደል ሆኖ – ወይ እንዳለመታደል ሆኖ – በዓለማችን ላይ በ20ኛው ክፍለ ዘመን – ለአንድ መቶ ዓመታት ገደማ ለሚሆን ጊዜ – በሁለት ጎራዎች መካከል በተደረገው ጦርነት – አሸናፊ ሆነው የወጡት – ለብዙዎቻችን የሚያማልለንን ‹‹የሰው ልጅ እኩልነት!›› ያቀነቀኑት ኃይሎች ሳይሆኑ – ‹‹እቅጩን እንንገራችሁ፣ ሰው እኩል ሊሆን አይችልም፣ አንዱ የበላይ አንዱ ከየታች ሆኖ ነው የሰው ልጅ መኖር ደስ የሚለው!›› – የሚሉት ኃይሎች ናቸው – በክፍለዘመኑ መጨረሻ ላይ – ድል አድራጊ ሆነው – በአሸናፊነት የወጡት፡፡
እነዚያ ‹‹የዜጎችን ሁሉ እኩልነት ያረጋገጠ የኢኮኖሚ ሥርዓት እናሠፍናለን!›› – ብለው የተነሡት የኮሙኒዝም እኩልነት የሠፈነበት ሥርዓት (ሃሳቡ ራሱ!) የማረካቸው – የሦሻሊዝም አራማጅ ግራ ዘመሞች – ከናቀነቀኑት የሦሻሊዝም-ኮሚኒዝም ርዕዮተዓለማዊ ሐይማኖታቸው ጋር – አፈር በላቸው፡፡
እና – በእነሱ መቃብር ላይ ያበበው – ድል አድራጊው የዘመናችን መንግሥት – የካፒታሊዝም ንዋይ-ተኮር ርዕዮተ-ዓለም አራማጅ የሆኑት – የቀኝ ዘመሞች እምነተ መንግሥት ነው፡፡ ዓለም ዘጠኝ ናት፡፡ ዘመኗም የእነ አይንራንድ ‹‹የራስ ወዳድነት ጥበብ›› የነገሠባት ናት፡፡ እና በቃ ይቺው ናት ዓለምህ፡፡ ዕወቃት፡፡ መርምራት፡፡ እና ሣትወድ በግድ ተቀበላት፡፡ እንግዲህ ምን ትሆን?
በእርግጥ ብዙዎች ለሰው ልጅ እኩልነትን የተመኙ ግራ ዘመሞች – ያን ምናባዊ እኩልነት በህይወት መስኮች ሁሉ ለማምጣት – ብዙ ዳክረዋል፡፡ ግን አልሆነም፡፡ አልሆነላቸውም፡፡ ግራዎች የምር ግራ ገባቸው፡፡ የሰው ልጅ እኩልነትን አይፈልግም ማለት ነው? እንዴ!? አዎ አይፈልግም፡፡ አዎ አንፈልግም፡፡ እንግዲህ ምን ይደረግ?!! በቃ ከሰው መብለጥ ደስ ይለናላ እኛ ሰዎች!!!
እና በቃ ያ – የሁሉም ሰው እኩልነት – የሁሉም ሰው ፍላጎት እንዳልሆነ ሲገነዘቡ – ግራዘመሞች – ያን መራር እውነታ – አምነው መቀበል ግድ ሆነባቸው፡፡ እናም እነሆ – ብዙዎች ግራዘመሞችን ያፈሩ ሀገሮች ሁሉ – ባነገቡት የሰው ልጅ እኩልነት መፈክር አፍረው – አንገታቸውን ደፍተው – ወደቀኝ ዘመሞች ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና የወድድር ዓለም – ፊታቸውን ቀለሱ፡፡ ቀለስን፡፡
ስንቀልስ – በግልጽ ያየነው – በተግባርም የገጠመን – የቀኝ ዘመሞች የማይናወፅ አቋም ደግሞ – ይህ ነበረ፡-
‹‹እናንት የኮሚኒዝም እኩልነት አላሚዎች፣ እናንት የጭቁኖች ጥሩር ለባሾች፣ እናንት የእኩልነት ጋሻጃግሬዎች፣ እስቲ አንድን እንጠይቃችሁ፣ እናንተም መልሡልን፡፡ በኀጥዖች በተሞላች ጊዜያዊ ምድር ላይ እየኖራችሁ፣ ስለምን የሠማይን ዓይነት ዘለዓለማዊ የፅድቅ አኗኗር ትመኛላችሁ? የሰው ልጅ ሁሉ በኪሱ እኩል ሆኖ አንድ ዓይነት ማዕድ ላይ ሊታደም የሚችልበት የእኩልነት ሥርዓት ሊገነባ የሚችለው፣ እዚህ የሰው ልጆች ምድር ላይ አይደለም፡፡
‹‹ይሄ እናንተ የምትሉት የእኩልነት መንግሥት እውን ሊሆን የሚችለው አይደለም፡፡ ዕውን ሊሆን ከቻለ ግን – በቃ ያ የእኩሌታ መንግሥት ያለው – ምናልባት – በመንግሥተ ሠማያት የገነት የአትክልት ሥፍራ ውስጥ ብቻ ይሆናል፡፡ የናንተ ሃሳብ የተቀደሰ መሆኑን አላጣነውም – ግን በቃ እሱን እርሱትና፣ ወደምድራዊው ተመለሱ፡፡ የየግል ኪሳችሁን ለመሙላት ተጣጣሩ፡፡ እኛ ደግሞ ወደሃብት ለምታደርጉት ጎዞ ሠፋፊ መንገዶችን አዘጋጅተን እንጠብቃችኋለን! በመንገዳችሁ – ኪሣችሁን – ከቀማኞች ጠብቁ!››
የሚል ነበር አቋማቸው፡፡ እንግዲህ ይህ ነው – ቀኝ ዘመሞችን – በግራ ዘመሞች ላይ – እና በሰው ልጆች ዘንድ – አሸናፊ ያደረጋቸው – ምድራዊ አቋም፡፡
እና አሁን ዘመኑ የቀኝ ዘመሞች ዘመን ነው፡፡ ግን ቀኝ ዘመሞችን ያን ያህል እርኩስ አርገህ አትቁጠር፡፡ አሁን አሁን ቀኝ ዘመሞችም – ‹‹ሁሉም ሰው እኩል ነው›› የሚለውን መርህ – መቀበል ጀምረዋል፡፡ ግን አንድ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው ነው፡፡ ‹‹ሁሉም እኩል ነው›› – ግን ቅድመ-ሁኔታው ምን የሚል ነው? ‹‹አንዳንዶች የበለጠ እኩል እስከሆኑ ድረስ! – ሁሉም እኩል ነው!›› የሚል፡፡ በዚህ ወደ እውነታው በቀረበ መንገድ – እኩልነትን እንቀበለዋለን – ባዮች ናቸው ቀኝ ዘመሞች!!
እኩልማ እኩል ብንሆን ችግር አልነበረውም፡፡ ግን በጫማ ቁጥራችን እንለያያለን፡፡ በቁመት፣ በአግድመት፣ በወገብ ቁጥር፣ በፀጉር ብዛት፣ በዓይን ቅላትና ንጣት፣ እና ደግሞ በካሽ እና በክላሽ እንለያያለንና – አንድ እንድንሆን ብንሻም – እውነቱ ግን – አንዳንዶቻችን – ከሌሎቻችን – ትንሽ ከፍ፣ ትንሽ ጎላ፣ ትንሽ ላቅ፣ ትንሽ ፈርጠም፣ ትንሽ ዳጎስ እንላለን!! ይህ ጆርጅ ኦርዌል – ከ70ና 80 ዓመት በፊት – በኮሚኒስታዊ አኗኗር ተጀምሮ – በአናርኪስታዊ ፍፃሜ በተጠናቀቀው – ‹‹የእንሥሣት ዕድር›› መጽሐፉ:–
“All anmals are equal, but some animals are more equal than others!”
– ሲል እንደተነበየው ነው:: አዎ፡፡ እውነቱ ያ ነው፡፡ የዘመናችን የቀኝ ዘመሞች መንግሥትም ያን እውነት ትቀበላለችና – ዛሬ – በምድሪቱ መንግሥታት ነዋሪዎች ዘንድ – አንዳንዶች – የግድ – ከሌሎች ይልቃሉ፡፡ ምክንያቱም – መንገዱ – የውድድር – እንዲሁም የፍትጊያ – እና የጥሎ ማለፍ – ስለሆነ!
ግራ ዘመሞች – ያኔ በየዋህነት – ወይ በጅልነታቸው – ሁሉንም ሰው እኩል ለማድረግ ተጉ፡፡ ግን አልሆነላቸውም፡፡ ምክንያቱም ሰውን እኩል ላርግህ ስትለው – ልዩ ነኝ እኔ የሚል ፍጡር ነው፡፡ ቢሆንማ ኖሮ እንደግራዘመሞች እኮ ሁሉን እኩል ለማድረግ ሰማዩን የቧጠጠ የምድራችን ቡድን እኮ አልነበረም፡፡
 ግን በመጨረሻ ግራ ዘመሞች እኩል ማድረግ የተሣካላቸው ብቸኛ ነገር ምንድነበር? ግራ ዘመሞች ሁሉንም እኩል ማድረግ የቻሉት ነገር ቢኖር – ‹‹ሁሉንም ሰዎች እኩል ደሃ አድርገው ማስቅረት›› – ብቻ ነበረ – ይሏቸዋል፡፡ ለዚህ ነው – ብዙ የምስራቅ አውሮጳ ነዋሪዎች – ዛሬ በምሬት እንዲህ የሚሉት፡- ‹‹አዎ! ግራ ዘመሞች – ሁላችንን እኩል አደረጉን – ለሁላችን ድህነትን በእኩል መጠን በማደል – ሁላችንንም ድሃ – ሁላችንንም እኩል – አደረጉን!››፡፡
እና ቀኝ ዘመሞች ምናቸው ሞኝ?! – የግራዎቹን መቃብር ሲያፋጥኑት እንዲህ እያሉ ነበራ፡-
‹‹እኛ እንደግራዎች ‹ሁሉንም ሰው እኩል እናደርጋለን!› ብለን የማይቻለውን ነገር ቃል አንገባም፣ አንወሻክትም! – እኛ የምናደርገው ነገር ቢኖር – ‹አብዛኛውን ሰው ደስ ማሰኘት!› ነው! የኛ የመጨረሻው ግባችን – ሁሉንም ሰው እኩል ማድረግ ሣይሆን – ሁሉንም ሰው በያለበት ጎጆው ደስ ማሰኘት ነው!››፡፡
እንዲያ ነበር የሚሉህ ቀኞች፡፡ እንዴ?! ግራኞች እኩልነትን ሲያድሉ – እኛስ ምን እናድል? ‹‹ደስታን!›› ብለው ነው የተነሱት፡፡ አዎ! የ‹‹እኩልነት›› አማላይ ሃሳብ መፎካከሪያው ‹‹ደስታ!›› ነው፡፡ አዎ፡፡ በግራኞች መንግሥት ሁሉም እኩል ነው፡፡ በቀኞች መንግሥት ደግሞ ሁሉም ደስተኛ!!! እና – በ‹‹ደስታ!›› – ግራኞችን ማሸነፍ እንችላለን ብለው ተነሱ – ቀኞች፡፡ እናም በትክክልም አሸነፉበት፡፡ በዚህ – ‹‹ደስታን ለሁሉ የማዳረስ!›› መፈክራቸው – የቀኞች ንዋይ እባብ – የግራኞችን የእኩልነት እባብ ዋጠቻት!፡፡
ግን ግን – ቀኞችም ቢሆኑ – የግራኞች ‹‹እኩልነት›› የሚል ቃል ከሰው ልብ ውስጥ በቀላሉ እንደማይጠፋ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ምን አመጡ? ከሶሻሊስቶቹ ግራ ዘመሞች መንደር – አንዳንድ ወሳኝ ነገሮችን መንትፈው አመጡ – ወደቀኞች ሰፈር፡፡ ለምሳሌ – የዋሆቹ ግራ ዘመሞች ድሮ – ሁሉም እኩል ሥራ የሚሠራ ሰው እኩል ተመሣሣይ ክፍያ ይገባዋል – ሲሉ ይጮኹ ነበር – ‹‹እኩል ሥራ፣ እኩል ክፍያ›› የሚሉትን ነገሮች – ከእኩልነት መርሃቸው ጋር ደምረው፡፡ እና ቀኞች ይህን ሰምተው የለ? ምንም ችግር አላገኙበትም፡፡ ስለዚህ – ቀኝ ዘመሞቹም ያንኑ ማለት ጀመሩ፡-
‹‹ሁሉም እንደየሥራው እኩል ይከፈለው፣ ሁሉም እንደየሥራው እኩል ብድር ይፈቀድለት፣ ሁሉም እንደየሥራው የሚሠራበት አካባቢ ምቹ ይደረግለት፣ ሁሉም እንደየሥራው መጠን ኪሡን ይሙላ፣ ሁሉም እንደየሥራው መጠን ይንፈላሰስ፣ ሁሉም እንደየሥራው መጠን የቻለውን ደስታ ይቀዳጅ፣ የቻለውን የግሉን ኑሮ ያሣድድ…! የቻለውን ….ያስተፌሰው ልበ ሰብ!!!! – ብለው እርፍ!!!!
ቀኝ ዘመሞቹ ካፒታሊስቶች ይህን ሁሉ ያደረጉት – አንድም ለሰዎች ቃል የገቡትን ‹‹ደስታ››ን እኩል ለማጋራት በቃላቸው መሠረት ለማዳረስ ነው፡፡ ሁለትም ግን– ይህ የሰዎች በያሉበት ሥፍራ ወደጎንዮሽ እርስ በራሳቸው አንድ ዓይነት ሥፍራ ላይ በተገኙ ሰዎች መካከል እኩልነት የማረጋገጥ ነገር – የጎንዮሽ እኩልነት ቢረጋገጥ – በሰዎች እኩልነት ላይ ላልተመሠረተው የካፒታሊስት ሥርዓት – የሚፈጥረው ዘለቄታዊ አደጋ እንደማኖር – በሚገባ ስለተረዱት ነው፡፡  ምክንያቱም የሰው መደቡ ይለያያላ!!! እኩል እኮ የምትሆነው ከእኩያህ ጋር – በተመሣሣይህ መደብ ካለው ጋር ነው!!! እንጂ – ወደላይኛው ከማይመስልህ ጋር ተንጠላጥለህ አይደለም!! እና ቀኞች ምን ተዳቸው?! ምንም!!!
ለምሣሌ – የታችኛው የባለሰማያዊ ቱታዎች መደብ ላይ ከተደመርክ – ከእኩዮችህ ያንተቢጤዎች እኩል ሥራ ትሠራለህ፣ እኩል ይከፈልሃል፣ እኩል ትበላለህ፣ እኩል ትቆጥባለህ፣ በዚያችው እኩልህ ልክ ብርችንችን ትላለህ – እና አንተ ወደላይኛው የነጭሸሚዞች መንደር አጥር እዘላለሁ ብለህ ሀገር ይያዝልኝ እስካላልክ ድረስ – እነሱ ባንተ የታችኛው ዓለም – ምን ጥልቅ አረጋቸው?? – ምንም!!!
እንዲያውም አንዳንዴ እንዳትከፋ ብለው – እኩል መሆንህን እያሰብክ እንድትደሰት ለአንተ ለዜጋቸው በ ማሰብ ጭምር – በመሪዎች ምርጫ ውድድር ሰሞን – የምርጫ ካርድ ይሰጡሃል! – ያንተም ድምፅ፣ የዲታውም ድምፅ፣ የጦር አበጋዙም ድምፅ፣ የያንዳንዱ ድምፅ – የሁሉም ድምፅ – እኩል ነው – እያሉህ ማለት ነው፡፡
የምርጫ ሰሞን ደሞ – ሌላኛቸውን ትተህ አንደኛቸውን እንድትመርጥ – ሁሉም በየፊናቸው – ጠቀም ያለ ጉርሻ፣ ጠቀም ያለ መደለያ፣ ጠቀም ያለ ቃል፣ ጠቀም ያለ ፖሊሲ ይዘውልህ ይመጣሉ – ሁሌም አንተ ደስተኛ መሆንህንም እያረጋገጡ ይጓዛሉ – ምክንያቱም – አንተ ያለህባትን መደብህን ሣትለቅ የምትደሰታት ደስታ – የእነርሱም የጋራ ደስታቸው ነችና!!! እና ከዚህ በላይ ደስታ ምን አለ? ከዚህ በላይስ ‹‹የደስታ እኩልነት›› ከወደየት ልታገኝ?
ይሄ ማለት – የአይሪሹ ኦስካር ዋይልድ – በ19ኛው ክ/ዘመን ማብቂያ ላይ – እውነቱ ፍንትው ብሎ ታይቶት እንዳለው ማለት ነው፡– ሞጃዎቹ ገዢዎች – በስመጥር ደራሲዎች የተቀናበረ ኦፔራቸውን – በስመጥር የቴአትር መድረኮች ታድመው ሲቋደሱ – እኛም ደግሞ – ስመጥሩ ሁሉን ቻይ አምላክ እንድናቀናብረው በፈቀደልን – በየገዛ ቤታችን መኝታ መድረኮች ላይ – መቅረዞቻችንን ሁሉ አጥፍተን – ከትዳር አጋሮቻችን ጋር – የየራሳችንን ስምአልባ ኦፔራ እንተውናለን፣ እንታደማለን – ያው ግን – እኛም እነሱም – ያቺን የፈለግናትን ደስታን እንደሰታታለን!! ደስታ! ደስታ ! ከደስታ ጋር ወደፊት!!
በመጨረሻም – ቀኝ ዘመሞች – አንተ አንዳንዴ – አሁንም አሁንም በየሰበብ አስባቡ በሃሳብህ ብልጭ ባለብህ ቁጥር – ‹‹እኩልነት! እኩልነት!›› እያልክ እንዳትረብሻቸው – እንዳትደርቅባቸው አንደኛ – ሀለተኛ ደግሞ – ‹‹እኩልነት›› የሚባለው ነገር ትክክለኛ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ሂደት ያለመሆኑን ደግሞ እንድታውቅ – ሁልጊዜም ያወዳድሩሃል!!! ያወዳድሩሃል ከሌሎች ጋር – ወይም የሌሎችን ውድድር በደስታ እንድትመለከት ያደርጉሃል፡፡
እና በውድድር ዓለም እየኖርክ – አንደኛ መውጣት እንድትፈልግ ያደርጉሃል፣ አንደኛ የተባለውን እንድታደንቅ ያበረታቱሃል፣ ቀድሞ መገኘትን እንድታወድስ ይቃኙሃል – እና በውድድር – እና በጥሎ ማለፍ – እና በሻምፒዮና – እና በውራ – እና በአሸናፊ – እና በተሸናፊ – እና ባለፈለት – እና ባላለፈለት – እና በመሳሰሉት የሰው ልጅ እኩል እንዳልሆነ ልትገነዘብባቸው በምትችልባቸው ውድድራዊ የማበላለጫ መንገዶች ሁሉ – የእነርሱን የቀኝ ዘመሞቹን እውነት ውስጥህ ድረስ አዝልቀህ – ከሁለመናህ ጋር እንድታዋህደው ያደርጉሃል!!
ውድድርን – አሸናፊነትን – ቀዳሚነትን – አትራፊነትን – በላጭነትን – አንደኛነትን – ትወድ ዘንድ – ጥቂት በጥቂት አዋዜ በሀሞት ጠብ እያደረጉ – የቀኝ ዘመሞችን ትኩስ ቃተኛ ያበሉሃል፡፡ ይህን ሁሉ ሲያደርጉ እና ሲያስደርጉህ ግን ሁልጊዜም አንተ – ደስታህን እና ደስታህን ብቻ አስበህ እንድታደርገው አመቻችተው – የዚህችን ዓለም የህይወት እንቅስቃሴ ሁሉ ዳይሬክት አድርገው ስለሆነ – ሳታውቀው እየተደሰትክ ነው እኩልነትን ከውስጥህ እያራገፍክ – በሙሉ ቀልብ – በሙሉ ልብ – በሙሉ ፍቃደኝነት የምትከተላቸው!! ወይም ኑሮህን ተከትለህ ወደቀጣዩ የህይወት ድራማ የምታዘግመው!
እና እኩልነት – በአሁኗ የቀኝ ዘመሞች ዓለም – በአሁኗ የቀኝ ዘመሞች ምድራዊ መንግሥት – የጎንዮሽ ናት፡፡ በዚህ የኛ ዘመን – እኩልነት – ወደላይ አይደለችም፡፡ ወደታች አይደለችም፡፡ ወደጎን ግን ነች፡፡ ግን ግን – ያቺም የጎንዮሽ እኩሌታ – የሆነ ደግሞ ከዚያ የበለጠም ተስፋ ያስፈልጋታል – ብለው ያስባሉ፡፡ ተስፋ ርቆ የተሰቀለ ዳቦ ነው – አይደል? ስለዚህ የቀኝ ዘመሞች በመደብህ ጎን ያለች እኩልነትም – በሩቅ የተሰቀለ – ከዚህም ካለህበት መደብህ በላይ የሆነም – ልታገኝ የምትችለው – ልትናፍቅ የምትችላት – ትልቅ የተስፋ ዳቦም – ከአንተ በላይ በሆነው እርከን ላይ ተንጠልጥላ እንድትታይህ ያደርጉሃል!!!
ምናልባትም – በእርግጥም – ባለህበት እርከን ተወስነህ ላትቀር ትችላለህ እኮ!!!! ምናልባትም – ከአንደኛው የኑሮ እርከን – ወደሌላኛው ከፍ ወዳለ የኑሮ እርከን – የመሻገር እድልም ታገኝ ይሆናል፡፡ አሁንን እየተፍጨረጨርክ ታልፋታለህ፡፡ ወደፊት ግን የሚሆነውን አታውቀውም፡፡ እና ትጓጓለህ – እንዴ!? ምንም አጓጊ ነገር ከሌለበት – እና ሁሉም ያገኘውን እኩል ተካፍሎ በቀቢፀ-ተስፋ – በመንጋ ከሚያዘግምበት – ደስታ የሌለው የጋራ እኩልነት – ይሄ አይሻልህም? ቀድሞ ነገር የማያጓጓ ባዶ እኩልነት ምንስ ሊሠራልህ? – ይሉሃል ቀኝ ዘመሞቹ!!
ደሞ ብቅ ይላሉ ባለህበት ሥፍራ – አንዳች የምሥራችን ተላብሰው – እና – ‹‹ሎተሪ ቁረጥ እንጂ!›› ሊሉህ፡፡ ሞክር ይሄን ሎተሪ – ሞክሪ ያንን ሎተሪ – ሞክር ባለ እንዲህ ሚሊዮኑን – ሞክር ባለመቶ ሺህውን – ሞክር ባለዕድሉን – ሞክር ባለገዱን – ሞክር – አልም – ዕጣ አውጣ – ባንዴ – ከዚህኛው እርከንህ ወደዚያኛው እርከንህ ሊያሻግርህ ይችላልና! – ነው የሚሉህ፡፡ እና – እውነትም ነው – እና – ሎተሪ ትቆርጣለህ፡፡ እና ሎተሪ ስትቆርጥ ትኖራለህ፡፡ እና በንዋይ ጉጉት ተሞልተህ፣ አቋራጭ መንገዶችን ሁሉ እያሰስክ ሕይወትህን ትመራታለህ፡፡ ካልሆነልህም ግን በማስተዛዘኛ ዕጣ – ‹‹የፍቅሬ ሎተሪ አንቺ መሆንሽን!›› ብለህ ወደገደላት እጥፍ!!!
እና – የዓለምን ህዝብማ ባያሸንፉት፣ የዓለምን ሕዝብ ድል ባያደርጉት፣ ግራዘመሙን ሁላ ድባቅ ባይመቱት እኮ ነበር የሚገርመን – ነው እኮ – የብዙዎች ድምዳሜ!!! ቀኝ ዘመሞችን – ከነተንኮላቸው የፈጠረ – ከነሲስተማቸው በድል ያመላለሰ – እንዲያው ነፍሱን አይማረው – ብለህ አትራገም ነገር – የደስታህን ምንጮች – የዘመንህን ፍፃሜ መንግሥቶች – ምን አድርጉ ልትል ነው??!!
እና እንግዲህ ይህች ነች ያሁኗ – ‹‹ሁሉም እኩል ነው›› ያሉት ግራ ዘመሞች የተሸነፉባትና ከምድሪቱ የተሰናበቱባት – ‹‹አንዳንዶች ከሌሎች በላይ እኩል እንደሆኑ›› አበክረው ያመኑትና የሰበኩት ቀኝ ዘመሞች ደግሞ በድል አድራጊነት የመቶ ዓመቱን ጦርነት አሸንፈው ሥርዓታቸውን የዘረጉባት – ይቺው ናት እንግዲህ – ይቺው ናት የዛሬዋ ካፒታሊስቷ ዓለምህ!!!
۞ እነሆ – በካፒታሊዝም አራማጆቹ በእነ አዳም ስሚዝ ስም እናምናለን!!!!
۞ እነ አሜሪካና አውሮፓ – እነ አውስትራሊያና ኤዢያ – ያለሙ ኃያላን ሁሉ አበክረው በሚያምኑባት – የሰው ልጆች የኢኮኖሚ የበላይነትና የበታችነት በተረጋገጠባት በአንዲቱ የቀኝ ዘመሞች መንግሥት – አበክረን እናምናለን!!!!
۞ ጥቂቶች ከፍ ያሉባትን፣ አብዛኞች ደግሞ ዝቅ ያሉባትን፣ ነገር ግን ሁሉም በያረፉባት በየተሠለፈባት የገበታ ጎራ – እኩል የሚሻማባትን – ይህችን ምድራዊ የሰው ልጆች ሥርዓት – በዘመናዊ ካፒታሊዝም ስም – እናሠፍናታለን!!
۞ ቀኝ ዘመሞች ለዘለዓለም ይኑሩ!!!
۞ በግራ ዘመም የሶሻሊቶች  ሥርዓት መቃብር ላይ – የንፁህ ካፒታሊስቶችን ሥርዓት እንገነባለን!!!
۞ በግራዘመሞች መቃብር ላይ – የቀኝ ዘመሞች መንግሥት ያብባል!!!!
۞ መች ሰማንና! መች ሰማንና! ያብባል ገና!!!! Loooooool!!!!!
የሆነስ ሆነና – ለመሆኑ – አንተ፣ አንቺ – እናንተ፣ እኛ – እነርሱ – በዚህ የካፒታሊስት ሥርዓት የኑሮ-ኬክ እርከኖች መካከል – በየትኛው የገበታ እርከን ላይ ትገኛለህ? ከየትኛው ጋር ነው የተደመርሺው? የትኛው የካፒታሊስት ፒራሚድ ላይ ነው – የትኞቻችን ያለነው???
አንድዬ በያለንበት እኩልነትን ይስጠን፡፡ ባለን ያርካን፡፡ ባለን ያስደስተን፡፡ ሎተሪ አያሳጣን፡፡ ከፍ ያርገን፡፡ ወደ ላይኛው እርከን!!! አበቃሁ!!!
ማስታወሻ፡– 
ለማንኛውም አድራሻችንን ማወቅ ለምትሹ ጥልቅ አንባቢዎቻችን :–
۞ አድራሻችን – ከታችኛው የሕብረተሰብ ክፍል – ወደ ውስጥ 50 ሜትር ገባ ብሎ መሆኑን – አበክረን – በፍቅር መግለጽ እንወዳለን!!! በአድራሻችን ይምጡና ይጎብኙን – በደስታ እንደሚመለሱ እናረጋግጥልዎታለን!!!! ዓላማችን – ደንበኞቻችንን ማስደሰት ነው!!!
                     – ቀኝ ዘመሞች!!!
ቻው አቦ!!!
Filed in: Amharic