>
6:15 pm - Wednesday November 30, 2022

ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት ለሁሉም ዜጎች እኩልነት የሚመኝ አድልኦን የሚጠየፍ ነው!!! (ግርማ ሰይፉ)

ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት ለሁሉም ዜጎች እኩልነት የሚመኝ አድልኦን የሚጠየፍ ነው!!!
ግርማ ሰይፉ
ብሔረተኝነት – ግራዋ የሆነ መራራ ብሔርተኝነት
ኢትዮጵያዊ ብሔረተኛ ነኝ፡፡ ይህ መብቴ እንዲከበር እፈልጋለሁ፣ ሰለዚህ ሌሎችም በፈለጉት ደረጃ ብሔረተኛ ቢሆኑ መብታቸው መሆኑን በማመን አከብራለሁ፡፡ አንድ አንድ ብሔረተኞች (በተለይ በኢህአዴግ ጥላ ሥር ያሉት) ለአማራ ብሔረተኝነት አንድ ሌላ ቅፅል ይሰጡት ነበር፡፡ ዴሞክራቲክ የአማራ ብሔረተኛ የሚል፡፡ ብአዴንም የአሁኑን አላውቅም “ዴሞክራቲክ የአማራ ብሔረተኝነት” የሚል ፈሊጥ ነበረው፡፡ በውስጠ ዘ “የአማራ ትምክተኝነት” የኢህአዴግ ብሔረተኝነት ዋልታና ማገር መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ ብዙዎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆኖ አጋሮቹ በአማራ ጭቆና ምክንያት ብሔረተኛ እንደሆኑ ሰለሚተረክላቸው እና በዚሁ አውድ ሰለተቀረፁ ከትምክተኛ አማራ ብሔርተኝነት የፀዳ ዴሞክራቲክ የአማራ ብሔርተኝነት አሰፈልጓቸው ነው፡፡ በዚህ ሰንገረም መክረማችን ብቻ አልበቃንም፣ ሌላ ደግሞ ፅንፈኛ ብሔረተኛ ተነስቶልናል፡፡ መራራ የሆነው “ግራዋ የአማራ ብሔረተኝነት” በአብን ሹም ክርስቲያን ታደለ ተደርሶ ቀርቦልናል፡፡
መቼም ዴሞክራቲክ የሚባል ብሔረተኝነት የለም፡፡ ብሔርተኝነት ወገንተኝነት በመሆኑ፡፡ ይህ ቅጥ አንባሩ የጠፋ ነገር መስመር መያዝ አለበት ስንል፣ የባሰ አታምጣ ሆነና ግራዋ ብሔርተኝነት ሊግቱን የተነሱ ሀይሎች መኖራቸውን በይፋ አብስረውናል፡፡ ግራዋን በውድ ስትጠጣው መድሐኒት የመሆኑን ያህል ስትጋት ግን የሚግተው ላይ መትፋት እንደሚኖር ተዘንግቷቸዋል፡፡ ቀጥሎም ያዘጋጁትን ግራዋ መልሶ ሊግታቸው የሚችል ሀይል እንደሚፈጠር አልገመቱም፡፡
ኢትዮጵያ ብሔረተኝነት ጣፋጭ ነው፡፡ ለሁሉም ዜጎች እኩልነት የሚመኝ ነው- አድልኦን የሚጠየፍ ነው፡፡ ነገር ግን ለኢትዮጵያዊያን ወገንተኛ ነው፡፡ ለሱዳን፣ ለኬኒያ፣ ለጂቡቲ፣ ወዘተ … እኩል እድል አይሰጥም፡፡ በእነርሱ ቦታ ሆነን ስንመለከተው ዴሞክራቲክ ላይሆን ይችላል፡፡ ለእነርሱም ቢሆን ግን መራራ- ግራዋ እንዳይሆን መጣር ዓለማቀፋዊ መርዕ መከተል ይኖርበታል፡፡ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ የግራዋ ብሔርተኝነት ይህን ዓይነት የፖሊሲ ማዕቀፍ ሳይሆን የሰሜት ጋሪ የሚጎትተው ነው፡፡
ግራዋው የአማራ ብሔረተኝነት- ሚሪንዳ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት እንዲገጥመው የሚፈልግ ከሆነ አይቻለም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ ሚሪንዳ የሆነ የሶማሌ፣ የኦሮሞ፣ የትግራይ፣ የሲዳማ፣ ወዘተ ብሔረተኝነት አይጠብቀውም፡፡ እሬት ሁሉ ሊሆን ይችላል፡፡ ቀኝህን ሲመታህ፣ ግራህን ሰጠው በሚባል ፈሊጥ የሚኬድ ብሔረተኝነት አይደለም፡፡ ግራዋ ለሚግት ምንም አቅም ከሌለህ እላዩ ላይ መትፋት፣ ከቻልክ አንተም ግራዋ ደግመህ ደግመህ መጋት የግድ ይላል፡፡ ይህ ነው የጫወታው ሕግ ሊሆን የሚችለው፡፡ ሰለዚህ የግራዋ አማራ ብሔርተኝነት ፈላስፎች ልብ ማለት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡
የግራዋ መራራ አማራ ብሔረተኝነት አቀንቃኞች ከህወሓት የተማሩት ነገር ቢኖር ቁጭት ፈጠራን ነው፡፡ ነገር ግን ህወሓት ቆሜለታለው ለሚለው የትግራይ ሕዝብ የፈየደው ነገር አለመኖሩን ቢያንስ በውጤyት ሊመዝኑት አልቻሉም፡፡ ከጥቂት የቀን ጅቦች በስተቀር የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ አሁን በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ተበትነው የሚገኙት የትግራይ ልጆቸ፣ ህወሓት ከማንኛውም ዓይነት እልቂትና መከራ ልትታደገቸው አትችለም፡፡ ዛሬ ህወሓት በስልጣን ላይ አይደለችም፡፡ ፅንፈኛ የትግራይ ብሔረተኞች ለአደጋ የተጋለጡት ከሚኖሩበት ሕዝብ አብልጠው በሺ ኪሎሚትር ርቀት ላለው ወገናቸው ፍቅር አሳይተዋል በሚል ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ ህወሓት በዘራቸው ልክ አደጋ ያልደረሰው ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት ማዕቀፍ ሆኖ ኢትዮጵያ የሁላችን በሚለው ጣፋጭ ብሔረተኝነት ምክንያት ነው፡፡
ዛሬ መራራውን ግራዋ የአማራ ብሔረተኝነት ሊግቱን የሚፈልግቱ የአማራ ብሔረተኞች የአማራን ሕዝብ ከተበተነበት የኢትዮጵያ ክፍል በዚህ አስተሳሳብ ምክንያት ሊደርስበት ከሚችለው አደጋ ሊጠብቁት የሚችሉበት አንድም ምድራዊ ሀይል እንደሌለ እና እንደማይኖር የተገነዘቡ አይመስለኝም፡፡ ከላይ መግለፅ እንደሞከርኩት ግራዋ ለመጋት የሚነሳን ሀይል ቢያንስ ትፋቱ ይደርሰዋል፡፡ ሲቀጥል ደግሞ ተገዶ ግራዋውን እራሱ ደጋግሞ ይጋተዋል፡፡ ማለት የፈለኩት የግራዋ ብሔረተኞች ክልላችን በምትሉት ተደራጅቶ መንቀሳቀስ መብት ቢሆንም ይህን ግራዋ ብሔርተኝነት ይዞ ወደ ሌሎች የአገራችን ክፍሎች መንቀሳቀስ ግን አደጋው የከፋ ይሆናል የሚል ማስታወሻ መክተብ ነው፡፡ ይህን በፍቅር ያልተገራ ቁጭትና ብሶት ያዘለ ብሔረተኝነት ለማንም አይጠቅምም፡፡ የቀድሞ ቁስልን ማሻር አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ቀጣይ አዲስ ቁስል ይፈጥራል የሚል ስጋት አላኝ፡፡ ጣፋጩን ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት እንዳይመርዙት መጠበቅ የግድ ይለናል፡፡ ኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ይለምልም፡፡
Filed in: Amharic