>

የበረከት ስምኦን መጽሐፍት - በመጽሐፍ ሰበብ ኪራይ መሰብሰብ!!! (ዉብሸት ሙላት)

የበረከት ስምኦን መጽሐፍት 
በመጽሐፍ ሰበብ ኪራይ መሰብሰብ!!!
ዉብሸት ሙላት
የበረከት ስምኦን ሁለቱም መጽፍሐት ማለትም “የሁለት ምርጫዎች ወግ” እና “ትንሳኤ ዘ-ኢትዮጵያ” የታተሙት ውጭ አገር ነው፡፡ የመጀመሪያው ኬንያ ሁለተኛው ደግሞ ህንድ፡፡ ሁለቱም የህትመት ጥራታቸው በአውሮፓውያን ደረጃ ነው፡፡ በተለይ ሁለተኛው አስደናቂ ነው፡፡
እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ማተሚያ ቤቶች የእሳቸውን መጽሐፍ ማተም ስለማይችሉ ውጭ አሳተሙ፡፡ የሚያንቆለጳጵሱት ዕድገት የእሳቸውን መጽሐፍ እንኳን የማተም የጥራት ችግር አለበት ማለት ነው፡፡ ደረጃው ለእሳቸው አይመጥንም ማለት ነው፡፡
ከእዚህ በተጨማሪ ስለ ውጭ ምንዛሬ ቁጠባ፣ የውጭ ምርትን በአገር ውስጥ ስለመተካት ወዘተ ሳይታክቱ ያወራሉ፡፡ እሳቸው ግን አገር ውሥጥ ማሳተም የሚችሉትን መጽሐፍም ውጭ ያሳትማሉ፡፡ “የቄሱን ቃሉን እንጂ ሥራውን አትከተል” መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡ አቶ በረከት የሚያወሩት ለእሳቸው አይሠራም፡፡ ዶላርም ቢሆን ለበረከት ከሆነ ይፈቀዳል፡፡ መጽሐፍ ለማሳተም ዶላር ማግኘት ለሌላ ሰው ባይፈቀድም፡፡ ዶላር ካላስፈቀዱ ውጭ ዶላር አላቸው ማለት ነው፡፡ ካልሆነም እንደባለፈው ባለሐብት አሳትሞላቸው ሊሆን ይችላል፡፡
“የሁለት ምርጫዎች ወግ”ን ወጪ የሸፈኑት ሼክ ሙሃመድ አላሙህዲን እንደሆኑ ሰምተናል፡፡ መቼም ከዚህ በላይ ኪራይ ሰብሳቢነት ካለ አቶ በረከትም ስለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያወሩት ለአፋቸው ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ አንድ ባለሃብት ጋር በዚህ መጠን መሞዳሞድ ካለ የበላ ሆድ እንደማያስችለው የታወቀ ነውና፡፡
የበረከት ኪራይ ሰብሳቢነት በሁለት ምርጫዎች ወግ፤
ለአቶ በረከት፣ የሄን መጽሐፋቸውን አላሙህዲን ነው አሉ ያሳተመላቸው፡፡ ለዚያውም ኬንያ፡፡ የታተመው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ በዚያን ወቅት የመሸጫ ዋጋው 85 ብር ነው፡፡ የተሸጠው ደግሞ በዋናነት በብአዴን አደረጃጀት በኩል ነበር፡፡ በየወረዳና በየከተማው በሚገኙ ጽሕፈት ቤቶች አማካይነት ለመሥሪያ ቤት ተጠሪ የብአዴን ሰዎች የተወሰነ ቁጥር ያለውን መጽሐፍ ሽጠው ገቢ እንዲያደርጉ ግዴታ ተጣለባቸው፡፡ እኔ እራሴ የገዛሁት በዚህ መንገድ ግዴታ ከተጣለባቸው ሰዎች፣ለዚያውም “ከደመወዜ ቀንሼም ቢሆን ሽጥ የተባልኩትን አስር መጽሐፍ ዋጋ እከፍላለሁ፡፡ ካልሸጥኩ ልገመገም እችላለሁ” አለኝ፡፡ እኔም አንድ ገዛሁት-በብር 85፡፡
ለአቶ በረከት፣ የአከፋፋይ ክፍያ የሌለበት፣ የአሳታሚ የለበት፡፡በዚያ ላይ ከገበያ ሥርዓት ውጭ በድርጂት በኩል ተሸጠ፡፡ ከዚህ በላይ ምን ኪራይ ሰብሳነት አለ?
በነገራችን ላይ ህላዌ ዮሴፍም ለመጽሐፍ ሻጮች በተለምዶ ለአከፋፋይ የሚቀነሰውን የዋጋውን ሠላሳ አምስት በመቶ ሳይቀነሱ በመጽሐፉ ዋጋ አስረክበው፣ሻጮቹ የመጽሐፉን ዋጋ (መቶ ብር) ሽጠው እንዲሰጡ አድርገዋል፡፡ በነጻ እንዲሸጡላቸው፡፡ በተለይ ለገበያ የቀረበ ሰሞን፡፡ ከዶ/ር ዓቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም በፊት ባለሥልጣን ስትሆን እንዲህ የማድረግ ሥልጣንም ጭምር ነበር፡፡
(እግረ መንገዳዊ ወግ እነሆ፡፡ የአቶ በረከት  የመጀመሪያው መጽሐፍ ምርቃት የተደረገው ሸራተን ሆቴል ነበር አሉ፡፡ ያው አሉ ነው-እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግን ደግሞ የነገረኝ አንድ መምህሬ ነው፡፡ እናም ምርቃቱ ላይ አላሙህዲን ተገኝቶ፣ ንግግር ሲያደርግ “ባላነበውም ጥሩ መጽሐፍ ነው” አለ አሉ፡፡)
በመጽሐፍ….ተጨማሪ የኪራይ ሰብሳቢ ድርጊታቸው
በመጽሐፍ አማካይነት አቶ በረከት የፈጸሙት ሌላ ኪራይ ሰብሳቢነትም፣ አማራ ላይ የሠሩትም ደባ አለ፡፡ ይኼኛው የተፈጸመው በመዝሙር ፈንቴ አማካይነት ነው፡፡ መዝሙር፣ በአላሙህዲን ‘ስፖንሰር’ አድራጊነት “አፍሪካዊው ልዑል” የሚል መጽሐፍ ተረጎመ፡፡ አሳተመለትም፡፡ መዝሙር የአቶ በረከት ባለቤት (ሚስት) ወንድም ወይም ሌላ የቅርብ ዘመድ፣ የኢሕዴን ታጋይ ነው፡፡ በአቶ በረከት በሁለቱም መጽሐፉ ላይ ተመስጋኝ ነው፡፡
የመዝሙርም፣ እንደ በረከት መጽሐፍ በብአዴን አደረጃጀት በኩል መቶ ብር እንዲሸጥ ተደረገ፡፡ ያው ይህም ከገበያ ሥርዓት ውጭ ነው፡፡ በዚያን ወቅት መቶ ብር ሲበዛ ውድ ነው፡፡ በዚያ ላይ አማራን የሚሳደብ፡፡ አቶ በረከት አማራን የሚሳደብ መጽሐፍ ፈልጎ አስተርጉሞ፣ በብአዴን አማካይነት በመሸጥ አማራን አሰደበ፡፡
የመዝሙርን መጽሐፍ በሚመለከት፣ የብአዴን አባል ሆኖ፣ ትንሽ ትንሽ አማራነት የተሰማቸውና ያነበቡት ሰዎች በዚህ መጽሐፍ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በግል ሲናገሩ ይሰማ ነበር፡፡ የብአዴን አባል ላልሆነ ነው ብዙ ጊዜ ያወሩ የነበረው ምክንያቱ ደግሞ ለአባላት ካወሩ ስብሰባ ላይ እንዳይገመገሟቸው ስለሚፈሩ ነው፡፡ ስንት ክፉ ጊዜ አልፏል’ኮ ጃል!
በነገራችን ላይ ይህን መጽሐፍ ሬዲዮ ፋና ተርኮታል፡፡ ከሻሸመኔ የሚተላለፈው ፋና ኤፍኤም በኩል ደቡብ ክልልን የሚያዳርሰው ሥርጭት ግን እንዳያስተላለፍ በደቡብ ክልል አስተዳደር አማካይነት ተከልክሏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የመንጃ እና የማና ማኅበረሰቦች ላይ ሌላ ጉዳት ያስከትላል ተብሎ ነው፡፡
አቶ በረከት አማራን ለማጥላላት መጽሐፍ ያስተረጉማል፡፡ እንዲተረክ ያደርጋል!!
አማራን እወክላለሁ የሚል ድርጅት አመራር ነው፡፡ የዚህ ድርጊት ለክፋቱ ደርዝ የለውም፡፡ አማራን የሚሰድብ መጽሐፍ ራሳቸው አማራዎቹ እንዲያነቡት በድርጅት ሰበብ ማስገደድ፣ እራስን እንደመስደብ ምን አዋራጅ ነገር አለ! አቶ በረከት ግን አማራ እራሱን በራሱ እንዲያዋርድ፣ በራሱ ሲያንሰው በዘመዱም ያሰድባል፡፡
ተጨማሪ በነገራችን ላይ ፡- “አፍሪካዊው ልዑል” የሚለው መጽሐፍ ላይ ከጀርባው አስተያየት የጻፉት መጽሐፉ በታተመበት በወቅት የውጭ ጉዳይ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ናቸው፡፡ እሳቸው ስለመጽሐፉ ሲናገሩ “ሥነ-ጽሑፋዊ ፋይዳው እንደ ፍቅር እስከ መቃብር ነው” አሉ፡፡ አቶ ኃይለማርያም ፣ምናልባት ፍቅር እስከ መቃብርን አራተኛ ክፍል ሆነው ስላነበቡትና ስለረሱት ይሆናል እንዲህ  የሥነ-ጽሑፋዊ ዉበቱን ዘመን አይሽሬነት ወደ አፍሪካዊው ልዑል መጽሐፍ ዝቅ አድርገው ያረከሱትና ያዋረዱት፡፡
አቶ ኃይለማርያም፣ አራተኛ ክፍል ሆነው እንዳነበቡት የሰማሁት የ2010 ዓ.ም. ዘመን መለወጫ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ነው፡፡ ለነገሩ ስላነበቧቸው መጽሐፍ ሲናገሩ “አቤ ጉበኛ፣ አንድ ለእናቱ …. “እያሉ ተናግረዋል፡፡ አቤ ጉበኛ የአንድ ለእናቱ ደራሲ መሆኑ ቀርቶ ራሱ መጽሐፍ የሆነ ይመስል፡፡ እናም ይህንን እኩይ ጽሑፍ ከፍቅር እስከ መቃብር ጋር አነጻጸሩት፡፡ የደሕዴኑ ሊቀመንበር፣እንዲህ ብለው ያንቆለጳጰሱትን መጽሐፍ የደቡብ ክልል ትረካውን በክልላቸው ውስጥ እንዳይተላለፍ አድርጎታል፡፡ ያው የዚያን ጊዜው ብአዴን መጽሐፉን በየጽሕፈት ቤቱ አሻሽጧል፡፡ አማራን ሰድቧል፡፡ አሰድቧል፡፡ ምን ይደረግ እነበረከት አዝዘዋልና!
አቶ በረከት “በሁለት ምርጫዎች ወግ” ላይ ብዙ ሰዎች ተሳልቀዋል፡፡ በተለይ አንዷለም አራጌ ላይ ልግጫቸው የበዛ ነው፤ለከት የለውም፡፡ እነ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያምንና ሌሎች የቅንጅት አመራሮችን (በቅንጅት አመራርነታቸው) ደግሞ እንዴት እንዳታለሏቸው በመስመር መካከል ንባቦች ነግረውናል፡፡
ምርጫ 97ትን ተከትሎ 1998 ከባተ በኋላ ሰልፍ ተጠርቶ ስለነበር ሰልፉን ካራዘሙ ቅንጅትና ሕብረት ባቀረቧቸው በስምንቱም ነጥቦች ላይ ኢሕአዴግ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን መግለጹን ያስታውናል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ኢሕአዴግ ሕዝቡን ለማግኘት ጊዜ አጥሮት ስለነበር  ሕዝቡን ለማግኘት ሲል እንጂ በስምንቱም ነጥቦች ላይ ለመደራደር እንዳልነበር ከአቶ በረከት  መጽሐፍ መረዳት ይቻላል፡፡ እሳቸው ያላገጡባቸው ሰዎች አሁን ሕዝብ ጀግናዬ ብሏቸዋል፡፡ ለነገሩ ያኔም ቢሆን እነአቶ በረከትን ፈርቶ ካልሆነ በስተቀር ሕዝብ እንደሚወዳቸው የታወቀ ነው፡፡ እንዲህ በሕዝብ ሲያላግጡ የነበሩት አቶ በረከት አሁን ላይ ቢያንስ በአማራ ክልል በመንገድ ሕዝብ እያያቸው ያለፍርሐት የሚንቀሳቀሱበት ጊዜ አብቅቷል፡፡ በየሚዲያው ብቅ እያሉ ሕዝብ ላይ የመዛትና የመሳለቅ ዕድላቸው ጠብቧል፡፡ ጊዜ ደጉ!
በአሁኑ መጽሐፋቸው ላይ ማን ማን ላይ እንዳላገጡ ስናነበው የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ አቶ በረከት ከጀርመናዊው መናጢ የፕሮፓጋንዳ ሰው፣ ጆሴፍ ጎብልስ በተጨማሪ  የ”Shock Doctrine” ቀማሪው ሚልተን ፍሪማንም (Milton Friedman) ሞደላቸው ይመስለኛል፡፡ ይህን ለመረዳት መጽሐፋቸውን በጥልቀት ማንበብ ነው፡፡ ያደረጓቸዋውን ነገሮችንም ማጤን  ስለ Shock Doctrine አብዝታ የጻፈችውን፣ ዘጋቢ ፊልም ያላትን ናኦሚ ክሌንን (Naomi Klein) በተደጋጋሚ እንደጠቀሷት ከአዲሱ መጽሐፋቸው መጨረሻ ላይ መመልከት ይቻላል፡፡ ስለ Shock Doctrine ማወቅ የሚፈልግ ሰው፣ በቀላሉ እሷ የምትተርከውን The Shock Doctrine የሚለውን ዘጋቢ ፊልም ማየት ነው፡፡ ወኔው ያለው (ወደ 600 ገጽ ገደማ ነው) ደግሞ መጽሐፏን ማንበብ ነው፡፡
መጽሐፉን ጊዜ ሲኖረን እናነበዋለን፡፡ ለክፉም ለደጉም ገዝተነዋል-አንጀታችንን አስረን ፤ 300 ብር አውጥተን፡፡ የምናገኛቸውን የክፋት ሐሳቦች እናጋራለን፡፡
እዚህ ወረቀት ላይ ያልተጣለ የግብር ዓይነት ባለመኖሩ የመጽሐፍ ዋጋ ሰማይ ነክቷል፡፡ አቶ በረከት ግን የመጽሐፍ ህትመት ድጎማ በሚደረግበት አገር ያሳትማሉ፡፡ የሠሯት አገር እንዲህ አስቸጋሪ ናት-ጸረ-ዕውቀትም ናት፡፡ ዕውቀት እንዳይስፋፋ የህትመት ግብዓቶች ላይ አሉ የተባሉ የግብር ዓይነቶችን ሁሉ የምትጥል የጉድ አገር፡፡
ያው የኢሕአዴግ ሰዎች የሚጽፉት አንብቦ መጨረስ ትልቅ ጽናት ይጠይቃል፡፡ በዚያ ላይ “ትንሳኤ ዘ-ኢትዮጵያ” 420 ገጽ ነው፡፡ ቻው!!!!!!
Filed in: Amharic