የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ከነሀሴ 14 እስከ 16/2010 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የጥልቅ ተሃድሶውን አፈፃፀምና ያስገኘውን ውጤት በተለመደው ድርጅታዊ ባህል፣ ዴሞክራሲያዊነትን በተላበሰ እና በሰከነ አግባብ በጥልቀት ገምግሟል፡፡
ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የጥልቅ ተሃድሶውን ተከትሎ የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች የአመራር ፈጠራ ታክሎባቸው የለውጡ ቱርፋት የሆኑ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አረጋግጧል፡፡
ከአሁን በፊት ውሳኔዎች እየተወሰኑ እና አቅጣጫዎች እየተቀመጡ በአፈፃፀም ድክመት ይታይባቸው የነበሩ ጉዳዮች በፍጥነት መፈፀም በመጀመራቸው በዚህ አጭር ጊዜ ሊመዘገቡ ይችላሉ ተብለው የማይታሰቡ ድሎች ተመዝግበዋል፡፡ እነዚህ ድሎች የመላ የኢትዮጵያውያንን ድጋፍ ያስገኙና ተስፋውን ያለመለሙ መሆናቸውን በአድናቆት ተመልክቷል፡፡
በፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች መመዝገብ የጀመሩ ለውጦች ጉልህና ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባችው መሆኑንም ገምግሟል፡፡
በፖለቲካው መስክ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ታራሚዎችን ከእስር ከመፍታት ጀምሮ፣ የትጥቅ ትግል ያካሂዱ የነበሩ የተለያዩ ድርጅቶች የትጥቅ ትግላቸውን በማቆም በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ በውይይትና በድርድር መተማመን በመፍጠር ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ የተሰሩ ሥራዎች፣ ህዝቡ ያለምንም መሸማቀቅ ሀሳቡን በተለያየ መንገድ በነፃነት ማራመድ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩ፣ የመንግስትን ሚዲያን ጨምሮ በሌሎች ሚዲያዎችም የተለያዩ ሀሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት ሁኔታ መጀመሩ፣ ተዘግተው የነበሩ ድረ-ገፆች መከፈታቸው የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት አይነተኛ ሚና መጫወታቸውን ገምግሟል፡፡
ለዜጎች ዋጋና ክብር በመስጠት ከሀገር ውስጥ ባሻገር በጎረቤት ሀገራትና በመካከለኛው
ምስራቅ ዜጎቻችን ከእስር እንዲፈቱና የነፃነት አየር እንዲተነፍሱ መደረጉ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብበዋል በሚል በተደጋጋሚ ከህዝብ ቅሬታ የሚቀርብባቸውን ህጎች ህዝብንና የመስኩን ሙያተኞች ባሳተፈ መልኩ ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ስኬቶች መሆናቸውን ስራ አስፈፃሚው ካያቸዉ ጉዳዮች አንዱ ነዉ፡፡
በሰብአዊ መብት አያያዝ አስከፊ ችግር የነበረባቸው የማረሚያ ቤቶች እና ሌሎች የፀጥታና ህግ አስከባሪ ተቋማት ሪፎርም ለማድረግ አመራሮቹን ከመለወጥ ጀምሮ እየተሰራ ያለው ሥራ እንዲሁም ህዝብ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያነሳባቸው ተቋማት ኃላፊዎችን በማንሳት የተጀመረው የአመራር ሪፎርም የተቀመጠውን አቅጣጫ በመከተል የተፈፀሙ እና ውጤትም ያመጡ መሆናቸውን ስራ አስፈፃሚው አረጋግጧል፡፡
እነኝህ እርምጃዎች የህዝቡን ድጋፍ ያገኙ፣ እንደ ሀገር የመቀጠል ስጋት ውስጥ ገብተን ከነበረበት ተጨባጭ አደጋ በመውጣት አንፃራዊ ሰላም እንዲመጣ ያስቻሉ መሆኑን በአዎንታ ገምግሟል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በነፃነት በሀገራቸው ጉዳይ እንዲሳተፉ ያስቻለ ውጤታማ ሥራ መከናወኑንና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ተቀምጧል፡፡
በዲፕሎማሲው መስክ የተሰራው አኩሪ ሥራ የሀገራችንን ተቀባይነትና ተደማጭነት ያሳደገ መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው ገምግሟል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት የህዝብ ለህዝብ እና የጋራ ጥቅሞች ላይ በመመስረት ህዝባዊነትን ተላብሶ በፍጥነት እንዲሻሻል ለማድረግ መሰራቱ ውጤታማ እንደሆነ አስቀምጧል፡፡
ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት በዘላቂ የጋራ ጥቅሞች ላይ ተመስርቶ እንዲጠናከር የተደረገው ጥረትና ያስገኘው ውጤት እንዲሁም ደግሞ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር የተደረጉ ግንኙነቶች እና በሀገራችን እየመጣ ያለውን ለውጥ ተከትሎ ከአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እየተገኘ ያለው ድጋፍ በአለም አቀፍ ደረጃም ኢትዮጵያ ያላትን ተሰሚነት ያሳደገ መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው ገምግሟል፡፡
በማህበራዊ ዘርፍ ለበርካታ አመታት በሁለት ሲኖዶሶች ተከፍላ የቆየችው የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የእስልምና እምነት ተከታዮችን መከፋፈል በማስቀረት ወደ አንድነት ለማምጣት የተደረገው ጥረት በኢትዮጵያውያን መካከል አንድነትን ለማጠናከር ያስቻሉ ጅምር ሥራዎች መሆኑን አረጋግጧል፡፡
በኢኮኖሚው መስክ በተከናወኑ ሥራዎች የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለል የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰድ በመጀመራቸው ችግሩን ለማስታገስ ያስቻሉ ውጤቶች መመዝገባቸውን በማየት ጥረቱ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ አስምሮበታል፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በመሰረታዊነት ለማቃለል የሚያስችለውን የግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ምርትና ምርታማነት የማሳደግ ስራ ላይ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
የዋጋ ንረት እያሳየ የነበረው ዕድገት እንዲገታ በማድረግ ረገድ መምጣት የጀመረውን ውጤት በአዎንታ ወስዶ ወደ ነጠላ አሀዝ እንዲወርድ ተጨማሪ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉንም የመፍትሄ አማራጮች በመጠቀም ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ገምግሟል፡፡
በተመሳሳይ ህገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የተጀመረዉ ስራና አፈፃፀማቸው የተጓተቱ ሜጋ ፕሮጀክቶች ያሉባቸው ችግሮች ተቃለው በተቻለ ፍጥነት እንዲጠናቀቁ እየተሰራ መሆኑን በጥንካሬ ገምግሞ ይሄው መልካም ጅምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ኢትዮጵያዊ ማንነት ተገቢውን ክብር እና ቦታ እንዲያገኝ የተጀመረው ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት በመስጠት ከብሔር ማንነት ጋር ተሰናስሎ እንዲፈፀም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የተጀመረው ለውጥ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ጥልቀት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ለውጡን በሁሉም ደረጃ ከማድረስና ከማስፋት አንፃር የሚታየውን እጥረት በፍጥነት ማስተካከል እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል::
ስራ አስፈፃሚው በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ያለው አንድነት በሚፈለገው ደረጃ የደረሰ እንዳልነበረ በመገምገም ይህንኑ የሚያሻሽልና የአመለካከት አንድነት ለማምጣት ያስቻለ ውይይት አካሂዷል፡፡ ውይይቱ ወደ ተጨባጭ ተግባር እንዲለወጥም በአፅንኦት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በለውጥ ሂደት እንደሚያጋጥሙ የሚጠበቁ ችግሮች የለውጡን ሂደት እየተገዳደሩት ያሉ መሆኑን፣ በተለይ ደግሞ የተገኘውን ነፃነት በአግባቡ በመያዝ ተቋማዊ እንዲሆን ለውጡን መደገፍ ሲገባ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የሚደረገው እንቅስቃሴ ከወዲሁ ካልተገታ ስርዓት አልበኝነት እንዲነግስ ሊያደርግ የሚችል ዝንባሌ እየተስተዋለ መሆኑን በአንክሮ ተመልክቶ የህግ የበላይነት ለማስፈን የሚያስችሉ ስራዎች በጥብቅ ክትትል እንዲሰሩ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በዚህ ረገድ ህዝቡ፣ የፀጥታና ደህንነት አካላት በለውጡ መንፈስ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በአጠቃላይ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሁሉም መስኮች ሊባል በሚችል ደረጃ ለውጡን ተከትሎ የተከናወኑ ሥራዎች እና የተመዘገቡ ውጤቶች አመርቂ መሆናቸውን እንዲሁም ለውጡን የሚገዳደሩ ችግሮች መኖራቸውን፣ ችግሮቹንም ተቋማዊ አሰራር በመከተል እንዲሁም ህዝቡን በተደራጀ መንገድ በማሳተፍ እየፈቱ መሄድ ብሎም የተጀመረውን ለውጥ ዳር ማድረስ የወደፊት የትኩረት እና የርብርብ ማዕከል እንደሚሆን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ለዚህም ስኬት ህዝቡ እያሳየ ያለውን የለውጥ ባለቤትነት እና ድጋፍ ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ኢህአዴግ ጥሪውን ያቀርባል! ለእስካሁኑ ድጋፍም የላቀ አድናቆትና ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
የድርጅታችን አባላትና አመራሮች የተጀመረዉ የለዉጥ ጉዞ ዳር እንዲደርስ በህዝባዊነት መንፈስ በትጋት እንድትንቀሳቀሱ ድርጅታችሁ ጥሪ ያቀርብላችኋል!