>

የትግራይ ጉዳይ ሀገርን ያሰጋል-ደርግ የሰራው ስህተት መደገም የለበትም!! (ጋዜጠኛ እና አክቲቪስት አብርሀም በላይ)

የትግራይ ጉዳይ ሀገርን ያሰጋል-ደርግ የሰራው ስህተት መደገም የለበትም!! 
ጋዜጠኛ እና አክቲቪስት አብርሀም በላይ
የትግራይ ህዝብ ጉዳይ በአገር አቀፍ ፖለቲካ የፊት ወንበሩን ይዞ አያውቅም። ይህ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ቀደም ባሉ መንግስታት የነበረ እውነታ ነው። ያለፉት መንግስታት ትግራይን ችላ ስላሉ፣ ከፍ ያለ ዋጋ ከፍለው አልፈዋል። ጦሱ ከትግራይ አልፎ ለኢትዮጵያ ተረፈ እንጂ።
በህዝብ ቁጥር ከሄድን ያነሳሁት ጉዳይ ላያሳስበን ይችላል። ግን የትግራይ ጉዳይ በቁጥር የሚወሰን አይደለም። ትግራይ ምን ልዩ የሚያረጋት ነገር ተፈጠረና ከቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ልዩ ትኩረት ይገባታል የምትለው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ተገቢም ነው።
ተወደደም ተጠላም፣ ኢትዮጵያን ተቆጣጥሮ የቆየው ኃይል መሰረቱ ትግራይ ውስጥ ነው። ይህ ኃይል በትግራይ ህዝብ ላይ በውድም ይሁን በግድ በ44 አመት እንቅስቃሴና አገዛዝ ያሳደረው ተጽእኖ እጅግ በጣም ከባድ ነው። የህወሃት አመራር ፍጹም ጨካኝ አምባገነን ነው። በዚህ ምክንያት በህዋህት ስር ወድቆ የኖረው የትግራይ ህዝብ “ነፃነት” ምን እንደሆነ ሳያጣጥም እስከዛሬ ድረስ አለ።
ጠ/ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ፣ ከትግራይ በስተቀር በኢትዮጵያ የነጻነት ነፋስ እየነፈሰ እንደሆነ ይታወቃል። በትግራይ ግን ያው የጨለማው ዘመን ቀጥሏል።
1. ህወሃት የትግራይ ህዝብን ያለገላጋይ ከ40 አመት በላይ የህዝቡ ሉ ዓላዊነት ገፎ፣ ረግጦና አደኽይቶ ስለገዛው፣ ህዝቡ ጠላቱን አግዝፎ በማየት ወደ ተስፋ መቁረጥ ያዘነበለ ይመስላል።
2. የትግራይን ህዝብ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ታግሎ የሚያታግለው ድርጅት ማጣት።
3. ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድም ቢሆኑ ትግራይን እንደፍጥርጥራችሁ ከህወሃት ጋር ተወጡት ብለው የተዋት ይመስላል።
4. በተለያዩ ከተሞች ሰረተው፣ ቤተሰብ መስርተው በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ጥቃቶች፣ ህዝቡ ህወሃትን “ከማይውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል” እንዲል አድርጎታል። ይህ ደግሞ የጠ/ሚ አብይን አካሄድ እየተቃወመ ላለው የህወሃት አመራር ወርቃማ እድል ፈጥሮለታል።
አደጋው ለኢትዮጵያ ይተርፋል
ግልጽ ለማድረግ በህወሃት እድሜ ለኢትዮጵያ የሚቆረቆሩ የድርጅቱ አመራር አባላት በሂደት ጠፍተዋል። የቀረው የመለስ ቡድን ነው። የስብሃት ነጋ ቡድን ነው። ይህ ቡድን ደግሞ የኦርቶዶክስ ቤ/ክርስትያን እና የአማራ አክርካሪታቸውን ተበጠሰዋል” ሲል ሲደነፋ የኖረ ኃይል ነው። በቅርቡ ዶ/ር ደብረጽዮን “በእኩልነት የማንኖርባት ኢትዮጵያ ትበታተን” ሲል የአፍ ወለምታ አለነበረም።
የህወሃት መሪዎች ጠ/ሚ አብይ አህመድ የሚመሩትን ለውጥ በግልጽ እየተቃወሙ ይገኛሉ። ለምሳሌ፦
1. የህወሃት መሪው ዶ/ር ደብረጽዮን በርካታ ወንጀሎች ፈጽሟል፣ ለፍርድ መቅረብ አለበት የተባለው የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ኢሌን “ተፈቶ ወደነበረበት ቢመለስስ” ሲል ያላንዳች ኀፍረት በሰሞኑ የኢህአዴግ ስብሰባ ላይ መጠየቁ፣ እውነትም ህወሃት እንደ አብዲ ኢሌ የመሳሰሉ ወንጀለኞችን በገንዘብና በጠመንጃ ሲያደራጅ የኖረ ወንጀለኛ ድርጅት መሆኑን በግልጽ ይመሰክራል።
2. ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር (ሞንጆሪኖ) የተባለችው የህወሃት የፖሊት ቢሮ አባልም ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ መመሪያ ሆኖ የኖረውን “አብዮታዊ ዴሞክራሲን” እየጣሱ አገሪቱ ወደ ባሰ የእርስ በርስ ግጭት እየወሰድዋት እንደሆነና ኢህአዴግም አገሪቷን ለመታደግ ወደ ቀድሞው መመሪያው መመለስ እንዳለበት በአንክሮ ስትናገር በሶሻል ሚድያ የተለቀቀ የቪድዮ ማስረጃ ያሳያል።
ከነዚህ ሁለት የህወሃት ከፍተኛ አመራር የምንረዳው ነገር ቢኖር ይዋል ይደር እንጂ፣ ህወሃት ለውጡን አጨናግፋ ወደ ጨለማው ዘመን ለመመለስ ወደ ኋላ እንደማትል ነው። ይህ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተደገፈው ሰላማዊ አብዮትን ማጨናገፍ ካልተቻለ ደግሞ በባርነት የያዘችውን ህዝብ ይዛ ትግራይን ከኢትዮጵያ ገንጥላ ለመሄድ እንደሆነ፣ ቅድመ-ዝግጅቱም እንደተጀመረ በአንዳንድ የትግራይ አዛውንቶች በድፍረት እየተነገረ ያለ ሃቅ ነው።
የሰይጣን ጀሮ አይስማውና ትግራይ ተገነጠለች ማለት ድፍን ኢትዮጵያ ወደ የእርስ በርስ ጦርነት ገባች ማለት ነው። ሩቅ ሳንሄድ ትግራይን ያስገነጠለው ኃይል ራሱ ጠንካራ መንግስት ሆኖ እንዲወጣ ግዛት አስፍቶ ካርታ አሳትሞ “ነጻነት” ማወጁ አይቀርም። ህወሃት ይህ ሲያደርግ፣ የተቀረው ኢትዮጵያዊው ኃይል እጁን አጣምሮ ዝም ብሎ ከሩቅ ያየዋል ማለት አይደለም። ሀገርን ከመገነጣጠልና ከመፈራረስ ለማዳን፣ ተገንጣዮችን ድል ነስቶ ያአገር ሰላም፣ ክብርና ሉዓላዊነት ለማስመለስ ከፍተኛ መስዋእትነት ይከፍላል ማለት ነው።
መፍትሄ
አዲሱ መንግስት ከኢትዮጵያ ህዝብ ያገኘውን ሙሉ ድጋፍ ተጠቅሞ –
1. የትግራይን ህዝብ ከአረመኔያዊ የህወሃት አገዛዝ ነፃ ለማውጣት ከፍተኛ ርብርቦሽ ማድረግ አለበት። በትግራይ እስር ቤቶች የሚማቅቁትን እንደሌሎች የፖለቲካ እስረኞች በነጻ መለቀቅ አለባቸው።
2. በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ማንኛውም አይነት ጥቃት የሚሰነዝር ወንጀለኛን መንግስት በአፋጣኝ እየያዘ ለፍርድ ማቅረብ አለበት። ይህ ጉዳይ በተለይ ህወሃት የሚፈልገው ጉዳይ ስለሆነ፣ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ትግራዮች እየተፈናቀሉ ወደ ትግራይ እንዲመለሱ ህወሃት ሳይጠየቅ የትራንስፖርት አገልግሎት ሁሉ ሊሰጥ ዝግጁ ነው። ለህዝቡ ብሎ ሳይሆን፣ መሰሪ አላማውን ለማሳካት እና የትግራይ ተወላጆችም “ያውላችሁ! አገራችን የምትልዋት እንዴት እንደ ጠላት እንደምታስተናግዳችሁ” እያሉ የህዝቡን ኃይል ኢትዮጵያን ለማበጣበጥ ሊጠቀምበት ስለሚፈልግ ነው።
ከላይ የተጠቀሱትን እውን ለማድረግ መንግስት ብሄራዊ የውይይት መድረኮችን እያዘጋጀ፣ የትግራይ ምሁራንን በመጋበዝ ህብረተሰቡ ይበልጥ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ማድረግ፣ በህወሃት መሪነት በትግራይ እየተጠነሰሰ ያለውን ጉዳይ ማምከን ይኖርበታል። ይህም በሀገር ደረጃ ቀደም ብሎ ከተሰራ “ሳይቃጠል በቅጠል” ይሆንልናል።
ደርግ ምንም አያመጡም ብሎ ትግራይን ልቆላቸው መሄዱ ለዚህ ሁሉ ችግር እንድንዳረግ ዳርጎናል። የሽብር ማሰልጠኛ እና ማከፋፈያ ማዕክል ያደርጉታል። ድርግ ጥሎላቸው መውጣቱ እንደፈለጉ እንዲፈነጩ እድል ፈጥሮላቸው ነበር። አሁንም ያ ታሪክ መደገም የለበትም። ተመልሰው ወደ ስልጣም ባይመጡም እንኳን ክልሉ ውስጥ ሁነው የትግራይ ህዝብ ከሌላው ወገኑ የመለየት ስራ መስራታቸው እንደ ሀገር ትልቅ አደጋ ያመጣል። ነፃነት ለሁሉም ህዝብ ይገባል።
 
ኢትዮጵያ በአንድነቷ ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
Filed in: Amharic