>
9:58 pm - Sunday January 23, 2022

ትንቢተ ዮሐንስ አድማሱ ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች (ሰሎሞን ዳውድ)

ትንቢተ ዮሐንስ አድማሱ ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች

ሰሎሞን ዳውድ

የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ኢትየጵያዊው ገጣሚ ዮሐንስ አድማሱ “እስኪ ተጠየቁ” በተሰኘው ግጥማቸው ላይ ከሕያዋኑ የልባቸውን ጠይቀውት ምላሽ ቢያጡ በመቃብር ዓለም የሚኖሩትን በስንኝ ቋጠሮ ይጠይቃሉ፤ ጥያቄዎቻቸው ዘመን ተሻግረው ዛሬን የሚያወሱ በተለይም ፖለቲካውና ባለስልጣናቱ ሕዝቡን የሚያስተዳድሩበትን መረን የለቀቀ ስርዓት የሚገመግሙና የሚተቹ ትንቢታዊ የግጥም ስንኞችን ቀነጫጭቤ ለማቅረብና ዕዝነ ልቦናውን ለሰጠኝ ድርሳነ “እስኪ ተጠየቁ”ን ዋቢ አድርጌ ምክረ-ዮሐንስ አድማሱን ጀባ ለማለት ነው፡፡  

በግጥም መድብሉ መጀመሪያ ላይ “ያልተፈፀመ መግቢያ – ተወርዋሪ ኮከብ” ሲሉ የመፅሃፍ መግቢያ የቀነበቡትና እነዚህን ግጥሞች ከሚያነሷቸው ቁም ነገሮች አንፃር ትላንት፣ ዛሬና ነገን የሚዳስሱ የሰው ልጆች የነፍስ ጥያቄዎች እንደሆኑ አስረግጠው የሚተርኩልን ዶክተር ፈቃደ አዘዘ ለዚህ ፅሁፌ መነሻ ሃሳብ አቀብለውኛል፡፡ ዶክተሩ አክለውም ግጥሞቹ ዘመን ጥሰው ቃል በቃል በሚባል መንገድ ቢያንስ ቢያንስ ስለዛሬው ሕይወታችንና ዓላማችን የሚናገሩ እንደሆኑ ያወሳሉ፡፡ ታዲያ በስነፅሁፍ አጋሮቻቸው በዶክተር ፈቃደ አዘዘና በደበበ ሰይፉ አገላለፅ “ተወርዋሪ ኮከብ” ሲባሉ የሚሞካሹት ዮሐንስ አድማሱ በወንድማቸው በዮናስ አድማሱ አሰናዳኢነት በ1990ዓ.ም ለሕትመት በበቃው የግጥም መድብል ውስጥ በምጡቅ ዕሳቤያቸው፣ በነብይ ዓይናቸው አሻግረው ተመልከተው የተቀኙትን ቅኔ ባነበብኩ ግዜ ይህ የእኔው ጊዜ የተገለፀበት መንገድ ዓለሙ የመቃብር ዓለም፣ ዘመኑ የሙት ዘመን፤ ነዋሪው በድን ሆኖ ታየኝና ከግጥሙ የተወሰኑ ስንኞችን እንዲህ አየኋቸው፡፡ “እስኪ ተጠየቁ” በሚለው የግጥም መድብል ውስጥ ባለቅኔው የልባቸውን ጥያቄ የሚመልስ አጥተው፤ መላሽ ሽተው አውጥተው አውርደው፤ ነፍስያቸው ያመላከታቸውን ሁሉ አማትረው የዚህ ዘመን ሰው ጥያቄዎች በአዕምሮአቸው ጓዳ ቢርመሰመስ እናንት በመቃብር ዓለም የምትኖሩ ሲሉ ወደ እኛ የትንቢት መነፅራቸውን አዙረው በሙታኑ መንደር በመቃብር ስፍራ መስለው እንዲህ ሲሉ ይሞግቱናል፤

እስኪ እናንተ ሁሉ ከወዲያ የምትኖሩ ከመቃብር አገር፤

እኛ እምንቆጥራችሁ በቋንቋ ነበር፡፡

ባጥንት የቀራችሁ ስጋችሁ ወስልታ፤

በማናውቀው አገር ነፍሳችሁም ዘምታ፡፡ (እስኪ ተጠየቁ፤ 36)

ባለቅኔው መኖር በመቃብር አገር ሲሉ የገለፁት ይህን ግዘፍ ነስቶ እየተላወሰ ኑሮው ግን ከመቃብር ያልተሻለው “አለሁ መኖር ከተባለ ከሞቱት በላይ ካሉት በታች” ሲል ኑሮን በማማረር የተጠመደ የኛውን ዘመን ባተሌ ቢመስለኝ፤ ባጥንት የቀራችሁ ሲሉ የሚሞግቱትም ይኸው ከሱስ፣ ከዝሙት፣ ዘረኝነት ጋር ሙጥኝ ብሎ አፅመ ርስቱ የቀረው የዘመኔ ወጣት ጋር ቢመሳሰልብኝ እምርም ነብይ አልኩኝ፤ አስከትለውም እጥር፣ ቅልብጭ ባለች አማርኛ እንዲህ ይሉናል፤

የመቃብር ዓለም ያ የሞት ግዛት፤

ፖለቲካ ኃይሉ ያገሩ ስራት፡፡

ብርሃን ነው ጨለማ ያገዛዙ ልኩ፤

ስራቱ የበራለት ስልቱ የጠፋበት የማይታወቅ መልኩ፡፡

የሃብቱስ መጠኑ እድገቱ ልማቱ፤

  እንዲያው ተቀብሯል ወይ ሆኖ ለጥቂቱ፡፡ (ዝኒከማሁ፤ 37)

“የሞት ግዛት” አሉት፤ ስለ እውነት ይህ ባለቅኔ የኛን ዘመን የኖሩት በርዕይ ሳይሆን በሕልው ነው፤ የሕሊናቸውን ተቀኝተው የልባችንን ነገሩን፤ የሞት ጥላ ያጠላበት፤ በዛሬ እሞት ነገ ሰው በጭንቅ የሚያመሽበት የፖለቲካ ስርዓት የአዳም ዘር በጨለማ፣ በድንቁርና፣ በብሄር፣ በጎጠኝነት፣ በድሕነት አረንቋ ተዘፍቆ የኖረበት፣ የሚኖርበት ከዚህ ዘመን ሌላ አለ? የለም ገጣሚው ድሕነትን ሲያጠይቁ የሃብቱስ መጠን እንዴት ነው? ሲሉ ይሞግቱናል፤ ይህማ ምን ይወራል አባት ዓለም ብዙሃኑ ተቀምቶ ባለረብጣ ከሆነ ጥቂቱ እጅግ ሰነባብቷል፤ አንዷ ለልጇ ጥቢኛ መግዢያ እጅ ሲያጥራት፤ ሌላው ድርንቢቱን ሞልቶ – ወርቅ ለብሷል፤ እውነት ነው ልዩነቱ ሰፍቷል፤ አንዱ ውሃ ያንቀዋል፤ አንዱ ሚልስ ሚቀምሰው አጥቷል፡፡

አባታቸው የበኩር ልጃቸውን ዮሐንስ ብለው ለምን እንደሰየሙት ሲገልፁ “… እወደው ስለነበር፤ እስመ ስሙ ይመርሆ ሀበ ግብሩ” ተብሎ በመፅሐፍ እንደተፃፈ እሱም በትምህርቱ በመጎበዝ በከፍተኛ ማዕረግ የክብር ዲግሪውን ተቀብሎ እያስተማረ..” በመኖሩ ልባቸው ሐሴትን እንዳደረገ ሁሉ በሞቱ ደግሞ ከባድ ሐዘን ውስጥ እንደወደቁ ይናገራሉ፡፡ እናም ይኸው የስምም የገቢርም ነብይ ባለቅኔ የዚህን ዘመን ሕዝብ ብርታት ሲጠይቁ እንዲህ ይላሉ፤

ሕዝቡ በጠቅላላው እንዴት ነው ብዛቱ፤

እንዴት ነው ብርታቱ፡፡

ከቶ ይስማማል ወይ ከሚመሩት ጋራ፤

ወይንስ ይጣላል ያሴራል ወይ ሴራ፡፡

በፍርሃት ዝም ይላል ሐሳቡን አምቆ፤

  ጥላ ወጊ ፈርቶ ዞትር ተደብቆ፡፡ (ዝኒከማሁ፤ 37)

ሲሉ ባለቅኔው ዮሐንስ ይሞግታሉ፤ የእኔም ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል፤

እውነት ነው ወዳጄ ሕዝቡ እጅግ በዝቷል፤

ግና ወኔ-መቅኔው ፈሶ፤ ፍርሐት ሸብቦታል፤

ጥላ ወጊውና ጆሮ ጠቢው በዝቷል፡፡

ብየ ዘመኑን ሹክ ብልህ

ምላሼ ባይሆን የልብህ

አንተ ግን ነብይ ነህ

የምስኪን ወገንህን አነዋወር፤  ገና በሩቁ የገለጥህ፤

እውነትም ኮከብ ተወርዋሪ ብልጭ ብለህ የጠፋህ፡፡    

ነገር ግን ዮሐንስ ከዚህ በበረታ ቃል ስለዚህ ሕዝብ የተነበዩበት የግጥም ስንኞች እጅግ ብዙ ቢሆኑም እስኪ የህቡን ስልቹነቱ፣ ለሃገር መስራት እንደነውር መቁጠሩን፣ ቆራጥነት ጥሎት መኮብለሉን ወዘተ ጠቅሰው በተቃራኒው ደግሞ ብድር፣ ወለድ አራጣ አናቱ ድረስ መልቶት በአልባስ፣ በመኪና፣ ጌጣጌጥና ጫማ ተኮፍሶ መታየት ፋሽን የሆነበት ዘመን እንደሆነ የተናገሩባቸው የሚከተሉትን የስንኝ ቋጠሮዎችን እንመልከት፤  

እንዴት ነው ነገሩ የመቃብሩ ሕዝብ፤

ልባም ነው ወይ ደፋር የጉብዝናው ዲብ፡፡

ያውቃል ወይ ጠርጥሮ ቆርጦ መነሳት፤

ባስፈለገው ጊዜ ባስፈለገው ወቅት፡፡

ፈሊጡ ምንድር ነው ማማረጥ መኪና በልብስ አሸብርቆ፤

 በግዢ በወለድ በብድር ባራጣ አለቅጥ ተራቆ፡፡ (ዝኒከማሁ፤ 38)

ባለቅኔው በመነሻቸውም የመቃብር ኑሮ ሲሉ የገለፁትን አሁንም የመቃብር ሕዝብ ይሉታል፤ እናም የዚህን ሕዝብ ኑሮ በመቃብር መስለው ያቀርቡታል፡፡ የምርም እኛ አስፈላጊ በሆነ ወቅት አስቀድሞ መጠርጠር፣ ጠርጥሮ፣ ቀድሞ መነሳት የተሳነን የመቃብር ሰዎች ነን! እውነት ነው ሀገራችንን ሳይቀር በዕዳ፣ ወለድ፣ ዱቤ አሲይዘን በራሳችንና በትውልድ ላይ የቆመርን፤ መሰልጠን መሰይጠን የሆነብን፤ ዓለም ወደ ፊት ሲራመድ እኛ ራሳችንን የገደልን ሙቶች ነን፡፡ ባለቅኔው ስለ ባለስልጣኖቻችን ማንነት ስለተቀኙት ቅኔ ስናስብ ደግሞ ይበልጥ ድርሳኑ ለእኛ የተከተበ ትንቢተ ዮሐንስ አድማሱ ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች መሆኑ ይገባናል፤   

ደግሞስ በህዝቡ ዘንድ ያለው ባለስልጣን የሕዝቡ መከታ፤

ግብዝ ነው አድር ባይ የሆዱ ከርታታ፤

ዕምነቱን የሸጠ ዓላማውን የሳተ ገደል የከተተ፡

እውነትን የሳተ፡፡ (ዝኒከማሁ፤ 38)

እርግጥ ነው ባለስልጣኖቻችን ይቅርና ዕምነት፣ ዓላማ፣ ፍቅር ሊኖራቸው፤ ፍፁም ያልፈጠረባቸው በሆዳቸው አዳሪ፤ ከሆዳቸው የሚያበልጡት አንዳቺ ነገር ያፈጠረባቸው አድር ባዮች ናቸው፡፡ ባለቅኔው ግጥማቸውን ሲደመድሙ እንዲህ ይላሉ፤

አመሰግናሁ የመቃብር ሕዝብ፤

ጥያቄየን ሁሉ ስለሰማችሁኝ ሁናችሁ ከልብ፡፡

እናንተው ትሻሉ፤

ነፍስ ካለው ሁሉ፡፡

መስማታችሁ እንኳን  ታላቅ ቁም ነገር፤

የምላሽ ጎዳናው አንድኛው መስመር፡፡

ለሐሳብ መዝለቂያ ከበሮቹ ሁሉ አንዱ ታላቅ በር፤

 ይኸው ነው አሁንም ጥንትም የነበር፡፡ (ዝኒከማሁ፤ 50)

Filed in: Amharic