>
5:13 pm - Thursday April 19, 0587

ኢሳቶች እንኳን በደህና መጣችሁ!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

ኢሳቶች እንኳን በደህና መጣችሁ!!!
ጌታቸው ሽፈራው
ኢሳት ብዙ ሰው ያነቃ ሚዲያ ነው። ያኔ ስሙን መጥራት  እንኳ በሚያስፈራበት ሰዓት፣ ያኔ ዲሽ የሚያስተካክሉትን አምኖ “ኢሳትን ጫንልኝ” ማለት በሚያስፈራበት ወቅት የቻልነውን አብረን ሰርተናል። አማራጭ በጠፋበት ሰዓት አማራጭ ሆኖ አገልግሏል።
ያኔ አንገት በሚያስቆርጥበት ወቅት በፌስቡክም፣ በኢሜልም፣ በስልክም የቻልነውን አድርሰናል። ብዙ መረጃ ወስደናል። ተከሰንበታል። አላፈርንበትም። አላዘንንበትም!
ዛሬ ስሙን ለመጥራት የተፈራው ኢሳት ወደ ሀገር ሲገባ ስመለከት በእጅጉ ደስ ብሎኛል። እንደ ትልቅ ወንጀል የላኩለት 98 ገፅ ዜና የሽብር ወንጀል ማስረጃ ተደርጎ  የተከሰስኩበት ኢሳት ወደ ሀገር ቤት በመምጣቱ ደስ ብሎኛል።
ወደ ሀገር ቤት ሲገባ ለትግሉ የተሻለ አማራጭ ይሆናል ብየ እገምታለሁ። በተለይ አሁን አሁን አንዳንድ የሚያድበሰብሷትን ነገር መቅረፍ ከቻሉ ጥሩ ይሰራሉ ብየ አምናለሁ።  ከሚታሙባት የድርጅት ልሳንነት ለመውጣት ከጣሩ ብዙ፣ እጅግ ብዙ ስራ እንደሚሰሩ መገመት ይቻላል።
ኢሳት ውስጥ ቅን ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ። ውጭ ሆነው ምንጭ የሆኑ ሀገር ውስጥ ሆነው መረጃዎችን በሚገባ   ያደርሳሉ ብየ አምናለሁ። የሚያስተቿቸውን አንድአንድ ነገሮች ይቀርፋሉ ብየ አምናለሁ።
ትጥቀምም አትጥቀምም፣ ይጠቀሙበትም አይጠቀሙበትም ያኔ በክፉው ወቅት፣ ያኔ በዛ ጨለማ ዘመን የአቅማችን እንደላክናት ሁሉ ዛሬም ተመልካች ሆነን ትችት፣ ክፍተት የተባለችውን እንደምንነግራቸው ግልፅ ነው!
ያ ወንጀል ተደርጎ የነበር ኢሳት ዛሬ ወደ ሀገር ሲገባ ደስ ብሎኛል። እንኳን ደሕና መጣችሁ። እንደ መፈክራችሁ የሕዝብ አይና ጀሮ እንደምትሆኑ ተስፋ አድርጋለሁ!
Filed in: Amharic