>
5:13 pm - Friday April 18, 5952

ተአምረ ኦሮሞ ወአማራ (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም)

ተአምረ ኦሮሞ ወአማራ

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም

ፍቅሬ ቶሎሳ ራሱን ከማናቸውም የጎሣ ቆዳ ገሽልጦ ወጥቶ፤ መጨረሻውን በቅጡ ሳያውቅ ከሀረር ተነሥቶ በአሜሪካ ዞሮ ኢትዮጵያ ገባ፤ በሁለት እጆቹ ኦሮሞንና አማራን በጋማቸው ይዞ አዛመዳቸው፤ የፍቅሬ ቶሎሳ ሀሳብ፣ እምነት፣ ሕልም (አንዳንዶች ቅዠት ይሉታል፤) ገና ባልታወቀ መለኮታዊ መንገድ ዞሮ ዞሮ ለማና ዓቢይ የሚባሉ ሰዎችን ያፈራ የኢትዮጵያ መሬት ላይ አረፈ፤ የኢትዮጵያን መሬት ከሰሜን እስከደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከምዕራብ ነዘረው፤ ለማና ዓቢይ የሚባሉትን ሁለት ኢትዮጵያውያን ከአንድ መቶ ሚልዮን ሕዝብ መሀል ነቅሶ አውጥቶ አንቀረቀባቸው፤ ለማንና ዓቢይን አንቀርቅቦ አወጣና አንድ አደረጋቸው!

ዘር፣ ፖሊቲካ፣ ጥቅም፣ ሥልጣን፣ ጉልበት ወይም ሀብት አይደለም፤ እግዚአብሔር በረቂቅ ጥበቡ ፍቅሬን ከአሜሪካ ለማንና ዓቢይን እነሱ በማያውቁት መንገድ አገናኝቶ፣ እነሱ ባልገባቸው መንገድ አስማምቶ ሀሳባቸውን ከእውቀታቸው ጋር አዋኅዶ፣ እምነታቸውን ከተግባር ጋር ፈትሎ የኢተዮጵያን ሕዝብ በአዲስ ድርና ማግ እየሸመኑ ኢትዮጵያን የተስፋ አገር እያደረጉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ ትኩረቱንና ሀሳቡን ከጊዜያዊ ማሸነፍና እልልታ አሳልፎ ከፊቱ በተደነቀሩት ሁለት አቅጣጫዎች አነጻጽሮ መመልከት ያለበት ይመስለኛል፤ አንደኛው፣ በእልልታና በፉከራ እየሰከሩ መጨፈር ሲሆን፣ ሁለተኛው የወደፊቱን ችግርና መከራ፣ ምናልባት ከዚያም አልፎ የጎሣ እልቂትና የማይበርድ የዘር ጥላቻ የፈረካከሰው ማኅበረሰብ ከመፍጠር መታደግ ይሆናል፡፡

በማናቸውም ደረጃ ላይ አሁን ያሉ አመራሮች ትኩረታቸውን ከፈንጠዝያው ወደቀጣዩ መራራ ትግል ቢያዞሩት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአደጋ ከማዳንም አልፈው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሰው የመሆን ነጻነቶችና መብቶች የተከበሩባት አገርን ለመገንባት፣ በሰው ሳይሆን በሕግ ለሕግ የሚገዙባት አገር፣ ለሁሉም በእኩልነት ከተስተካከለ የኑሮ መተዳደሪያ ሥርዓት ጋር ሊገነቡ የሚችሉ ይመስላል፡፡

እንደገና ኢትዮጵያ የኮሩና የተከበሩ ሰዎች አገር እንድትሆን ከለማና ከዓቢይ ጋር ለትግል መሰለፍ ግዴታ ነው!!!

ሁሉም በአሸናፊነት እንዲኮራ የሚከፍለው ግዴታ ዛሬም ሆነ ነገ፣ በውድም ይሁን በግድ አይቀርም!!!!

ፈንጠዝያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ለሚመጣው የተሟላ ነጻነት እናቆየው!!!

Filed in: Amharic