>

‹‹የጅምላና ችርቻሮ ፖለቲካ›› (ከይኄይስ እውነቱ)

‹‹የጅምላና ችርቻሮ ፖለቲካ››

ከይኄይስ እውነቱ

ፖለቲካን በጥቅሉ ስናየው የአገር ወይም የሕዝብ አስተዳደር ጥበብ፤ ነገረ መንግሥት፤የመንግሥትን ሥልጣን ለመያዝ ወይም ተጽእኖ ለማሳደር በተደራጁ ማኅበራት የሚደረግ እንቅስቃሴ፤ በዓለም አቀፍ መስክ በሁለት አገሮች መካከል ያለ ግንኙነት፤ ሀገረ መንግሥትን እና የመንግሥትን የዕለት ተዕለት ተግባራት የሚያከናውነው መስተዳድር ጉዳይን የሚያጠና የዕውቀት ዘርፍ፤ የሚለው ፍቺ ለዚህ አስተያየት ዓላማ በቂ ይሆናል፡፡

ፖለቲካ ዕውቀትና ጥበብ እንደመሆኑ መጠን የራሳቸውን ፍላጎት ባሸነፉ፣ ስግብግብነትን በሚጠየፉ፣ ለሌሎች ቅድሚያ በሚሰጡ፣ ከመንደርተኝነት ይልቅ ትልቁን አገራዊውን ሥዕል የማየትና የማስተዋል ብቃት ባላቸው፣ ዘመንን አሻግረው መጪ ትውልዶችን በሚያስቡ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ባላቸው፣ ቅንነትን ከሞራል ልዕልና ጋር በተላበሱ ዐዋቂዎች እጅ ሲገባ፤ የሕዝብ ነፃነቶችና መብቶች፣ የሕዝብና የአገር ሉዐላዊነት፣ የግዛትና ዳር ድንበር አንድነት ተከብረው የሚታዩበት፤ እኩልነትና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት፤ ልማትና ብልጽግና የተመቻቸበት፤ የክብርና የኩራት ምንጭ በመሆን የሥልጡን ማኅበረሰብ ዓይነተኛ መለያ ይሆናል፡፡

በተቃራኒው ነገረ መንግሥት፣ ነገረ ሀገር በደናቁርት ደጓዕሌዎች÷ በመንደርተኞች÷ በመንጋ አሳቢዎች፣ ጎሣ/ነገድ በሚባል ግዑዝ ጣዖታት አምላኪዎች÷ ጭካኔን ከስግብግብነት÷ ጥላቻን ከቂመኝነት÷ ዝርፊያን ከአልጠግብ ባይነት÷ እስከ በሌለው ክፋትና ተንኮል በታጠሩ መሠሪዎች÷ ኅሊናና ልቦናቸው በታወረ ሆድ አምላኪዎች÷ ዕኩያንና ዕቡያን÷ ከሰብአዊ ፍጡርነት ወደ አውሬነት በተሸጋገሩ ‹ካልእ› ፍጥረቶች÷ ባጠቃላይ ነውርን ኹሉ ክብር ባደረጉ ጉዶች እጅ ሲወድቅ ውጤቱ የሕዝብ ተዋርዶ፤ ሥር የሰደደ ማኅበራዊ ድቀት፣ የአገር ምድራዊ ሲዖልነት÷ ሲከፋም አገርና ሀገረ መንግሥት አልባነት፣ ባጭሩ ከሥልጣኔ የተራቆተ ማኅበረሰብ ዓይነተኛ መለያ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ‹ፖለቲካ› ፖለቲካም አይሰኝ፡፡ ተራ የጅምላና ችርቻሮ ንግድ ይሆናል፡፡ ያውም ሥርዓት የሌለው÷ ማጅራት መቺዎች ወይም ጉልበተኞች የሚሠለጥኑበት የዘራፎችና ቀማኞች ‹ንግድ› ይሆናል፡፡ አገር የወንበዴዎች ዋሻ ትሆናለች፡፡ በዚህ ዓይነቱ የጅምላና ችርቻሮ ‹ፖለቲካ› የገንዘብ ተመን የሌላቸው ሕዝብና አገር እስከነ መልካም ዕሤቶቻቸው (ሃይማኖት÷ ባህል፣ ትውፊት፣ ወግና ልማድ ወዘተ.) ተራ ‹ሸቀጥ› ይሆናሉ፡፡ ይሸጣሉ ይለወጣሉ፡፡ በመሸጥና በመለወጥ ብቻ አያቆምም፡፡ ድምጥማጣቸውንም ያጠፋሉ፡፡

አለመታደል ሆኖ፣ በእኛም ጥፋት ጭምር ኢትዮጵያ አገራችን ላለፉት 27 ዓመታት ወያኔ ትግሬ (ሕወሓት) በሚባሉ (አንዳንዶች ይህን ስያሜ ለምን ትጠቀማለህ ይሉኛል፡፡ በደደቢት ጫካ ዳቦ ባይቆርሱም ለራሳቸው የሰጡት ስያሜ ነው፡፡ የታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ እስኪጣሉ በዚሁ ስም ነው የምጠራቸው) የፖለቲካ ነጋዴዎች (ፋሺስቶች) እጅ ወድቃ አበሳዋን/ቁም ስቅሏን አይታለች፡፡ አሁንም እነዚህ ርጕማን አገር ከማመስ አልታቀቡም፡፡ እነዚህ ጅምላ ነጋዴዎች እነርሱን ከሚመስሉ እንደ ኦነግ ካሉ ቡድኖች ጋር የዘር ፖለቲካን ችግኝ እያፈሉ በመላ ኢትዮጵያ በጅምላ ሲያከፋፍሉ ኖረዋል፡፡ የወያኔ የእጅ ሥራ ከሆኑት መሸጦዎች (3ቱ የጎሣ ድርጅቶች እና ‹አጋር› የተባሉትን የጎሣ ቡድኖች ጨምሮ) አንስቶ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በጎሣ ተደራጅተው (የግለሰቦች ዕውቅናና ማንነት ግምት ውስጥ ሳይገባ) የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የሚመኙ በሙሉ፤ በኅብረ ብሔራዊነት ስም (በነገራችን ላይ የጎሣ ድርጅቶች ተሰባስበው የሚፈጥሩት ‹ኅብረት› ድርጅቱን ሀገር አቀፍ አያደርገውም) አሥሬ እየተሰነጣጠቁና እንደ አሸን እየፈሉ÷ ኅብረትና የዓላማ ጽናት የሌላቸው በሙሉ፤ እና ፖለቲካን የትርፍ ጊዜ ሥራና መተዳደሪያ ያደረጉ ኹሉ የጅምላ ነጋዴዎቹ ‹ሸቀጥ› አከፋፋይ የችርቻሮ ፖለቲካ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ባጭሩ ዘርን ከፖለቲካ ጋር ያዛመዱ÷ በሕዝብ ስም የሚነግዱ÷ በብዙኀኑ ኪሣራ ፖለቲካን ለግል ጥቅም ማትረፊያ የሚያውሉ የ‹ፖለቲካ› ጅምላና ችርቻሮ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ የሚገርመው ደግሞ እነዚህ የፖለቲካ ደላላዎች ‹ንግዱን› የሚያካሂዱት ከ‹ሀብቱ› ባለቤት (ከሕዝቡ) ያልተሰጠና ዕውቅና የሌለው የሐሰት የውክልና ሥልጣን ሰነድ ይዘናል በማለት ነው፡፡ ወያኔ ትግሬ የትግራይ ነፃ አውጪ ነኝ ብሎ ራሱም ነፃ ሳይወጣ አገርን አምሶና አተራምሶ ለጊዜው ወደ ደደቢት አፈግፍጓል፡፡

እውነት ከአእምሮአችንና ከኅሊናችን ጋር ካለን የበቀለበትን ምድርና ነገድ አዋርዶና አሸማቅቆ÷ ሳይወክለው እወክለዋለሁ ብሎ÷የትግራይን ሕዝብ ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር አቃቅሮ÷ አእላፋትን ገድሎ፣ እንደ ትኋን ‹ካልጋው› ተጣብቄ ካልኖርኹ ኢትዮጵያ መበታተን አለባት ብሎ እየዛት ካለው ‹የጎሣ ሻምፒዮኑ› ወያኔ መማር አቃተን? የኦሮሞ ሕዝብ ተወካይ ነኝ በሚል ለሥልጣን ለሃጩን እያዝረበረበ ያለው የጎሣ ስብስብ የትየለሌ ነው፡፡ መንጋ ተከታይ ማፍራትና ውክልና ለየቅል መሆናቸውን መረዳት ይገባል፡፡ ከሁሉ የሚደንቀው አማርኛ ተናጋሪውን ነገድ እወክላለኹ ብሎ የተነሳው አዲሱ ምልምል ጎሠኛ ነው፡፡ ይህንንም ነገድ እንወክላለን ብለው የተነሱ ቊጥራቸው በርካታ ነው፡፡ አንዳንዶቹ በኮምፒውተር መረብ ግንኙነት ከሚደረግበት ምናባዊው ከባቢ ውጭ ህልውና ያላቸውም አይመስለኝም፡፡ በቅርቡ ተቋቋመ የሚባለው ደግሞ ብዙዎች ምስክርነታቸውን እየሰጡ እንደሚገኙት የመሸጦው በረከትና ጓዶቹ የእጅ ሥራ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ባይሆንስ ምን ለውጥ አለው? በዘረኝነት በሽታው እስከተለከፈ ድረስ፡፡ ራሱ መድኃኒት የሚሻ አካል እንዴት ለሌላው ፈውስ መሆን ይችላል? እንኳን ለኢትዮጵያ÷ ውክልናው የለውም እንጂ በድርቅና ወክዬዋለኹ ለሚለው ነገድም ረብ ያለው ነገር እንደማይፈይድ ወደፊት የምናየው ነው፡፡ ሌሎችም በጎሣ/ነገድ የተሰባሰቡ የ‹ፖለቲካ› ነጋዴ ድርጅቶች መጨረሻቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ሕዝብን ከሥልጣኔ ወደ ድንቁርና መሣብ፡፡ ወያኔ በቀደደላችሁ ቦይ እየፈሰሳችሁ እንዴት የተለየ ውጤት ለማምጣት ትጠበቃላችሁ? እውነት እንነጋገር ከተባለ መንፈሳዊነቱ ይቅርና ለጎሣ/ዘር ጣዖት ተንበርክኮ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ አማኝ ነኝ ማለት ይቻላል? እነዚህ የፖለቲካ ንግድ ውስጥ የተሠማሩ ወገኖች ባንዱ ወይም በሌላው ቤተ እምነት አባል ይመስሉኛል፡፡ እንደ ወያኔ አልቦ እግዚአብሔር ባዮች (Atheists) ከሆኑ ሥጋታችንን የበለጠ ከፍ ያደርገዋል፡፡

እነዚህ የጎሣ ቡድኖች እውነት የወገናቸው እልቂት፣ መገፋት፣ መጠቃት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ ባገሩ ባይተዋር፣ የበዪ ተመልካች መሆን የሚያንገበግባቸው ከሆነ የማኅበረሰብ ድርጅት አቋቁመው ለህልውናው ÷ለመብቱ የሚታይ የሚዳሰስ ተግባር ቢያከናውኑለት ትልቅ የትድግና ሥራ በነበር፡፡

የዘር ‹ፖለቲከኞች› ባመዛኙ በመንጋ አስተሳሰብ የሚመሩ በመሆናቸው ጅምላ አከፋፋዮቹና መሸጦ የሆኑት ቸርቻሪዎቻቸው በጅምላም ሆነ በችርቻሮ ለመግደል፣ ዘግናኝ ስቃዮችን ለመፈጸም፣ ለማፈናቀል፣ ለመዝረፍ፣ በእምነትና በጎሣ ለማጋጨት፣ ሽብር የሚነዙ የፈጠራ ወሬዎችንና የሐሰት መረጃዎችን በመደበኛና በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛዎች ለመናኘት፣ ጭፍን ተከታዮችን ለማፍራት፣ ባጠቃላይ ዕኩይ ድርጊቶችን ለመፈጸም ወደ ኋላ አይሉም፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ጅምላ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ለራሳቸውና መሸጦ ሎሌዎቻቸው ‹ትርፍ› (ሥልጣን ላይ እስካስቆየና ሥልጣንን ጥግ አድርጎ የሚገኝን ጥቅም እስካስጠበቀ ድረስ)  እስካስገኘ ድረስ የ‹ፖለቲካ ንግዱን› በማናቸውም ሕገ ወጥ መንገድ (ኮንትራባንድ፣ ‹አየር ባየር›፣ ያለ ግብርና ቀረጥ ክፍያ፣ ያለ መያዣ በሚሰጥ የመንግሥት ባንኮች ብድር፣ ‹የተበላሸ› በሚል በሚሠረዝ ዕዳ፣ ባርኔጣን እየቀያየሩ ‹መንግሥትም ፓርቲም› በመሆን፣ ሠርተው ለፍተው ራሳቸውንና ወገናቸውን ለመጥቀም የሚፈልጉ ዜጎችን ከማናቸውም የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ውጪ በማድረግና በጎሣ የተደራጀ የንግድ ሞኖፖሊ በመፍጠር ወዘተ.) ያካሂዳሉ፡፡ ሲያካሂዱም ቆይተዋል፡፡ አሁንም ቀጥሏል፡፡

‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ› በሚባል ማጭበርበሪያ መንግሥተ ሕዝብ ወደሰፈነበት ሥርዓት መድረስ እንደማይቻል ኹሉ፤ በመርዛማው የጎሣ/ዘረኝነት መንገድ በፍጹም ወደ ኢትዮጵያዊነት መድረስ አይቻልም፡፡ የዘር ፖለቲካ ከሰውነት ስለሚያዋርድ መጫረሻው መንደርተኝነት፣ ሲከፋ ደግሞ ፋሽሲትነትን ያስከትላል፡፡

ወያኔ ትግሬ አገርን በመንደር ቀይሮ ራሱ ኮስሶ አገራችንን አኮሰሳት፤ ሕዝብን (ለመናገርና መጻፍ በሚከብደኝ) ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› በሚል ትርጕም አልባ የቃላት ኳኳታ ተክቶ ኢትዮጵያን ባለቤት አልባ አደረጋት፡፡

የፖለቲካ ንግድ ላይ የተሠማራችሁ ወገኖች አሁንም ለበጎ እስከሆነ ድረስ ጊዜው አይረፍድምና ወደ ኅሊናችሁ ወደ አእምሮአችሁ ተመለሱ፡፡ ዝንባሌአችሁ ፖለቲካ ከሆነ የጨዋታውን ሕግ አክብራችሁ በዜግነት ፖለቲካ በኢትዮጵያ መልክዐ ምድር ኹሉ ቧርቁበት፡፡ በስብስባችሁ ዘር ቆጠራ ቦታ እንዳይኖረው ተግታችሁ ሥሩ፡፡ የአባልነት መለኪያው ኢትዮጵያዊ ዜግነት÷ የአገርና የወገን ፍቅር÷ ችሎታ÷ ብቃት÷ ቅንነትና የሞራል ልዕልና ወዘተ ቢሆን፡፡ ላገር ለወገን ይበጃል የምትሉትን በዕውቀት÷ በጥበብ÷ በልምድ የዘለበ ፖሊሲያችሁን፣ ርዕዮታችሁን፣ ሃሳባችሁን፣ እምነታችሁን፣ አመለካከታችሁን በሕዝብ አደባባይ ገበያ ለ‹ሽያጭ› አቅርቡት፡፡ ምርጫውን ለሕዝቡ ተዉለት፡፡

ሰው በጠፋበት ዘመን ሰው የማያጣ÷ በቀቢፀ ተስፋ ለነበሩ ተስፋ የሚሆን÷ በጨለማ ድንቁርና ለኖሩ ብርሃን ዕውቀትን የሚገልጥ የኢትዮጵያ አምላክ በወንድሞቻችን በእነ ዐቢይና ለማ አማካይነት የትድግና ሥራውን ጀምሯል፡፡ አገር በማረጋጋቱም ሆነ ወደ ዴሞክራሲ በማሸጋገሩ ረገድ የኹላችንም ትርጕም ያለው እገዛ ያስፈልጋቸዋል፡፡

መጪውን ዘመን፤ ዘመነ ሰላም ወፍቅር÷ ዘመነ ፍሥሓ ወሐሴት ያድርግልን፡፡ ለነፃነት ÷ ለፍትሕ÷ ለእኩልነት÷ ለሕግ የበላይነት÷ ለመንግሥተ ሕዝብ÷ ባጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህልውናና አንድነት ውድ ሕይወታቸውን የሰጡ ወገኖቻችንን በሙሉ እግዚአብሔር አምላክ ነፍሳቸውን በመካነ ዕረፍት ያኑርልን፡፡ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይስጥልን፡፡

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ መልካም ርእሰ ዓውደ ዓመት እመኝላችኋለሁ፡፡

Filed in: Amharic