ፕሮፌሰር በየነ የባዮሎጂ ምሁር ናቸው ። አሜሪካ ከሚገኙ ቱሌን እና ዊስኮንሲን ዩኒቨርስቲዎች የባዮሎጂ ዲግሪዎቻቸውን ከሰሩ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለበርካታ አመታት አስተምረዋል ፤ ለትንሽ ጊዜም ምክትል የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል (በወቅቱ ሚኒስትር የነበረችው ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ነበረች መሰለኝ)
ምሁሩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተቃዋሚው ጎራ ውስጥ ሆነው ላለፉት 27 አመታት ተስፋ ሳይቆርጡ ታግለዋል ። ሰውዬው ህወሃት/ኢህአዴግ የሃገሪቱን ስልጣን ከያዘ ጊዜ አንስቶ የሃዲያን ህዝብ በመወከል የፖለቲካ ድርጅት አቋቁመው በኋላም መድረክን ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በጋራ በመመስረት ግፈኛውን የወያኔ ስርዓት ያቅማቸውን ያህል ታግለዋል ። ያቅማቸውን የሚለው ይሰመርበት ። የፓርላማ አባል በነበሩበት አመታትም ወያኔ በማንኪያ ሰፍሮ በሚሰጣቸው ጥቂት ደቂቃዎች ማለት የሚፈልጉትን ቁጭ ቁጭ ማድረግ ሲሳናቸው አይተናል ፤ መናገር የሚፈልጉትን ነገር ቶሎ ቶሎ በመናገር ፋንታ ኧኧኧኧኧ እያሉ ሲጎተቱና ማስታወሻዎቻቸውን ሲያገላብጡ “የተከበሩ ዶ/ር በየነ ሰዓቶን ጨርሰዋል” ተብለው ማይካቸውን አፈጉባዬው ከመድረክ ሆኖ ያጠፋባቸዋል ። ሰውዬው ማይክ ሳይጠፋባቸውና አፈጉባዬው ሳያስቆማቸው ንግግራቸውን የቋጩበት ጊዜ አይቼ አላውቅም ። ሰወዬው ድምፃቸው አሰልቺ monotonous ነው ።
ፕሮፌሰር በየነ ለወያኔ ስጋት ሆነው አያውቁም ። ሰውዬው ለዘብተኛ “ተቃዋሚ” ናቸው ። እኔን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን ህወሃት በየነ ፔጥሮስን እንደ ለማዳ የህወሃት/ኢህአዴግ ግብር አድማቂ እንጂ እንደተቃዋሚ አይቷቸው አያውቅም ብለን እናምናለን ። ለዚህም ነው ወያኔ አስሯቸው የማያውቀው ። ለብዙ አመታት የወያኔ የይስሙላ ተቃዋሚ ምልክት ሆነው “በሃገሪቱ ላይ ዴሞክራሲ አለ” ለሚል የህዝብ ግንኙነት ፍጆታ (ፕሮፓጋንዳ) መንግስት ቲቪ ላይ እያቀረባቸው ተጠቅሞባቸዋል ። ሰውዬው የመከራ ዘመናችንንም አስረዝመውብናል ።
በየነ ፕጥሮስ በሆነ ጉዳይ ላይ ነገር ሲጋጋል አስተያየት እንዲሰጡ የኢቲቪ ጋዜጠኞች ካሜራና ማይክ ይዘው ያሉበት ድረስ ይመጡና ኢንተርቪዉ ያደርጓቸውና ፕሮፓጋንዳ ይሰሩባቸዋል ፤ በተጋጋለ የፖለቲካ ትግል ላይ ሳይታወቃቸው ቀዝቃዛ ውሃ እንዲቸልሱ ያደርጓቸዋል ። በአንድ ወቅት ስለሩዝ የተናገሩትን ኢቲቪ እየደጋገመ እያቀረበ የህዝብ መሳቂያ አድርጓቸዋል ። ምን ያህል እውነት እንደሆነ ባላውቅም በአንድ ወቅት “ከታቃውሞ ፖለቲካ እራሶን ያግልሉና የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት እናድርግዎ ” ብለው ወያኔዎች ጠይቀዋቸው “እስኪ ላስብበት” ብለዋል እየተባለ ሲወራ ነበር ።
በቀደም አንድ ጋዜጠኛ ኢቲቪ ስቱዲዮ ውስጥ አስቀምጦ የ 7 ሰዓት ዜና ላይ ስለ ኢትዮ ኤርትራ እርቅና የአቶ ኢሳያስ ጉብኝት በተመለከተ አስተያየታቸውን ሲጠይቃቸው “…… እርቁ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሆኑ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል ፤ ለምሳሌ ስለ እስረኞች ልውውጥ ምንም የተባለ ነገር የለም” እያሉ ሲልጎመጎሙ ነበር ። በዛብህ ፔጥሮስ የሚባል ወንድማቸው የአየር ሃይል ጀት አብራሪ ሲሆን ሻቢያ ሁለት ጊዜ ጀቱን እያጋየ እሱን ማርኮታል (አንዱ ደርግ ሻቢያን ሲደበደብ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ የተማረከው ደግሞ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ነው) ። ታዲያ በየነ ፔጥሮስ ” ስለ እስረኛ ልውውጥ ያለምንም ስምምነት እንዴት እርቅ ይካሄዳል ?” የሚሉት ስለ ወንድማቸው ማንሳታቸው ነው ። “ወንድሜ በዛብህ ኤርትራ ውስጥ እስር ላይ ነው ፤ እሱ ሳይፈታ እንዴት ሁለቱ ሃገሮች ይታረቃሉ ?” ብለው እቅጩን መናገር ፈርተው ዙሪያ ጥምጥም ይጥመለመላሉ ።
ከአንድ ከሳምንት በፊት ደግሞ “በአሁኑ ወቅት እዛም እዛም የሚነሱትን ግጭቶች የሚያስነሱት ኢህአዴግ ያሰማራቸው ካድሬዎች ናቸው” ሲሉ ነበር ። ወያኔ ነው ማለት ፈርተው እኮ ነው ። እንግዲህ ሰውዬው ሁሌም እንዲህ ናቸው ። እርምጥምጥ ። ጠንካራ መሬት ይዘው መቆም የማይፈልጉ ፥ ተቃውሞን እንደ ስራ መስክ የያዙ ፥ ቴሌቪዥን ላይ መቅረብ ብርቃቸው የሆነ ፥ እስር የሚፈሩ ፥ ይሄን ሁሉ አመት ተተኪ ያላፈሩ ተመላላሽ ደካማ ፖለቲከኛ ናቸው ።
ሰውዬው ብሎግ አያደርጉም ። ጋዜጣ ላይ እርሳቸው የፃፉትን ፅሑፍ አንብቤም አላውቅም (አንድ ሁለት መፅሐፍት ጽፈዋል ሲባል የሰማሁ ግን ይመስለኛል ) ። ለአመታት “የዲሞክራሲ ምህዳሩ ጠቧል” ሲሉ የነበሩ ሰውዬ ዛሬ ሁሉም አዳራሽና ስታዲየም ላይ ህዝብ ጠርቶ ማወያየት ሲፈቀድለት እርሳቸው የሉም ። ሰውዬው የባዮሎጂ እድሜያቸው 68 ቢሆንም የፖለቲካ እድሜያቸው ግን እንደነ አቦይ ስብሃት ነጋ ጃጅቷል !!
በየነ በ digital ዘመን analogue ላይ ደርቀው ቀርተዋል ።
ስለዚህ ፕሮፌሰር በየነ ሆይ ሃገር መጫወቻ አይደለምና ከይቅርታ ጋር የእርሶ ፖለቲካ ከዚህ በኋላ ቦታ የሌለውና አርጅቶ የጃጀ ስለሆነ እባክዎ በቃዎት ፤ ለአዲሱ ትውልድ መድረኩንም መድረክንም ይልቀቁ ። አልቻሉበትም ። እስከዛሬ ላደረጉት ሁሉ እናመሰግናለን ።
” Say goodbye and Never show up again” የሚለውን country ዘፈን ጋበዝኮት ።
ግልባጭ : ለአቶ አየለ ጫሚሶ