>
5:18 pm - Monday June 15, 3795

የኢትዮጵያውያን የጋራ ጥምረትና አንድነት ሀገራዊ ብሔራዊ ስትራቴጂ (እና ፖሊሲ) አስፈላጊነት ! (አሰፋ ሀይሉ)

የኢትዮጵያውያን የጋራ ጥምረትና አንድነት ሀገራዊ ብሔራዊ ስትራቴጂ (እና ፖሊሲ) አስፈላጊነት !
አሰፋ ሀይሉ
The need for a NATIONAL SOLIDARITY STRATEGY (&POLICY) !
የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይን ጨምሮ – በአሁኑ ወቅት – በርካታ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ መንግሥታዊና ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የብዙሃን መገናኛዎች፣ እና በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ ኃላፊነት የሚሰማቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ – በማናቸውም ሥፍራ የሚገኝ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ – በአንድነት፣ በኅብረት፣ እጅ ለእጅ ተጣምሮ – ሁሉም ያለውን የሚችለውን ሁሉ አበርክቶ የሚያልፍበት ታላቅ አጀንዳ ነው የማነሳው አሁን፡፡
ማናቸውም – ኢትዮጵያዊ የሆነ ዜጋ ሁሉ – ክልል ከክልል ሳይለይ – ብሔር ከብሔር ሳይለይ – ሰሜን ከደቡብ፣ ምስራቅ ከምዕራብ ሣይለይ – ሐይማኖትና ጎሣ ሣይለይ – ሁሉም ኢትዮጵያዊ – ሌላውን ኢትዮጵያዊ – እንደወገን ተሰምቶት –  እንደ አንዲት ሀገር ዜጋነት የአንዲት የጋራ ሀገር አብሮ ኗሪዎች፣ አብሮ ሟቾች ነን የሚል ልባዊ ወገናዊ ስሜት ተሰምቶት – ሁላችንም አሁን ያለነው ትውልዶች – የነገ ትውልዶቻችንን መፃዔ ዕጣ ፈንታ በእጆቻችን መዳፍ የያዝን – በትከሻችን የተሸከምን – ከባድ አደራን የተሸከምን የአሁን ትውልድ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ነን በሚል ስሜት ሁሉም እንደዜጋ ያለበትን ኃላፊነት ተገንዝቦ – ኢትዮጵያውያን ሁሉ – ሌሎችን ወገኖቻቸው የሆኑ ኢትዮጵያውያንን – ካሉበት የኑሮ፣ የዕድገት፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የፍትህ፣ የዲሞክራሲ፣ የህልውና፣ እና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማውጣት – ሁሉም እንደሀገር ልጅ – በአንድ ኢትዮጵያዊነት ስሜት – ሁሉም – ከያለበት የሀገር ጥግ – እና የዓለም ጥግ – ሁሉም ኢትዮጵያዊ – የሌላው ጉዳይ የኔ ጉዳይ ነው ብሎ – የእርሱ ነገር እኔን ያገባኛል ብሎ – ለጋራ ሀገራዊ ራዕይ – እንዲነሣ ስለሚያስችል ታላቅ ሀገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነው አሁን የምናነሳው፡፡
በየትኛውም ሥፍራ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ – በሌላው ሥፍራ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ – የእርሱ መሶብ የእኔ መሶብ ነው ብሎ – የእርሱ ጎጆ የእኔን ጎጆ ይመስላል ብሎ – የእርሱ ልጅ ችግር የእኔም ልጅ ችግር ነው ብሎ – ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት፣ በኅብረት ሆ ብሎ ለጋራ ዕድገት በጋራ በመነሣት – ወገን ከወገኑ ጋር አብሮነቱን የሚያጎላበት – አንድነቱን የሚያጎለብትበት – ትውልዱን ለታላቅ ሀገራዊ እና አህጉራዊ ብሎም ዓለማዊ ዓላማ የሚያበለጽግበት – ከልዩነቶች ባሻገር – ወይም በልዩነቶች ውስጥ – ያለውን ታላቅ ሀገራዊ አንድነት በትውልድ አዕምሮ ውስጥ ሊፈጥር ስለሚችል – አንድ ወጥ ሀገራዊ የወገናዊ መተሳሰብን ማጎልበቻ ስትራቴጂ አስፈላጊነት ነው የምናነሳው አሁን፡፡
ያ በሀገር ደረጃ የሚጸድቅ ብሔራዊ የዜጎች መግባባትና ሀገራዊ አንድነት ማበልጸጊያ ስትራቴጂ – ተከታታይነት ያለው – የታቀደ – ዘርፈ ብዙ የሀገር ሽማግሌዎችን – የሀገሪቱን ምሁራን – የሐይማኖት አባቶችን – ትምህርት ቤቶችን – ሀገራዊ ስታንዳርድ አውጪዎችን – የባህልና ስነጥበባት ባለሙያዎችን – በመገናኛ ብዙሃንና በማስታወቂያ ኢንዱስትሪ ያሉ ባለሙያዎችን – በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ያሉ ከያኒዎችን – ክልል ተሻጋሪ የሆኑ ምርቶችን ለዜጎች የሚያሰራጩ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን – ሀገራዊ ሽፋን ያላቸውን እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉ መንግሥታዊ ያልሆኑ የሀገር ውስጥና የዓለማቀፍ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶችን – እንዲሁም መምህራንን – ጸሐፍትን – የመንግሥት ባለሥልጣናትን – ተሰሚነት ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ የሚያጠቃልል – አንድ ወጥ የሆነ – ብሔራዊ የኢትዮጵያውያን ጥምረት ፖሊሲ ነው የሚሆነው፡፡ እና ደግሞ – ያንኑ የተንተራሰ – በፌዴራል ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት – ከላይ ከተጠቀሱት የህብረተሰብ ክፍሎችና መሠል ተቋማት የሚዋቀር – እና ዘርፈ-ብዙ ጉዳዮችን አካትቶ የሚረቀቅ – አንድ ወጥ ስለሆነ – የኢትዮጵያውያን ዜጎች ጥምረት ሀገራዊ ስትራቴጂ አስፈላጊነት ነው – አሁን የምናወራው፡፡ እና ያ እጅግ እጅግ እጅግ ወቅታዊ፣ አንገብጋቢ፣ እና እጅግ ተፈላጊና አስፈላጊ ጉዳይ ነው – ነው እያልኩ ያለሁት፡፡
ይህን ዓይነቱ ራሱን የቻለ – የራሱ የአጭር ጊዜና የረዥም ጊዜ ዕቅዶችና ስትራቴጂዎችን ነድፎ የሚይዝ – እና በብሔራዊ ደረጃ ሁሉንም የሚመለከተውን አካል ሁሉ የሚያሣትፍ – አንድ በብሔራዊ ደረጃ የሚጸድቅ ታላቅ ሀገራዊ ስትራቴጂ መኖር – በአሁን ወቅት – በግለሰቦች ደረጃ – በበጎ ፈቃደኛ ዜጎች ደረጃ – እና በመሪዎች ደረጃና ጥረት ብቻ ተወስኖ የሚቀረውን – ታላቅ ሀገራዊ ሰብዕናንና አብሮነትን፣ ታላቅ የጋራ ሀገራዊ ራዕይና ወገናዊነትን ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን በጎ ጥረት – በተደራጀና በበሠለ፣ ሣይንሳዊ በሆነ – እና በእቅድና በበጀት በሚመራ – ተጠሪነትና ክትትል ባለው – እንደ ትምህርት ካሪኩለም ቀረጻ ባለ መልኩ በወገንና በትውልድ ላይ አነጣጥሮ እንዲሠራ የሚያስችለው  ተቋማዊ አቅምና ቁመና መስጠት – ይህን አሁን እየተደረገ ያለውን ጥረት – ወደታላቅና ተጨባጭ – ወጥነት ያለው – ዘመንን የሚሻገር – የኢትዮጵያውያን የጋራ ወገናዊነትን ለመፍጠር – ምቹ ሁኔታዎችን የሚያመቻች – ታላቅ ዘመን-ተሻጋሪ – ግለሰቦችን-ተሻጋሪ – ብሔርን-ተሻጋሪ – ትውልድን-ተሻጋሪ ፋይዳ እና አበርክቶት እና ታላቅ ሀገራዊ ውጤት እንዲኖረው ያግዛል! ያስችላልም!!
ለምሣሌ እንደእነ ሜክሲኮ በመሣሠሉትና – የተለያዩ ዓይነት ዜጎች በሞሉባቸው – የዜጎች የኑሮ ልዩነት እጅግ በተራራቀባቸው – አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ ደግሞ ከብዙ የማንነትና የአስተሳሰብ የባህል ልዩነቶቹ ባሻገር – በብዙ ተመሣሣይ መፍትሄን በሚፈልጉ – ተመሣሣይ ችግሮች ውስጥ የሚገኝ ወጣትና ድህነት ያጠቃው ማህበረሰብን በያዙ ሀገሮች ውስጥ – ይህን መሠሉ – ሀገራዊ National Solidarity Strategy – የአብዛኛውን ሕዝብ ተመሣሣይ ችግሮች – እንደየሁኔታው ተጨባጭ የሆኑ ሀገራዊ መፍትሄዎችን በማምጣት – እና እነዚያን በተመሣሣይ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን ወጣቶችና ዜጎች ሁሉ – በአንድ ላይ በማሰባሰብ – ታላቅ ሀገራዊ የጋራ ዓላማ እንዲኖራቸውና – አዲስ ሀገራዊ ወገናዊ አብሮነትን ያነገቡ – የታችኛው ማህበረሰብ ክፍሎች እንዲያቆጠቁጡ በማድረግ – በብዙ መልኩ – በልዩነቶች የተነሣ የሚመጡትን ግጭቶች – እና እነዚያን ተከትሎ የሚመጡትን የዲሞክራሲ እጦቶች፣ የዜጎች ፍላጎት ያለመሰማት፣ እንዲሁም የሙስናና የሌሎች መብቶችን መነፈጎችን በከፍተኛ ሁኔታ ከዜጎች ጫንቃ ላይ ለመቀነስ – ታላቅ የዜጎች ሀገራዊ የጋራ ግንባር በመፍጠር – ታላቅ በጎ ፋይዳን፣ አንድነትን፣ ኅብረትን፣ እና ለጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ  – ሁሉም ዜጋ በአንድነት የሚቆምበትን – ሀገራዊ መግባባት እንዳመጣ – ብዙ በጉዳዩ ላይ መጻሕፍትን የጻፉ የላቲንና የኤዥያ ምሁራንን ሥራዎች ከነስታቲስቲክሳቸው አይቶ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ስለሆነም – በበኩሌ – በአሁን እጅግ ልዩነቶች ሰፍተው – ለአሉታዊ የጎንዮሽ ውጤቶች እየዳረጉን ባሉበት በአሁን ሰዓት – እና ወደፊት የሚመጣው ትውልዳችን የአንዱ ነገር የእኔም ነገር ነው – ያንን እኔ ጠንቅቄ አውቀዋለሁ – ያም እኔን አበክሮ ያውቀኛል – የሚሉ – ሀገራዊ ራዕዮችን ሰንቆ – አንዱ ያንዱን ችግር ለመፍታት – በጋራ ሀገራዊ ራዕይን ይዞ – ዜጋ ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለጋራ ብልጽግና በህብረት የሚቆምበትን፣ እና በጋራ ታላቅ ተስፋ የሚጓዝበትን  ሀገራዊ ዘዴዎች ፍኖተ ካርታ የያዘ – ምናልባትም ተጠሪነቱ – ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት – አሊያም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ – አሊያም ለፕሬዚደንቱም ሆነ ለሌሎች አቅም ያላቸው ህዝባዊ፣ ሀገራዊ ተቋማት እንዲሆን ሆኖ የሚቋቋምና  – ከላይ በመነሻዬ ላይ የጠቀስኳቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ የሚያሳትፍ – ይህችን ሀገርንና ትውልድን ለወደፊት በአስተማማኝ ወገናዊ የጋራ መሠረት ላይ ሊገነባ የሚችል  – ታላቅ የሀገራዊ ጥምረት ወይ የሀገራዊ መተሳሰብ ብሔራዊ ስትራቴጂና ፖሊሲ – በፌዴራል መንግሥቱና በክልሎችም ምክክርና ይሁንታ ተዋቅሮ – በአፋጣኝ በሥራ ላይ እንዲውል ቢደረግ ተግባራዊ ሀገራዊ ፋይዳው – እጅግ እጅግ ማናችንም አሁን ላይ ሆነን ከምንገምተው በላይ የሆነን – ታላቅ ኢትዮጵያዊ ትውልድን የምናፈራበት ተግባር እንደሚሆን – መልዕክቴን ለሚሰማ ለማንኛውም ሀገር-ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ – መልዕክቴን አበክሬ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡
በዚህ ሀገራዊ የጥምረትና የመተሳሰብ ጉዳይ ላይ – በየትኛውም የዓለም ሥፍራ ተበትነው ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ – እነርሱንም እና ልጆቻቸውን ሁሉ ያካተተ – ታላቅ ሀገራዊ ስትራቴጂና ፖሊሲ እንደሚመጣልን እጅግ የለመለመ ተስፋ አለኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ – ማናቸውም ሀገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊና – ብዙ ሃሳብን ሊያመነጩ የሚችሉ በርካታ ዕውቀቱ፣ ፍላጎቱና ሙያው ዝንባሌው እንዲሁም ለጉዳዮቹ ቅርበቱ ያላቸው ዜጎች ሁሉ – የበኩላቸውን ሃሳብ ቢሰጡበት – ጉዳዩ በቀጥታ ወደሚመለከተው – እና ራሱም በግሉ ለዚሁ ተመሣሣይ ራዕይን ሰንቆ በቻለው አቅም ሁሉ የበኩሉን ለማድረግ ሲተጋ ወደማየው – ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ – ይሄ መልዕክት እንዲደርስ ማድረግ የምንችለውን ሁሉ – ማድረግ የሚችሉ – ቢያግዙን – ውጤቱ የጋራ – ውጤቱ የትውልድ – ውጤቱ የወገን የሀገር ነውና – ለሚችሉ ሁሉ – የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ የበዛ ልመናዬን በትህትና ዝቅ ብዬ  አቀርባለሁ፡፡ ለሁሉም በዚህ ጉዳይ ለሚደረገው ወገናዊ ጥረት ሁሉ ደግሞ – እነሆ አስቀድሜ – ከመቀመጫዬ ብድግ ብዬ – በአክብሮት እጅ እነሳለሁ፡፡
አምላክ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልዶቻቸውን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ፡፡ የብዙሃን እናት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ አሜን፡፡
Filed in: Amharic