>

ህወሀቶቹ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆችን ብቻ እየለዩ በላባቸው የገዙትን ትጥቅ እየቀሙ ነው" (ጌታቸው ሽፈራው)

ህወሀቶቹ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆችን ብቻ እየለዩ በላባቸው የገዙትን ትጥቅ እየቀሙ ነው”

ጌታቸው ሽፈራው

* የወልቃይት ጠገዴ  ሕዝብ ወኪሎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የላኩትን የአቤቱታ ደብዳቤ ይመልከቱ
 
~”በቅርቡ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆችን ሙሉ በሙሉ ከትውልድ ቦታቸው ለማስለቀቅ እቅድ መያዙን ለጦርነት እየተዘጋጀ ያለ መሆኑን በሚደረጉት ሥራዎች አረጋግጠናል”
ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ/ም
ለክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚንስትር
 አዲስ አበባ
አመልካቾች የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በወኪሎቻቸው አማካኝነት
ጉዳዩ፡- እየደረሰብን ያለ ግፍና በደል በአስቸኳይ እንዲቆምልን ስለመጠየቅ
እኛ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ድርጅት (ሕወሐት) ከ40 ዓመታት በላይ እየደረሰብን ያለውን ግፍና በደል እንዲሁም የዘር ማጥፋት እና ማፅዳት ተግባር እንዲቆምልን እኛም ከሕግ ውጭ ተገድደን የተጣለብን ማንነት ተነስቶ ከዘር ከትውልዳችን ይዘነው የቆየነው የተነጠቀው የአማራ ማንነታችን እንዲመለስልን በየጊዜው ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እና ለፖለቲካ ድርጅቶች ስናቀርብ ብንቆይም ምላሽ የሚሰጠን አላገኘንም፡፡ በተለይ ደግሞ ግንቦት 8 ቀን 2010 ዓ/ም ለከቡርነትዎ በአድራሻ በፃፍነው ማመልከቻ በርካታ ማስረጃዎችን አባሪ በማድረግ ለጽ/ቤትዎ በላክነው ደብዳቤ ገልፀናል፤ ስለመድረሱም በፖስታ ቤት በኩል አረጋግጠናል፡፡
ይሁን እንጅ አቤቱታችን አሁንም በእርስዎ በኩል ምላሽ ባለማግኘቱ እስከ አሁን ድረስ በወልቃይት ጠቀዴ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍ ካለመቆሙ በላይ አሁን በዚህ ሳምንት የበለጠ ተጠናክሮ በመቀጠል ከዚህ የሚከተሉት በደሎች ተፈፅመውብናል፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከአባቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የቆየንን ባህል በመከተል ከነሐሴ 1 ቀን እስከ 16 ቀን ለሚደረገው የፍልሰታ ፆም ማጠናቀቂያ ከነሐሴ 16 እስከ 18 ቀን ድረስ ‹‹አድርሽኝ›› የሚባል የአካባቢው ማህበረሰብ በየቅርበቱ ተገናኝቶ በአንድነት የሚጫወትበት እና ማህበራዊ እና ባህላዊ አንድነቱን የሚገልፅበት ቀን ነው፡፡
 በዚህ በቆየ ባህሉ መሠረት ነሐሴ 17 ቀን 2010 ዓ/ም አዲረመጥ ከተማ በየዓመቱ የተለመደውን ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ጭዋታቸውን በመጫወት ላይ እንዳሉ ‹‹በአማርኛ ዘፍናችኋል›› በሚል የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ከዚህ በታች ስማቸው የተዘረዘረውን ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ በመደብደብ በእሥር ቤት አጉረው እያሰቃዩአቸው የሚገኙ ሲሆን በ1ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሰው ሰው ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበት በጎንደር ሆስፒታል በሕክምና ላይ ይገኛል፡፡ በሕይዎት ስለመቆየቱ ወደፊት የሚታይ ነው፡፡
 1ኛ ካሣሁን ተወልደ በከፍተኛ ሁኔታ ተደብድቦ ሆስፒታል ያለ
 2ኛ ሙላው አቸነፈ
  3ኛ ዳዊት ባየ
 4ኛ ልዑል አለማው
5ኛ ይለፍ ተስፋየ
 6ኛ ሙላው የሽወንድም
 7ኛ ግደይ ፋንታ
 8ኛ ወንጌል ካሣ
9ኛ አለሙ ይደግ
10ኛ ዓለሙ ንጉሤ
11ኛ ኤርምያስ ልኡል
  12ኛ ልኡል ከሣ
13ኛ ገዛኸኝ ጌታቸው
  14ኛ የሐነስ ተፈራ
15ኛ ህጻን መብራቴ
 16ኛ አባ ለምለሙ
17ኛ አማኑኤል ተወልደመድኅን
18ኛ ይደግ አለባቸው
 19ኛ ወገሾ ተወልደ ብርሃን
ከላይ የተዘረዘሩት ሰዎች አድርሽኝ እየጠጡ ከሚጫወቱበት በአማርኛ ዘፍናቸኋል በሚል ምክንያት ብቻ ሲሆን ሌሎችም ለውጡን ደግፋችኋል፣ የዶ/ር ዐቢይ ምስል ያለበት ቲሸርት ለብሣችኋል በሚል በበርካታ ፖሊስ ጣቢያዎች ታሥረዋል፣ ተደብድበዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የማንነት ጥያቄ በመጠየቃቸው ምክንያት የአሸባሪነት ስም ተሰጥቷቸው በፌደራል ፖሊስ የድብደባ ማዕከል (ማዕከላዊ) በሚባለው ለ4 ወራት በከፍተኛ ስቃይ ከቆዩ በኋላ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው በመከታተል ላይ እንዳሉ መንግሥትዎ በወሰደው የለውጥ ርምጃ ከዚህ ከፌደራል እሥር ቤት ተፈትተው ቢሄዱም ወደትውልድ ቦታቸው የሄዱት በሁመራ እና በዳንሻ እየታሠሩ ሲሆን ቀድመው የሄዱት መታሠራቸውን ሲሰሙ አብዛኛዎቹ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጎንደር ከተማ በከፍተኛ ችግር እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ተፈትተው ከሄዱ በኋላ በሁመራ ከታሠሩት መካከል አቶ ማማየ አየልኝን በምሣሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል በወልቃይት ጠገዴ የሕዝብ አኗኗር ሥርዓት አካባቢው ቆላማ እና ጫካ ከመሆኑ አንፃር ራሱን ከሽፍታ ለመከላከል እና ንብረቶቹን ከአዳኝ አውሬዎች ለመከላከል ሲባል ነዋሪው በራሱ ሀብት ቀላል የጦር መሣሪያዎችን (ከምንሽር እስከ ከላሽ ኮፕ ጠመንጃ ድረስ) እየገዛ ራሱን ይጠብቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የትግራይ ክልል መንግሥት የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆችን ብቻ እየለየ በሀብታቸው የገዙትን ትጥቅ እየቀማ ለትግራይ ተወላጆች በማስታጠቅ ላይ ሲሆን በተጨማሪም ሚሊሻ ወታደሮችን በመመልመል እያሰለጠነ እና ከፍተኛ የጦር መሣሪያ እያስታጠቀ እንዲሁም የውጊያ ምሽጎችን እያዘጋጀ ስለሆነ በቅርቡ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆችን ሙሉ በሙሉ ከትውልድ ቦታቸው ለማስለቀቅ እቅድ መያዙን ለጦርነት እየተዘጋጀ ያለ መሆኑን በሚደረጉት ሥራዎች አረጋግጠናል፡፡
ስለዚህ መንግሥትዎ ስለፍቅር አጥብቆ ቢታገልም በወልቃይት ጠገዴ ሕዝቦች ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍ ግን ከቀን ወደቀን እጅግ እየከበደ ስለመጣ በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠን፤ ታሥረው በስቃይ ላይ ያሉት ሁሉም በአስቸኳይ እንዲፈቱ ለትግራይ ክልል መንግሥት መመሪያ እንዲሰጥልን፤ ፌደራል መንግሥቱን ያወቀሩት ክልሎች ከሕግ በላይ ሆነው ሕገመንግሥቱን በመጣስ መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶችን ሲጥሱ የፌደራሉ መንግሥት በዝምታ የሚመለከት ከሆነ ግን የተፈለገውን ሰላም ሊያስገኝ ስለማይችል በሁሉም የወልቃይት ጠገዴ ከተሞች የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት እንዲመደብልን እና ዘራችን ከመጥፋት እንዲታደግልን በአፅንዖት እንጠይቃለን፡፡ ቅጅ የተደረገላችሁ የሚዲያ ተቋማት እየደረሰብን ያለውን ግፍ ለዓለም ሕዝብ እንድታሣውቁልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
ግልባጭ:_
~ለኢትዮጵያ ብሮስድካስቲን ኮርፖሬሽን (የኢትዮጵያ ተሌቪዥን)
    ~  ለዋልታ ኢንፎርሜሽን
  ~ለአልጀዚራ ቴሌቪዥን የአማርኛው ክፍል
   ~   ለብሪቲሽ ብሮድካስቲን ኮርፖሬሽን (ቢቢሲ) አማርኛው ክፍል
    ~  ለቮይስ ኦፍ አሜሪካ (ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ)
   ~   ለጀርመን ድምፅ ራዲዮ
        አዲስ አበባ
     ~ለአማራ ብዙሐን መገናኛ ድርጅት (የአማራ ክልል ቴሌቪዥን እና ራዲዮ) ክፍል
            ባህርዳር
Filed in: Amharic