>
5:18 pm - Monday June 15, 4972

ሸራፋ ነጻነት የለም! (በፍቃዱ ኃይሉ)

ሸራፋ ነጻነት የለም!
 
በፍቃዱ ኃይሉ  
 
 
ልክ የዛሬ ሁለት ዓመት የተጋጋሉትን አመፆች ለማስቆም መፍትሔው ምንድን ነው ብዬ የጻፍኩት ጽሑፍ አብዛኛው መልስ አግኝቷል/እያገኘ ነው። በወቅቱ ይህ ይሆናል ተብሎ ካለመታሰቡ የተነሳ “ኢሕአዴግን አታውቀውም ነበር ማለት ነው” የሚሉ ኮሜንቶች ይገጥሙኝ ነበር። 
“መፍትሔው ምንድር ነው?”
ሰሞኑን የተለያዩ  ወዳጆች ‘ታግ’ እያደረጉኝ ለኢትዮጵያውያን አመፅ መፍትሔ ሲጠቁሙ ነበር። አብዛኞቹ ሕወሓት ጥገናዊ ለውጥ (maintenance/cosmetic change) እንዲያመጣ የሚጠይቁ ዓይነት ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ሕወሓት ላይ የኦሮሞ እና የአማራ ተወላጆች በማበራቸው ምክንያት ሁለቱን ግዙፍ ባለድርሻዎች የማጋጨት ሸፍጥ ያዘሉ እንደሆኑ ይመስላሉ። ይኸውም፣ የኦሮሞ ጥያቄ ብቻ ሐቀኛ እንደሆነ እና ሕወሓት ሲሸፍት ጀምሮ በጠላትነት የፈረጀው የአማራ ሕዝብ ከሥልጣን ጥም በቀር ምንም ጥያቄ እንደሌለው የሚያስመስሉ ነበሩ።
ሸራፋ ነጻነት የለም!
በኔ እምነት፣ ነጻነት ለአንዱ ወገን ተሰጥቶ ለሌላው ሊነፈግ የሚችል አይደለም። ወይ ለሁሉም ይሰጣል፣ ወይ ለሁሉም ይነፈጋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ብሔሮች አንዳቸው ተለይተው ክልላዊ ነጻነት እና አገራዊ ተመጣጣኝ ውክልና ሊሰጣቸው አይችልም። ወይ ከሌሎቹ ጋር አብረው ይጨቆናሉ፣ አሊያም አብረው ነጻ ይወጣሉ። ሌላው ቀርቶ ሕወሓት እና አንጋሾቹ (cadres) ነጻ መውጣት የሚችሉት ሌሎቹ ነጻ ሲወጡ ነው። ለምሳሌ፣ አሳሪ እና ታሳሪ ባለበት ሁኔታ፣ ታሳሪው እስካለ ድረስ አሳሪውም ነጻ አይወጣም፤ ቢያንስ እስረኛው እንዳያመልጥ አሳሪውም በጥበቃ ይታሰራል።
 
ስለዚህ መፍትሔውስ?
መፍትሔው ለሁሉም የሚበጅ መሆን አለበት። እንደዚያ የሚሆነው ደግሞ ሁላችንም ለቀጣይ ሕልማችን (ፍትሕ፣ ርትዕ እና ሠላም) የሚበጅ መፍትሔ ለማፍለቅ ቅንነቱ ሲኖረን ነው። እርግጥ ለዚህ አሁን ሁሉንም ኃይል እና ዕድል የተቆጣጠረው ሕወሓት/ኢሕአዴግ ፈቃደኛ መሆን አለበት። ጉዳዩ ራሱንም ነጻ የሚያወጣው ነውና! አለበለዚያ የቱንም ያክል አፈናውን ቢጨምር፣ ሕዝባዊ ብሶቱም፣ አመፁም ይቀጥላል፤ ዛሬ በድርድር መፍታት የሚቻለውን ነገ በልመናም ማግኘት ይቸግራል።
በዚህ ገዢው ፓርቲ ይሰማ ይሆናል የሚል የዋህ እምነት የሚከተሉትን የመፍትሔ ሐሳቦች (ከተለያዩ ሰዎች እና አካላት የተሰጡ ምክሮችን አሰባስቤ እና አጥልዬ) እንደሚከተለው እጠቁማለሁ።
1ኛ) ይቅርታ
ሕወሓት/ኢሕአዴግ ከፅንሰቱ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ላጠፋው ጥፋት እና ወደጎጂ አቅጣጫ እንድንሔድ በመምራቱ የኢትዮጵያ ሕዝብን በተጻፈ ደብዳቤ ይቅርታ ይጠይቅ።
2ኛ) ምኅ-ዋስ
ኢሕአዴግ በፖለቲካ ሰበብ አስባብ ሥልጣን ከተቆጣጠረ ጀምሮ ያሰራቸውን፣ የተፈረደባቸውንም ይሁን ገና ፍርድ ቤት የሚመላለሱትን በሙሉ በምኅረት ይፍታ፤ ምኅረቱ በምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ወይም ድኅረ ሁኔታ ሊገደብ አይገባም። (‘ምኅረት’ የሚለውን ቃል የተጠቀምኩት እስረኞቹ ‘ጥፋተኛ’ በመሆናቸው ሳይሆን በሕግ አግባብ ትክክለኛው ቃል ስለሆነ ብቻ ነው።) በተጨማሪም፣ በሽብርተኝነት የተፈረጁት የስርዓቱ ተቃዋሚዎች ኦነግ፣ ግንቦት 7 እና ኦብነግ ይህ ሥያሜ ይሰረዝላቸው፤ የተሰደዱት ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የዴሞክራሲ አራማጆች እንዲሁም አማፅያን ወደ አገራቸው ገብተው የአገራቸውን ዕጣ ፈንታ በሠላማዊ መንገድ፣ በጋራ መፍትሔ የሚሰጡበት ዋስትና በአዋጅ ይረጋገጥላቸው።
3ኛ) ተዋስኦ (discourse)
ለጊዜው፣ ዴሞክራሲያዊ ተዋስኦን የሚያግዱት የፀረ–ሽብርተኝነት እና የመያድ አዋጆች ታግደው ዓለምዐቀፍ የሰብኣዊ መብት እና የዴሞክራሲ ተቋማት የሚመሩት/የሚያስተባብሩት በ‘ምኅዋስ’ የተፈቱ እና የተመለሱትን ዜጎች እንዲሁም አገር ውስጥ በዝምታና ፍርሐት የተቀመጡትን እና የአሁኑን ገዢ የሚያሳትፉ፣ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ አገርዐቀፍ እና ተከታታይ ውይይቶች ይካሔዱ።
4ኛ) ምርጫ
በመጨረሻም፣ አሁን ያለውን ምክር ቤት እና ምርጫ ቦርድ በማገድ፣ ገለልተኛ (ከሌላ አገር በመጡ ባለሙያዎች (technocrats) የተዋቀሩ) ወገኖች የሚመሩት አገርዐቀፍ (የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) እና የክልል ምርጫዎችን ማድረግ።
እነዚህ የመፍትሔ አማራጮች ላይ ሊሰነዘሩ የሚችሉት ትችቶች፦
ሀ) የሕወሓት/ኢሕአዴግን የማመቻመች (compromise) እምቢተኝነት ያላገናዘበ፣
ለ) አሁን የተቀሰቀሰውን አመፅ ሕወሓት/ኢሕአዴግን ከአቅሙ በላይ ሆኗል (ሊጥለው ደርሷል) በሚል ያልበሰለ ግምት ላይ ተመሥርቶ የተሰነዘረ፣
ሐ) የውጭ ኃይሎች ላይ ጥገኛ የሆነ፣
መ) የፌዴራሊዝሙን፣ የምርጫ ስርዓቱን፣ የፓርላማ ስርዓቱን እና ሌሎችም አወዛጋቢ ወይም “አገር አጥፊ” ጉዳዮችን ቅፅበታዊ መፍትሔ የማይሰጥ፣ የሚሉት ዋናዎቹ ናቸው ብዬ እገምታለሁ።
ነገር ግን (‘ሀ’ እና ‘ለ’ን በተመለከተ) የመፍትሔ አማራጮቹን መጻፍ ያስፈለገኝ ነገሮች እየተባባሱ መሔዳቸው አይቀሬ ስለሆነ ወይም ስለመሰለኝ እና በጊዜ ቢታሰብባቸው ይሻላል የሚለውን ምክር ሳይሰነዝሩ ከማለፍ ሞክሮ መክሰር ይሻላል የሚል እምነት ስላለኝ ነው። በሌላ በኩል፣ በምርጫ ሒደቱ እና ውጤቱ ላይ ምንም ዓይነት የግል ፍላጎት (ወይም እጅግ አነስተኛ የማጭበርበር ዕድል ያላቸው) ገለልተኛ – የውጭ አካላት ካልመሩት በስተቀር ሌላ የንትርክ መንስዔ ይሆናል የሚል ስጋት ስላለኝ ነው። ‘መ’ ላይ የተጠቀሰው ትችትም ቢሆን በሕዝባዊ ይሁንታ የተመረጠ ምክር ቤት እና በዚሁ መሠረት የተቋቋመ መንግሥት ካለ በሒደት እና ሕዝቡን በአሳተፈ መልኩ መፍታት የሚችላቸው ናቸው። ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ቢያስፈልግም በዚሁ መንገድ ማሻሻል ይቻላል። ለኔ፣ አስቸኳዩ፣ አሳሳቢውና መሠረታዊው ጉዳይ ብዙኃን የሚቀበሉት መንግሥት መመሥረት ነው።
Filed in: Amharic