>
4:42 pm - Tuesday January 18, 3250

ዘይቱን ያላዘጋጀ ሙሽራውን እንዴት ይቀበለው?  (መሳይ መኮንን)

ዘይቱን ያላዘጋጀ ሙሽራውን እንዴት ይቀበለው? 
መሳይ መኮንን
አብዲ ዒሌ እስር ቤት ገብቷል። በረከት ስምዖን የውርደትን እፍታ ቀምሷል።  ጌታቸው አሰፋ የሚደበቅበት ጉድጓድ ፍለጋ ላይ ተጠምዷል። አባይ ጸሀዬ ድምጹን አጥፍቷል። ስብሃት ነጋ በመቀሌ አክሱም ሆቴል ውስኪውን እየላፈ ቆዝሟል። በእብሪትና ትዕቢት ያበጠው የጌታቸው ረዳ ልብም ተንፍሷል። ሳሞራ የኑስ የጡረታ ዘመኑን በስጋት ይገፋል። አስመላሽ ወ/ስላሴ ግን አሁንም ይፎክራል። ሞንጆሪኖም ”የትላንቱ ይበጀናል” ዜማ እያቀነቀነች በትካዜ ተውጣለች። ደብረጺዮን መሀል ላይ ይዋልላል። አዲስ አበባ ሲደርስ ይደመርና ወደ መቀሌ ሲመለስ ይቀነሳል።
ወደ ለውጡ ቅጥር ግቢ ለመግባት አጥር ላይ የተንጠለጠሉ አንዳንድ የህወሀት አመራሮች እንዳሉ ይሰማል። የህዝብ ማዕበል ወደ ለውጡ ይጎትታቸውና የነባሮቹ ህወሀቶች ቁንጥጫ ይመልሳቸዋል። አጥሩ ላይ እንደተንጠለጠሉ አራት ወራት አለፋቸው። ህወሀቶች ዘይቱን ሳያዘጋጁ ሙሽራው መጥቶባቸዋል። ዘይቱ ንሰሀ ነበር። ሙሽራው ደግሞ ለውጥ። እናም ዘይቱን ያላዘጋጀ ሙሽራውን እንዴት ይቀበለው?
ባለፈው ሳምንት አንድ የናዚ የጦር ወንጀለኛ ለ70 ዓመታት ከተደበቀባት አሜሪካ ለጀርመን ተላልፎ ተሰጥቷል። በ95 ዓመቱ በእጆቹ ላይ ሰንሰለት ጠልቆ ከርቸሌ ገብቷል። በእኛም ታሪክ ተመሳሳይ ክስተት ተመዝግቧል። በቀይ ሽብር ዘመን መሪ ተዋናይ የሆኑ ነፍሰ ገዳዮች ለዘመናት ከተደበቁባቸው ሀገራት ማንቁርታቸው እየታነቀ ለፍርድ ቀርበው አይተናል። የቀልቤሳ ነገዎን እዚህ ላይ መጥቀስ ይቻላል። ከፍትህ ለጊዜው ማምለጥ ይቻል ይሆናል። ቢዘገይም ግን አይቀርም። ሞት ቢቀድም እንኳን ነፍስ ዘላለሟን እረፍት ታጣለች። መለስ ዜናዊ ለፍርድ ሳይቀርብ ቢሄድም ስሙ በምድር እየተረገመ፡ ነፍሱ በሰማይ እየተሰቃየ ነው። ከመቃብር በላይ ትቷት ያለፈው በዘር ልትበጣጠቅ ጫፍ የደረሰች ሀገር ነበረችና መለስ ከምድራዊ ፍርድ ቢያመልጥም ዘላለማዊ ስሙ የተወገዘ፡ የረከሰ ሆኗል።
ጌታቸው አሰፋ ለጊዜው ከፍትህ ተደብቋል። እንደሰማሁት በኢንተርፖል ራዳር ስር እንዲሆን እንቅስቃሴው ተጀምሯል። ወደ አሜሪካ ያሸሻቸው ቤተሰቦቹ ዘንድ ሊመጣ እንደሚችል ይገመታል። ከፎቶና ከቪዲዮ ተደብቆ ስለኖረ በቀላሉ ላይታወቅ ይችላል። ግን አያመልጥም። እየተሽሎከለከ እድሜውን ሊያቆይ እየሞከረ ነው። ከመደበኛው ፍርድ ለጊዜው ሊሸሸግ ይችላል። ከምንም በላይ ከህሊና ፍርድ አያመልጥም። በሄደበት የሚከተለው ትንሹ እግዚያብሄር የሆነው ህሊናው እረፍት ሲነሳው ይኖራል። የኢትዮጵያ እናቶች እምባስ መች በከንቱ ፈሶ ያውቅና?
ህወሀቶች ጸሀይ እየጠለቀችባቸውም የተሰጣቸውን እድል መጠቀም አልቻሉም። ሰሞኑን ከመቀሌ ተሰብስበው ያወጡት መግለጫ ጥርሱ አልቆበት በድዱ ለመናከስ የሚንገታገት ያረጀ አውሬ አስመስሏቸዋል። በምስራቁ በር አንዱ የጥፋት እጃቸው ተቆርጦባቸውም ለተስፋ መቁረጥ እጅ መስጠት አልፈለጉም። አብዲ ዒሌ የተሰኘ የጥፋት ፈረሳቸው አይናቸው እያየ  ከፍትህ እጅ ላይ ወድቋል። አያስመልጡት ነገር አቅም የለም። የእነሱንም እድል እጣ ፈንታ እርግጠኛ አይደሉም። ለጊዜው እድል ሰጥቶ የተዋቸውን ህዝብ ትዕግስት ግን እያስጨረሱት ነው።
ብአዴን
ብአዴን መጨረሻውን እያሳመረ ይመስላል። ከአፈጣጠሩ ጀምሮ በህወሀት ልክ የተሰፋለትን ጥብቆ አድርጎ የኖረው ብአዴን ሰሞኑን ያወጣው መግለጫ ከህወሀት ጋር የሚደረገው ፍቺ ቅርብ መሆኑን አመላካች ነው። ብአዴን ቆርጧል። የህወሀትን ቀሚስ አውልቋል። አርማና ስያሜ መቀየሩ ትርጉሙ ቀላል አይደለም። ህወሀት ብአዴንን ጠፍጥፎ ሲሰሰራ የልደት ቀኑን ከህወሀት የአፈጣጠር ታሪክ ጋር እንዲመሳሰል ስለመደረጉ መገመት ይቻላል። 11 ቁጥር ላይ የቆረበው ህወሀት የብአዴንን የልደት ቀን ህዳር 11 ላይ ያደረገው ያለምክንያት አልነበረም። አርማውን ከህወህት አርማ የተቀዳ አድርጎታል። ብአዴን አርማውን ብቻ ሳይሆን በህወሀት የተተከለትን የልደት ቀኑንም መቀየር ይኖርበታል።
የብአዴን መግለጫ የህወህት የበላይነት ፍጻሜ ላይ ትልቅ ሚስማር የቸነከረ ነው። ኦህዴድ ታህሳስ ላይ የብሄር ጭቆና የለም የሚል አዲስ ትርክት ይዞ ሲመጣ ህወሀት የሚይዝ የሚጨብጠው አጥቶ ነበር። የመጽአት ቀኑን ያየበት አስደንጋጩ ምልክት የታህሳሱ የኦህዴድ መግለጫ ነው ማለት ይቻላል። በብሄር ጭቆና ላይ ታሪክ ፈጥሮ ስጋ ደምና አጥንት አልብሶ፡ እስትንፋስ ዘርቶበት ኢህአዴግ በሚባል ፈረስ ኢትዮጵያን ለብዙ ዘመናት ሊጋልብ የተፈናጠጠው ህወሀት በኦህዴድ መግለጫ ህልሙ በአጭሩ ተቀጭቷል።  ሲጠበቅ የነበረው የብአዴን አቋም ነበር። ሰሞኑን ብአዴንም አፈረጠው። የብአዴን መግለጫ በህወሀት አንገት ላይ የጠለቀ ገመድ ማለት ነው። የሚቀረው ገመዱን ሸምቀቅ ማድረግና ህወሀት የረገጠውን መንጠልጠያ ማንሳት ነው። አዲዮስ ህወሀት!
መግለጫው በህወሀት ህልውና ላይ ሪፈረንደም ያደረገ ነው። የአማራ ክልል ወሰን ከእንደገና ይሰመር ዓይነት አቋም ከብአዴን ሲሰማ መቼም ተአምር ነው። ይህ ማለት የወልቃይት፡ ራያና ሌሎች አከባቢዎችን በተመለከተ ብአዴን ጥያቄ ለማንሳት ወስኗል ማለት ነው። በቅርቡ በአንድ መድረክ ላይ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የወልቃይትን ጉዳይ ከእንግዲህ ችላ የምንለው አይደለም ሲሉ ጠርጥሬአቸው ነበር። ይሀው የድርጅታቸው አቋም ሆኖ ይፋ ተደርጓል። የሱዳን ወታደሮች ከያዙት የኢትዮጵያ መሬት እንዲለቁ በብአዴን መጠየቁ ለህወሀት ትልቅ መርዶ ነው። ህወሀት ለሱዳን የኢትዮጵያን መሬት የሰጠበት ድብቅ ስምምነት የራሱ የሆነ ምክንያት አለው። ሱዳን ለህወሀት ምሽግ ናት። የክፉ ጊዜ መደበቂያ ናት። ለውለታዋ የጎንደር መሬት በስጦታ ተብርክቶላታል። ሱዳን ያን መሬት ከተነጠቀች ከህወሀት ጋር ያላትን ድብቅ ፍቅር መቀነሷ አይቀርም። ያ ደግሞ ለህወሀት የመጨረሻው ጥይት ነው። የትግራይ ህዝብ የተፋው ዕለት የሚደበቅበትን ዋሻ ያጣል ማለት ነው።
ብአዴን በግል መብት ላይ የወሰደው አቋም በራሱ ለህወሀት አስደንጋጭ ነው። በቡድን መብት ስም ዘረኝነትን በማስፋፋት የበላይነቱን አስጠብቆ ለመኖር ፕሮግራም(ህገመንግስት) የቀረጸው ህወሀት ከብአዴን በቃህ ተብሏል። የቡድን መብት እንዳለ ሆኖ የግለሰብ መብት ላይ ማተኮር ለዴሞክራሲ ወሳኝ ነው የሚል አቋም ላይ የደረሰው ብአዴን በብሄራቸው እየተደበቁ ቁማር የሚጫወቱ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞችንም ቅስማቸውን የሰበረ አቋም ላይ መድረሱ አስደናቂ ነው። ህወሀት በቁሙ ተዝካሩን በላና አረፈው። በዚህ አልቆመም። የህወሀትን ጥቅም በአማራው ህዝብ ኪሳራ ለማስጠበቅ በብ አዴን ውስጥ የተሰገሰጉ አፍቃሪ ህወሀት የሆኑ ቀንደኛ አመራሮችን ጠራርጎ ማባረር የጀመረው ብአዴን ለህወሀት አንድ መልዕክት እንዲደርሰው የፈለገ ይመስላል። ”በቃ”
በረከተ መርገምት
አቶ በረከት ስምዖን አየሩን ተቆጣጥሮታል። የመንደር የኮሚኒቴ ሬዲዮ ሳይቀር ደጅ እየጠና እንዳለም ሰምቼአለሁ። ብዙ ሰዎች በረከት ሰሞኑን የሰጠው ቃለመጥይቅና አብሮት ከተባረረው ታደሰ ጥንቅሹ ጋር የጻፉት ደብዳቤ ላይ በማተኮር የበረከት ቅጥፈቶች ላይ ጊዜ ሰጥቶ ሲወያዩ ታዝቤአለሁ። ለእኔ በረከት እንዲህ ተዝረክርኮ፡ በስጋት ተንጦ፡ ቅስሙ ተሰብሮ፡ የሚደገፍበት አጥቶ፡ ሲንከራርተት እንደማየት የሚያስደስት ነገር አላየሁም። ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፡ በምዕራብና ምስራቁ እየተወነጨፈ ያሻውን ሲያደርግ፡ ሲያስገድልና ሲያሳስር የከረመ፡ ምድር አልበቃ ብላው በሰማይ መንሳፈፍ እስኪቀረው የደረሰ፡ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ረጅሙን ርቀት የተጓዘ ሰው ዘመን ተገልብጦ፡ በሰፈረው ቁና የሚሰፈርበት ጊዜ መጥቶ ”እንዳልንቀሳቀስ ገደብ ተጥሎብኛል” ዓይነት እዬዬውን ሲያስነካው እንደመስማት ያለ ምን ድል ይገኝ ይሆን? እንደዚያ በትዕቢት ተወጥሮ የሚታወቀው በረከት ኩምሽሽ ብሎ፡ በፍርሃት ርዶ የምቆም የምቀመጥበት አጣሁ ሲል መስማት ለእኔም ሆነ የፍትህን መረጋገጥ ሲናፍቁ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ድል ነው።
በረከትን ሳስበው ሁል ጌዜ ከአእምሮዬ ጓዳ ብቅ የሚለው አንድ ወቅት ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ስለበረከት የተናገሩት ነው። ”መለስ ክፉ ነው። መለስን የበለጠ ክፉ ያደረገው ደግሞ በረከት ስምዖን ነው” እንግዲህ የክፋት አለቃ፡ የጭካኔ ደቀመዝሙር፡ የተንኮል ሀዋሪያ፡ የቅጥፈት አምባሳደር የሆነው በረከት ስምዖን ጊዜ ጥሎት፡ ዘመኑ አብቅቶ ዋጋውን ሊያገኝ ነው። በየሚዲያው ቀርቦ ”ቅዱስ ነበርኩ፡ ክንፍ የሌለው መልዕክ ከእኔ በላይ የት ይገኛል?” ዓይነት የሌባ አይነደረቅ ዲስኩሩን እየለቀቀው ነው።  በረከት ብአዴኖች ላይ የጀመረው ውግዘት አፈጣጠሩንና ስነልቦናውን እንድንመራመርበት የቤት ስራ የሚሰጠን ሆኗል። ምድር የተጠየፈችው፡ በእኩይ ምግባሩ ሀገርና ህዝብ በአንድ ሰልፍ ፊት የነሳው ሰው፡ ከደሙ ንጹህ ነኝ የሚል መፈክር ይዞ መልሶ ለእኛው ልንገራችሁ ማለት የጤና አይመስለኝም። የሚቀርቡት ወዳጆች ካሉት በጊዜ ዶክተሩን እንዲጎበኝ ቢመክሩት ጥሩ ነው። ጤናም እንዳልሆነ በብዙ ይነገርለታል።
በዘመኑ በሀሳብ የተለዩትን በጭካኔ አስሯል። የፖለቲካ ተቀናቃኝ ያላቸውን የሀሰት ዶሴ እየከፈተ ከእድሜአቸው ላይ ተቀንሶ በማጎሪያ እስር ቤት እንዲሰነብቱ አድርጓል። መለስ ሲሞት ለቅሶን በሀገር ደረጃ አደራጅቶ፡ ማቅ አስለብሶ፡ ህዝቡን በማህበር እንዲያዝን በማድረግ ታላቅ ግፍ የፈጸመ ወንጀለኛ ነው። በረከት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ስም ያለው ነው። ዛሬ ”በነጻነት፡ በፖሊሲ” እንከራከር ሲል አለማፈሩ ይገርማል። ዛሬ እሱ የሚጠይቀውን መብት ትላንት የጠየቁትን ሲያዋርድ፡ የቴሌቪዥን ድራማ እያሰራ ስም ሲያጨቀይና ገፍቶም ሲያሳስርና ሲያስገድል ዓለም የሚያውቀው ሰው ዛሬ ተነስቶ ”በፖሊሲ እንከራከር” ብሎ አይኑን በጨው አጥቦ መጥቷል። እንግዲህ ‘ፍትህ’ ለዚህ ሰውዬም ያስፈልጋል።
በረከትን ‘ኢትዮጵያዊው’ ጎብልስ በሚል የሚጠቅሱትም አሉ። የናዚው የፕሮፖጋንዳ ማሽን ጆሴፍ ጎብልስ ”ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል” የሚለውን አስቀያሚ ትርክት ለዓለም ያስተዋወቀ፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በዚሁ ትርክቱ የናዚን ወታደሮችና የጀርመንን ህዝብ ለጦርነት የማገደ እንደነበረ ይነገርለታል። በረከት ስምዖን የዘመኑ ጎብልስ ሆኖ ኢትዮጵያውያን ላይ ተሰይሟል። ሀገሪቱን የውሸት ፋብሪካ አድርጓት አንድ ትውልድ በውሸት ተወልዶ እንዲያድግ ፈርዶበታል። በእርግጥ በናዚው ጎብልስና በህወሀቱ ጎብልስ መሀል ልዩነት አለ። ጎብልስ የቆመለት የናዚ ስርዓት ሲገነደስና እንደአምላክ የሚያየው አዶልፍ ሂትለር ራሱን ሲያጠፋ ጎብልስም ስድስት ልጆቹን መርዝ አብልቶ እሱንና ሚስቱንም በሽጉጥ ገድሎ ይህቺን ምድር ተሰናብቷል። በረከት ስምዖን ግን ፈሪ ነው። አምላኩ መለስ ዜናዊ ሞቶም እሱ እስከአሁን አለ። ወንድሙን ገድሎበት እንኳን በታማኝነት የገበረለትና የተገዛለት የህወሀት ስርዓት በቁሙ ሲገነደስ እያየ በረከት ግን መኖር ይፈልጋል። ፈሪ። መርገምት።
 እኔ በእሱ ቦታ ብሆን የክብር ሞቴን በገዛ ፍቃዴ እውን አደርጋለሁ። ሰው እንዴት ሳር ቅጠሉ ሳይቀር ጠልቶት፡ እዚህም እዚያም ቤተክርስቲያን እንደገባች ድመት እየተባረረ መኖርን ይመርጣል? በረከት ስምዖን ለፍርድ ቀርቦ ማየት እፈልጋለሁ። በየሚዲያው የሚለው ለመስማት ጊዜም አፕታይቱም የለኝም። በረከት የሚነግረኝ የማላውቀው የለም። እሱ ዘንድ ለእኔ የሚጠቅም መረጃም ሆነ እውቀትም ይኖራል ብዬ አላምንም። በረከት የውሸት አቁማዳውን ይዞ በየሚዲያው ደጅ እየጠና ነው። የክፋት መርዙን አሁንም ለመርጨት ታጥቆ ተነስቷል። በረከት የክፋት አቅሙ አልደከመም። ለብ አዴን ከታደሰ ጥንቅሹ ጋር በጻፈው ሀሜት መሰል ደብዳቤ ላይ ለማ መገርሳንና ገዱ አንዳርጋቸውን ለማጋጨት ይሞክራል። እናም ሚዲያዎች ይህን ሰው ሲያገኙት መርዙን ረጭቶ ብቻ እንዲሄድ ባይፈቅዱለት ጥሩ ነው። ነፍሱ እስኪላቀቅ የሚጠይ በመረጃና ማስረጃ በረከትን ራቁቱን የሚያስቀር እንጂ የበረከትን ዲስኩር እንደወረደ የሚያስተናግድ ሚዲያ ለጊዜው አያስፈልገንም። በረከት በቃው!
Filed in: Amharic