>
4:42 pm - Tuesday January 18, 5814

ኢትዮጵያ የአንድ ብዙ ልጇን እቅፏ ልታስገባ ሽር ጉድ እያለች ነው [ቋጠሮ]

ኢትዮጵያ የአንድ ብዙ ልጇን እቅፏ ልታስገባ ሽር ጉድ እያለች ነው

ቋጠሮ

ታማኝ በየነ፤ ከ25 ዓመታት በኋላ ወደ ሃገር ሊገባ ነው። ለታማኝ የሚደረገውን የአቀባበል መርሃ-ግብር አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ እንደተመለከተው በሚቀጥለው አርብ የአገሩን መሬት ይረግጣል። ኢትዮጵያም “ውዱ የክፉ ቀን ልጄ እንኳን ደህና መጣህ!” ብላ የአንድ ብዙውን ልጇን እቅፏ ልታስገባው በጉጉት እየጠበቀች ነው።

ታማኝ! የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ልጅ መባሉ ባለፉት 27 ዓመታት ያደረገው እንቅስቃሴ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጓዳ ያንኳኳ ስለነበር ነው ።

ታማኝ የሰባዊ መብት ተሟጋች

 • በግፍ ለታሰሩ ወገኖች ጮኋል፡
 • ከቅያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች አልቅሷል፤
 • በየትኛው የሃገሪቷ ክፍል የተፈጸሙ የግፍ ግድያዎችን አውግዟል፤
 • በርሃብ ለተጎዱ ወገኖች ደርሷል፤
 • የተረሱ ጀግኖች ተገቢ ክብር እንዲያገኙ አድርጓል፤
 • አስታማሚና ረዳት ያጡ ብርቅዬ ኢትዮጵያዊያንን አሳክሟል፤ ረድቷል፤
 • በአረብ አገር የሚሰቃዩ እህቶችን አለሁላችሁ ብሏል፤
 • መብታቸውን በጠየቁ ሽብርተኛ ለተባሉት ሙስሊም ወገኖቹ ጮኋል፤
 • ለዋልድባ መነኮሳት ስቃይ አልቅሷል፤
 • ለቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ድምጽ ሆኖ ተሟግቷል፤

ሌላም ሌላም ….. ብቻ በደል በነበረበት ሁሉ ታማኝ ነበር ፤ ግፍ በተፈጸመበት ሁሉ ታማኝ አለ፤ የድረሱልኝ ጥሪ በተደመጠበት ሁሉ ታማኝ ፈጥኖ ደርሷል፤  በሚል ላጠቃለው። እናም ከዚህ ሁሉ ዝርዝር ተግባራቱ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ያልተነካ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይኖራል ብሎ መገመት ይከብዳል። ለዚህም ነው ታማኝ የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ልጅ …የምንለው!!!

እነዚህ እንግዲህ ባለፉት 27 አመታት በሰባዊ መብት ተከራካሪነትና በበጎ አድራጎት እንቅስቃሴው ካደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ጥቂቶቹ ናቸው።

ታማኝ አገዛዙን ተቃዋሚ አክቲቪስት

ታማኝ አፋኙን ህወሃት መራሽ ሥርዓት በመታገል ረገድም ከ1983 ግንቦት 20 ጀምሮ በጽናት ተንቀሳቅሷል።

የሥርዓቱን እጸጾችን እየነቀሱ ያጋለጡ ፡

 • ሽብርተኛ ማነው ?
 • ፌዜ-ራሊዝም፤
 • የቁልቁለት ጉዞ፤
 • እባብን ለሰለሰ ተብሎ በኪስ አይያዝም
 • በመከላከያ ውስጥ የህወሃትን የበላይነት ያጋለጠበትና ሌሎችም በርካታ ዘጋቢ ቪዲዮዎች አቅርቧል።

ታማኝ የኢሳት የጀርባ አጥንት

ታማኝ የወያኔን እለተ ሞት ካፋጠኑት የሚዲያ አውታራት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደውን ኢሳትን በማቋቋም ረገድ እሱም የአንበሳውን ድርሻ ወስዷል። ለኢሳት ገቢ ለማሰባሰብ ኢትዮጵያዊያን ባሉበት የዓለም ጥጋግ ሁሉ ተጉዟል። ለዚህ ዋቢ በማድረግ የምጠቅሰው እኔ በምገኝበት አውስትራሊያ ያደርገውን አድካሚ ቆይታ ነው፡፤ ታማኝ ለኢሳት ገቢ ለማሰባሰብ በአውስትራሊያ በሚገኙ 5 ስቴቶችና በኒውዚላን ባደረገው ቆይታ በቂ እንቅልፍ ሳያገኝ ከ75 ሰዓታት በላይ በረራ አድርጓል። ለማሳያ ያህል የአውስትራሊያ ቆይታው ተገለጸ እንጂ በተለያዩ ዓለማት ሲዞር ይህን መሰል በርካታ አድካሚ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የአንድ ወቅት መደበኛ ተግባሩ ነበር፡፤ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ደግሞ ለልጆቹና ለቤተሰቡ ሊሰጥ የሚገባውን ግዜ በመሰረዝ ነበር።

ታማኝ የቴሌቪዥን ፕሮግራም መሪ

ታማኝ ከኢሳት ቀደም ባሉ ዓመታት ከጥቂት ሰዎች ጋር ሆኖ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኔት ወርክ የሚል የቴሌቪዥን ጣቢያ ከፍቶ ህብረተሰቡን ሲስተምር ሲያዝና፤ ታሪክና ባህል ሲያስተዋውቅ ነበር።

ኢሳት ከተቋቋመ በኋላም በጀመረው “ታማኝ ሾው” በተሰኘው ፕሮግራሙ በርካታ ያልታዩ ታሪካዊ ቪዲዮዎችን ከክምችቱ እያቃመሰ ፤ የታሪክ ክተትን እየሸፈነና እያዝናና ይገኛል።

ባጠቃላይ ታማኝ ብቻውን፤ ከተቃዋሚ ድርጅት ባላነሰ ወያኔን ፈትኗል።ታማኝ ብቻውን፤  ከታጣቂ ባላነሰ ወያኔን አቁስሏል ። ታማኝ ብቻውን፤ ከሰባዊ መብት ድርጅቶች በላነሰ የወያኔን ግፍ አጋልጧል። ታማኝ ብቻውን ከበጎ አድራጎት ድርጅት ባላነሰ የተቸገሩን ረድታል።

እናም ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ሳምንት ይህን የአንድ ብዙ ልጇን እጆቿን ዘርግታ ትቀበላለች። ዜጎቿም ለጀግና ወንድማቸው የክብር አቀባበል ለማድረግ ዝግጅታቸውን አጠናቀው በጉጉት እየጠበቁ ነው።

ጎበዝ ከዚህ በላይ ምን የሚያስደስት ነገር ይኖር ይሆን? … ታማኝ ይህን ሁሉ ዋጋ የከፈለላትን የሃገሩን መሬት ሲረግጥ ፤ ስቃይህ ስቃዬ ነው ብሎ የጮሕለትን ወገኑን ሲቀላቀል የሚፈጠረውን የደስታ ስሜት ለማየት ጓጉቻለሁ……

ውድ ታማኝ በሰላም ለሃገርህ ያብቃህ…

Filed in: Amharic