>

ሰሚ የሌለው የምድረበዳ ጩህት!!! (ቬሮኒካ መላኩ)

ሰሚ የሌለው የምድረበዳ ጩህት!!!
ቬሮኒካ መላኩ
ትናንት የአማራ አክቲቪስቶች  ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ  ንባብ በነፃ ይውል ዘንድ እንደ ሀምሌ ጌሾ በበይነመረብ ላይ  ያሰጡትን የበረከትን መፅሀፍ  በፒዴፍ “አውርድ” ብዬ  አዝዤ ያወረድኩትን ለማንበብ ጀምሬ አሮጌ የመንግስት ፋይል እንደሚያገላብጥ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ  ምንም ነገር ሳጣበት ሰአቴን በማባከኔ እየቆጨኝ ተመለሰኩ።
በረከት የመጨረሻው ቀሽምና አሰልች ፀሃፊ ነው። ቃላቶችን እንደጉድ ያባክናል ሳይሆን ያዝረከርካቸዋል ማለት ይሻላል።
በ6 ቃላት ሊገለጥ የሚችለውን ጉዳይ በ25 ቃላትና በረጅም አረፍተ ነገር  ያንዛዛዋል።
 በመፅሀፉ  አይረቤነት ብሽቅ  ብልም ብስጭቴን የሚያካክስ የአራዳ ልጆች ያፌዙበትን ሳይ ብብቱ ውስጥ ገብተው እንደኮረኮሩት ህፃን ልጅ ፍርፍር አድርገውኛል።
አንዱ የተረገመ  “በረከት ሁሉንም ሚዲያዎች ጨርሶ ሲያልቅበት ኢትዮጵያን አይዶል ላይ ቀርቦ “ደመቀ “፣”ገዱ “ እያለ መዝፈኑ አይቀርም “አለ ።
ወደ ቁምነገሩ ስመለስ የበረከት የሰሞኑ ከአንዱ ሚዲያ ወደ ሌላ ሚዲያ ጡል ጡል እያለ የሚያዝረከርከው ባዶ ኩነና (  Vacant condemnation) በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን በቃህ ሊባል ይገባል።
በረከት ስምኦንና ምክትል ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን የሁለት አለም ሰዎች ናቸው። በረከት እልም ያለ ተራ ዱርዬ ነው። ውሸት የበረከት መለዮና ማንነት ከሆነ  አመታት ተቆጥረዋል። በረከት ተሳስቶ እውነት መናገር አልፈጠረበትም።
በረከት ከ20ኛ ፎቅ  ላይ እየተምዘገዘገ እየወደቀ ሳለ 8ኛ ፎቅ ያሉ ሰዎች ” እንደት ነህ? ” ቢሉት ” እረ በጣም ደህናነኝ ” የሚል አይንአውጣ ነው ።
በተቃራኒው ደመቀ መኮንን እጅግ ሲበዛ ትእግስተኛና ትሁት (Humble) ሰው ነው። አባይ ፀሃዬ ፈርሞ ለሱዳን የሰጠውን መሬት እንኳን ” ደመቀ ነው የሰጠው ” እየተባለ ሲብጠለጠል  መልስ ለመስጠት ያልፈለገ ሰው ነው። ይሄ ዝምተኛነቱ ግን እየጎዳው ነው። በረከትም ደመቀ ዝምተኛ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው ስሙን ጥላሸት በመቀባት የተጠመደው። በረከት የጀመረው blame _ shifting በአስቸኳይ ተገዝግዞ መቆረጥ አለበት።
እርግጥ የበረከት ጩህት በህዝቡ ዘንድ ማንም የማያዳምጠው የምድረበዳ ጩህት ( Crying in the Wildness)  መሆኑ የታወቀ ቢሆንም ውሎ አድሮ ሲደጋገም ግን ጉዳት ሊያመጣ ይችላል።
በረከት አሁን ስራ ፈት ፖለቲከኛ ነው። ስራ ፈት ፖለቲከኛ ደሞ ሴራ ሲጎነጉን የመዋል እድሉ ከፍተኛ ነው።
ፈረንጆቹ “An idle mind is the devil workshop ” ( ስራ የፈታ አእምሮ የሰይጣን  ስራቤት ይሆናል)  የሚሉት ወደው አይደለም።
በመጨረሻ  እንደ በረከት ስምኦን ያሉ ወንጀለኛና ውሸተኛ እየበዙና አየሩን እየተቆጣጠሩ ከመጡ  እውነተኛዎቹ እየሳሱና ዝም እያሉ ከመጡ አሁንም አገራችን አደጋ ላይ ናት ።
እንግሊዛዊው ደራሲ ዊሊያም ሸክስፒር ” Oh Justice thy has flown to beasts “( ፍትህ ሆይ! ወደ አራዊት በረርሽን)  እንዳለው የኢትዮጵያም ፍትህ ወደ አራዊቶቹ በመብረር አብራቸው ቁጭ ብላ እየዘመረች እንደሆነ እየተመለከትን ነው። ፍትህ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ጭቁኖች ብትሆንማ ኖሮ እነበረከትን የመሰለ አለምአቀፍ ወንጀለኞች ጆሯችንን በነጋ በጠባ ባላደነቆሩት ነበር ።
Filed in: Amharic