>

የአቋም ሰው! ታማኝ በየነ!!!! (ኤርሚያስ ለገሰ)

የአቋም ሰው! ታማኝ በየነ!!!!
ኤርሚያስ ለገሰ
ታማኝ በየነ ዶቅማዎችን እያየ ሾላዎችን ፣ ዝግባዎቸውን እያየ ጥዶችን አይረሳም። እያንዳንዱ የዛፍ አይነት የራሱ ባህሪያት ቢኖረውም ሁሉም ደኑን እንደፈጠሩት ያምናል። ጫካው የእያንዳንዱ ተክል ድምር ውጤት ነው።
 ኤክስትሮቨርቶች ሰብአዊነት፣ የኔታነትና መስኮት ሰባሪነት ደምረው ሲይዙ የአቋም ሰው ይሆናሉ። ግንባር ቀደምትነት ከእውቀትና መልካም ሳምራዊነት ጋር ሲዋሃድ የመርህ ሰው ያደርጋል።
የአቋም ሰው በራሱ ይተማመናል። የማኅበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት እንደሚነግሩን በራስ መተማመን በግልም ይሁን ቡድናዊ ህይወታችን ውስጥ የምናስመዘግበውን የስኬት መጠን ይወስናል። በራስ መተማመን የፈጠረ ሰው በራሱ ላይ ከመለወጥ አልፎ የሌሎችን ሰዎች ህይወት በመርህና መልካም አቅጣጫ እንዲቀየር ያደርጋል። በራስ መተማመን ክህሎትና የግል ብቃትን ከማሳደግ ይመነጫል። ታማኝ የአቋም ሰው ነው ስንል ቁርጠኝነት እና በራስ መተማመንን እንደ ዋነኛ ማስፈፀሚያ መሳሪያ ስለሚወስድ ነው።
                      ***
ታማኝ የአቋም ሰው በመሆኑ ምሉዕ እንዲሆን አድርጐታል። ምሉዕ በመሆኑ ለነፃነት ሲታገል ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። የሰው መውደዱ በቤተሰቦቹ ዙሪያ የታጠረ ሳይሆን አጠቃላይ ሕዝቡን ጭምር ነው። የሚታገለውን ሐይል በአገም ጠቀም ሳይሆን እስከመጨረሻው ጫፍ በመሄድ ጭምር ነው። የጥፋት ሀይሉን ግለሰባዊም ሆነ ቡድናዊ አሻጥር ለማጋለጥ ቀን ከሌት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። የእውነተኛ እና ያልተሸራረፈ ፍትህና ርትህ ጥማት አለው። የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃነት መደፈርና መረገጥ በራሱ ጫንቃ ላይ የመከራ ሸክም የተሸከመ ያህል ይሰማዋል።
                    ***
ታማኝ በሚያስተላልፈው ማዕከላዊ መልዕክት ላይ ሁለንተናዊ እይታ አለው። ጫካውን እያየ ዛፎችን አይረሳም። እዚህ ላይ የዶክተር ታደሰ ብሩን አማርኛ ልዋስና ስብዕናውን ልግለጠው። ታማኝ በየነ ዶቅማዎችን እያየ ሾላዎችን ፣ ዝግባዎቸውን እያየ ጥዶችን አይረሳም። እያንዳንዱ የዛፍ አይነት የራሱ ባህሪያት ቢኖረውም ሁሉም ደኑን እንደፈጠሩት ያምናል። ጫካው የእያንዳንዱ ተክል ድምር ውጤት ነው።
 አገራችን ኢትዮጲያ ጫካ ናት። በውስጧ ያሉት ደግሞ የተለያየ ባህሪና እድሜ ያላቸው ዛፎች ናቸው። ዛፎቹ ከሌሉ ጫካው አይኖርም። ጫካው ከወደመ እያንዳንዱ ዛፍ ይቃጠላል።እናም ታማኝ በየነ ኢትዮጲያን ኢትዮጲያ ያደረጋት የሁሉም ድምር ውጤት እንደሆነ የፀና እምነት አለው።
                     ***
ታማኝ የአቋም ሰው በመሆኑ መራሩን ሀቅ ይጋፈጣል። ዝሆኑ በመኖሪያ ቤት ውስጥ መኖሩን ለመናገር ወደ ኃላ አይልም። ግጭት አይሸሽም። መራሩ ሀቅ ምንም ያህል መስዋዕትነት ቢጠይቀው ተስፋ አይቆርጥም። አላማዬ ብሎ ለተነሳበት ጉዳይ ጥልቅ ስሜት አለው። ለተግባራዊነቱ በፅናት ይታገላል። በመድረክ ንግግሩ፣ በአዳራሽ ዲስኩሩ፣ በሚዲያ በሚሰጠው አስተያየት፣ በዘጋቢ ፊልሞቹ አገራችን የገባችበትን መራር ሀቅ ተጋፍጧል። የተዘራው የዘር ፓለቲካ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ለመሄድ ፓስፓርትና ቪዛ የሚያስጠይቅበት ደረጃ እያደረሰን እንደሆነ ስጋቱን ገልጧል። እንደ ሩዋንዳ መታወቂያ ላይ በተፃፈ የዘውጌ ማንነት እርስ በራስ መተላለቅ ሊመጣ እንደሚችል በአደባባይ አስጠንቅቋል።
ይህም ሆኖ ኢትዮጲያ በሚደረገው በመርህ ላይ የተመሰረተ ትግል ነፃ ትወጣለች የሚል ተስፋ የሰነቀ ሰው ነው።ጨለምተኛ አይደለም። ኢትዮጲያ እንደምትድን ልበ ሙሉ ነው። የጀግኖች መብቀያ የሆነችው አገራችን አሁንም እንዳልነጠፈች የፀና እምነት አለው።
       እምነቱ ይሳካለት!!
                  ***
 ( “ጥላሁን ያረፈ ቀን” ከሚለው መጽሐፌ ገፅ 273 -274 የተወሰደ)
Filed in: Amharic