>

* በባህር ዳር በጎንደር ደማቅ የሆነ የክብር አቀባበል ይጠብቀዋል! (አቶ ንጉሡ ጥላሁን)

 በባህር ዳር በጎንደር ደማቅ የሆነ የክብር አቀባበል ይጠብቀዋል!

–  አቶ ንጉሡ ጥላሁን


    ዛሬ ከጠዋቱ 1፡30 ላይ አዲስ አበባ የሚገባው አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ፤ ከቦሌ አየር ማረፊያ ጀምሮ ደማቅ አቀባበል የሚደረግለት ሲሆን የፊታችን ሰኞ ወደ ባህር ዳር እንደሚያመራና በዚያም ልዩ አቀባበል እንደሚጠብቀው ታውቋል። ለታማኝ አቀባበል የተቋቋመው ኮሚቴ፣ አርቲስቱን በልዩ ሁኔታ ለመቀበል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የአማራ ክልል አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
አርቲስቱ በባህር ዳር አየር ማረፊያ ልዩ አቀባበል ከተደረገለት በኋላ ወደ ባህር ዳር ስቴዲየም እንደሚሄድና ከሚወደው ህዝብ ጋር በግንባር እንዲገናኝ እንደሚደረግ አቶ ንጉሱ ተናግረዋል። በማግስቱ ማለትም ነሐሴ 29 ቀን 2010 ዓ.ም ከከተማው ወጣቶች ጋር የሚነጋገርበት የውይይት መድረክ መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡ በቀጣዩ ቀን ወደ ጎንደር እንደሚሄድና በዚያም በተመሳሳይ መንገድ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግለት አቶ ንጉሱ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
“ለአገር አንድነት፣ ለህዝቦች መቻቻልና መከባበር ሲታገሉ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ክልላችን በልዩ አክብሮትና ፍቅር ይመለከታል” ያሉት አቶ ንጉሱ ጥላሁን፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደረገላቸው ጥሪ ከተለያዩ አገራት የሚመጡና ለአገራቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የየትኛውንም ፓርቲ አባላትና እንግዶች ክልላቸው በከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት እንደሚቀበል ገልፀዋል፡፡
በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ የሚገባውን አርቲስት ታማኝ በየነንና ጳጉሜ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ አገራቸው የሚመለሱትን የግንቦት 7 አመራሮች ለመቀበል የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ኢትዮጵያውያን ለመቀበል የተቋቋመው ‹ናፍቆት› የተሰኘው የአቀባበል ኮሚቴ፤ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችም በግላቸው የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮችን ለመቀበል ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ትናንት በተዘዋወርንባቸው የፒያሳ፣ አዲሱ ገበያ፣ ኮልፌና ሜክሲኮ አካባቢዎች “ነፃነትን የሚያውቁ ነፃ አውጪዎቻችንን በክብር እንቀበል”፣ “እንኳን በድል ተመለሳችሁ፤ እናከብራችኋለን” ወዘተ የሚሉ መልዕክቶችን የያዙ ባነሮች እንዲሁም የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮችና የታማኝ በየነን ምስሎች የያዙ ፖስተሮች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተለጥፈው አይተናል፡፡ ወጣቶች አካባቢያቸውን በማፅዳት፣ የተቆፈሩ ጉድጓዶችን በመድፈንና የተለያዩ የፅዳት ሥራዎችን በማከናወን አቀባበሉን ያማረ እንዲሆን ተፍ ተፍ እያሉ ይገኛሉ፡፡
በዛሬው ዕለት ታማኝ በብሔራዊ ቴአትር የሙያ አጋሮቹ ደማቅ አቀባበል የሚያደርጉለት ሲሆን በነገው ዕለት ከ10 ሰዓት ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ ልዩ የሙዚቃ ፕሮግራም ተዘጋጅቶለታል

Filed in: Amharic