>

አዲሶቹ መንደርተኞች (ከይኄይስ እውነቱ)

አዲሶቹ መንደርተኞች

ከይኄይስ እውነቱ

ነገደ ብዙ ኢትዮጵያ አንዴ ሲሰፋ አንዴ ሲጠብ በኖረው መልክዐ ምድሯ የየራሳቸው ቋንቋ÷ ባህል÷እምነት፣ ታሪክ÷ትውፊት ያላቸው፤ በዘመናት መስተጋብር እነዚህ እሴቶች ተወራርሰውና ተመጋግበው ኢትዮጵያዊነት የሚባል የጋራ ብሔራዊ ማንነትና ሥነ ልቡና ፈጥረው ባንድ ሰንደቅ ዓላማ ሥር የኖሩባት አገር ነች፡፡ ይህ የጋራ ማንነትም ለሕዝቧ የአንድነት÷የጥንካሬ÷የክብርና ኩራት ምንጭ ሆኖ በክፉም ሆነ በደጉ ጊዜ የውስጥም ሆነ የውጭ ፈተናዎችን ተቋቁማ በጥቁሩ የዓለም ማኅበረሰብ ውስጥ የነፃነት ፈርጥ ሆና እንድትዘልቅ ረድቷታል፡፡

ባንፃሩም የሀገረ መንግሥትነት ታሪኳ ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆንም፤ እንደ እምዬ ምንይልክ ዓይነት ጥበብን ከማስተዋል፣ ጀግንነትን ከትእግስትና ርህራሄ፣ ብልህነትን ከየወሃት ገንዘቡ ያደረገ ንጉሠ ነገሥት ኖሯት ቢያውቅም፤ አሁን እስካለንበት 21ኛው መቶ ክ/ዘመን ድረስ መንግሥተ ሕዝብ ለመመሥረት አልታደለችም፡፡ ድንቁርና፣የአካባቢ ጉልበተኞች ለሥልጣን ያደረጉት የርስ በርስ የማያቋርጥ ግጭት፣ፍርድን የማያደላድሉ÷ የሀብት እኩል ተጠቃሚነትን የማያረጋግጡ÷ ባጠቃላይ ተፈጥሮአዊ ነፃነቶቹንና መብቶቹን የሚገፉ አገዛዞች እየተፈራረቁበት መደቆሱ፣ ሕዝቡም ለኑሮው ኃላፊነት አለመውሰዱና በእምነት ሽፋን ግፍና ጭቆናን ለመሸከም ያሳየው ዝንባሌ፣ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና መሠሪነት ታክሎበት ወዘተ. በነገረ መንግሥትም ሆነ በማኅበረ ምጣኔ ሀብት ረገድ ከሥልጣኔ የተራቆተች፣ ከፊተኞች መካከል አንዷ የነበረች ብትሆንም አሁን ጭራ ከሆኑት ከኋለኞቹ መካከል የምትገኝ አገር ሆናለች፡፡

በቡሀ ላይ ቈረቈር እንዲሉ ባለፉት 27 ዓመታት ደግሞ አገዛዝ የሚለው ብቻውን የማይገልጸው አገርና ሕዝብን ለማጥፋት የክፋትና ተንኮል ጥግ የተባለውን ኹሉ የፈጸመ ወያኔ ትግሬ የተባለ ሀገር በቀል የወንበዴዎችና የአሸባሪዎች ቡድን በኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ÷ በዘር ፖለቲካ አምሶንና አተራምሶን የአምላክ ቸርነት ባይታደገን ኖሮ የኢትዮጵያን ህልውና ከቋፍ አድርሶ እንደነበር የወራት ትውስታ ነው፡፡ ይህ የደናቁርትና ባለጌዎች ስብስብ በመላ ኢትዮጵያ የመንደርተኝነትን መርዛማ አስተሳሰብ ከመርጨቱ በተጨማሪ እንደ ለደባል ሱስ ተገዥነት÷ አለመተማመን÷ የጭካኔን ድርጊት ማየትም ሆነ መስማትን መለማመድና መደንዘዝ ÷ለከት የሌለው ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት÷ ሥርቆትና ቅጥፈትን የመሳሰሉ ነውሮችን የማኅበረሰባችን ‹ባህል› እንዲሆን በእጅጉ ደክሟል፡፡ ሕዝባችን የተፈተለበትን ማኅበራዊ ድርና ማግ ከመሠረቱ በማናጋት ለዘመናት የተገነቡ መልካም እሴቶች እንዲሸረሸሩ አድርጓል፡፡ ማኅበራዊ ድቀቱ ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ የዘር ፖለቲካውን ያህል አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ባጠቃላይ ለኢትዮጵያ በተለይ ለበቀለበት ትግራይ ማፊሪያ የሆነ ይህ የድውያነ አእምሮ ስብስብ ሕዝብና አገር እንዲሁም ታሪክ በጭራሽ ይቅር የማይሉት ነውሮችን ኹሉ ፈጽሟል፡፡

ወያኔ ትግሬ በጉልበት ለያዘው ሥልጣንና ይህንንም ተገን አድርጎ ለፈጸመው ቅጥ ያጣ ዝርፊያ የአገርን ህልውና መያዣ ከማድረጉ ሌላ እስካሁን መፍትሄ ያልተበጀለትን በታሪክ ተወዳዳሪ የሌለው ግፍና መከራ ባደባባይ መርሐ ግብሩ አድርጎ÷ ዐቅዶ÷ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትንም የማጥፊያ ዋና ስልት አድርጎ በአማራው ነገድ ላይ እልቂትን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህ ነገድ በተለየ መልኩ የወያኔ ትግሬና ጠፍጥፎ የሠራቸው 3ት የጎሣ ድርጅቶች (ከጥቂት ወራት ወዲህ አንዳንዶቹ ከወያኔ ፍቺ በመፈጸም በለውጥ ሂደት ጅማሮ ላይ እንደሆኑ ቢነገርም) ጥቃት ሰለባ የሆነበት ምክንያት የ‹ጨቋኝነት› የፈጠራ ትርክት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዐቢዩ ምክንያት ገና ከማለዳው ቤተ ዘመድ÷ጎሣ÷ነገድ÷ዘር ከሚባሉ መንደርተኛ አስተሳሰቦች ራሱን አላቅቆ የሥልጣኔ ዓይነተኛ መለያ የሆነውን ዜግነትን (ኢትዮጵያዊነትን) ገንዘብ አድርጎ ለሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹም በቅድሚያ አብነት ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ ነገድ ተገኝተናል የሚሉ ወገኖች የዚህን ነገድ ጥቃት የማስተባበያ ምክንያት (pretext) አድርጎ በማቅረብ ወያኔ ትግሬ አገር ያጠፋበትን የዘር ፖለቲካ ለማራመድ (ቊጥራቸውን በውል ባላውቀውም) የ‹ፖለቲካ ድርጅት› በማቋቋም አዲስ ‹ነፃ አውጪዎች› ለመሆን ቢያንስ በወሬ ደረጃ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ እየተደመጡ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በተናጥል ነፃ መውጣት የሚባል ነገር የለም፡፡ ባንድ ሕዝብ ዘንድ ግማሽ ነፃነት ግማሽ ባርነት ባለመኖሩ፡፡

በሌላ በኩል አንድን ሃሳብ ባንስማማበትም÷ባንቀበለውም ከነፃነት አኳያ ማስተናገድ አንድ ጉዳይ ነው፤ ሃሳቡ ላገርና ለሕዝብ የማይበጅ ሆኖ በተግባር ተገልጦ አደጋ እንደሚያመጣ ተገንዝቦ መቃወም ደግሞ የተለየ ጉዳይ ነው፡፡ ደጋግሜ እንደገለጽኩት የተጠቃን ነገድ ለመታደግ በማኅበረሰብ ተቋምነት ተደራጅቶ በጎ አስተዋጽኦ ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጂ በ‹ፖለቲካ ማኅበርነት› ተደራጅቶ ነፃ አወጣኸለሁ ማለት ግን ነገዱን አስቀድሞ ከደረሰበት የሥልጣኔ ማማ ማውረድና ማዋረድ ነው፡፡ አንድ ነገድ በግለሰብም ሆነ በፖለቲካ ድርጅት አይወከልም፡፡ ሕዝብ ከድርጅት በላይ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለጊዜው የ‹ፖለቲካ ማኅበርን› በዘር የማደራጀቱ ጉዳይ በወያኔ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› የተከለከለ ባይሆንም (በተቃራኒው የሚበረታታ ነው) የተፈቀደ ኹሉ ግን አይጠቅምም፡፡ በዚህ ረገድ ከበቂ በላይ የሆነ 27 የጨለማ ዘመን ተሞክሮ አለን፡፡ ይህ ተረፈ-ወያኔነት ነው፡፡ የወያኔን የጨለማ ምዕራፍ እየዘጋን ባለንበት ሰዓት ተረፈ-ወያኔ ሆኖ ብቅ ማለት ትርጕሙ ምንድን ነው? ለዚህም ይመስለኛል የአዲሶቹን ጎሠኞች እንቅስቃሴ የነ በረከት/ወያኔ እጅ አለበት እየተባለ የሚታማው፡፡ በቅርቡ አንዱ የዚህ እንቅስቃሴ አባል ነኝ የሚል ግለሰብ የኢትዮጵያ ዕንቊ ልጅ የሆነው የጥበብ ሰው እንዲሁም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነ ላይ ዛቻ አዘል በማር የተለወሰ እሬት መልእክት ማስተላለፉ ይህንን ጥርጣሬ በጣም የሚያጠናክር ይመስለኛል፡፡ ሰው ጎሣ/ነገዱን ይዞ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ያለና የሚኖር ነው፡፡ ልዩነት ባንድነት የሚባለውም ይህ ነው፡፡ ችግሩና ግጭቱ የሚመጣው ሃይማኖት÷ ዘር÷ነገድ÷ጎሣ ወዘተ. ሳይለይ ኹሉን በእኩልነት የሚያስተናግደውን ሥልጡን የዜግነት ፖለቲካ ትቶ ፖለቲካን በዘር/ደም ቋጠሮ ላይ መሥርቶ ለመንቀሳቀስ ሲሞከር ነው፡፡  ይህ ዓይነቱ አደረጃጀት እንኳን የአንድ አገር ሕዝብ ለማስተዳደር ይቅርና ማኅበራዊ ለሆኑት ለዕድርና ዕቁብም አይመጥንም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ማጭበርበርና ማጨናበር የትም አያደርስም፡፡ ወንድማችን ታማኝ የመድረክ ናፍቆት ኖሮትና ፈልጎ የመጣ ሰው አይደለም፡፡ አንድ ነገድን ወክሎም አልመጣም፡፡ የሱ መነሻና መድረሻም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው፡፡ ታማኝን ያህል እንደ ወርቅ በመከራ የተፈተነ ወንድማችን በዛቻ አቋሙን የሚለውጥ ይመስላችኋል? ዛቻውን ‹ምክር› ለማለት የዳዳው ግለሰብ ከመነሻውም ባይሞክረው ጥሩ ነበር፡፡ ራሱንም ሆነ እወክለዋለሁ የሚለውን የጎሣ ድርጅት ግምት ውስጥ ከማስገባት ባለፈ ድርጊቱን ነውረኛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ግለሰቡና እወክለዋለሁ የሚለው ድርጅት በራሱ የሚተማመንና የዓላማ ጽናት ካለው በታማኝ መገኘት ምን አስበረገገው? በነገዱ በደልና ጥቃት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ የሚያደርገውን ‹የንግድ› እንቅስቃሴ ያስተጓጉልብኛል ብሎ ሠግቶ ይሆን?

ለማጠቃለል በማቀርባቸው አስተያየቶች ኹሉ የዘር ፖለቲካን ጉዳይ ወይም የወያኔን ትግሬ ግዙፍ ጥፋት ደጋግሜ የማነሳው በከንቱ አይደለም፡፡ አገር አጥፊና በቀጣይም የህልውናችን ፈተና መሆኑን በመገንዘብ እንጂ፡፡ በተደጋጋሚ የሚደረገው ሙከራ አንድን ኢትዮጵያዊ ከዘር ፖለቲካው መርዝ ነፃ ካወጣ እንደ ትልቅ ውጤት እቆጥረዋለሁ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ የአዲሶቹ ጎሠኞች አነሳስ ምናልባት በቅንነት ከሆነ እግዚአብሔር ልቦናውን እንዲሰጣቸው እመኛለሁ፡፡

Filed in: Amharic