>
2:43 am - Sunday December 5, 2021

በረከትና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ (ተስፋዬ ሃይለማሪያም)

በረከትና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ

ተስፋዬ ሃይለማሪያም

ደስ የሚለኝ ማስታወቂያ አለ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ማስታወቂያ፡፡ ቢራውን ባልፈልገውም ፤ ማስታወቂያው ግን በጣም ደስ ይለኛል፡፡

እንዲህ ይላል ፤

– ጣልያን ከኢትዮጵያ ሲባረር ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ነበረ፡፡

– አበበ ቢቂላ በሮም በባዶ እግሩ ማራቶንን ሲያሸንፍ ፤ ያኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ነበረ፡፡

– ኢትዮጵያ ሶስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ስታሸንፍ ፤ ያኔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ነበረ፡፡

– ጃንሆይ ዋይት ሀውስን ሲጎበኙ ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ነበረ፡፡

ነገር ግን በተመሳሳይ ፤

– ወያኔ በለስ ቀንቶት አዲስ አበባ ሲገባ ፤ በረከት ስምኦን ነበረ፡፡

– የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ወያኔን ተቃውመው ሲወጡና እነ ተስፋሁን ሲገደሉ ፤ በረከት ነበረ፡፡

– አሰፋ ማሩ በጠራራ ፀሀይ ሲረሸን ፤ በረከት ነበረ፡፡

– አንዋር መስጊድ ወገኖቻችን ሲገደሉ ፤ በረከት ነበረ፡፡

– በ97 ምርጫ ሰበብ እነ ሺብሬ እና የ14 ዓመቱ ታዳጊው ነብዩ አለማየሁ ባንክ ሊዘርፉ ነበር ተብለው ሲገደሉ ፤ ያኔም በረከት ስምኦን ነበረ፡፡

– መለስ ዜናዊ ጣት እንቆርጣለን ብሎ በፎከረ ማግስት የብዙ ወጣቶች የመሀል ጣት እንደ ካሮት በፒንሳ ሲቆረጥ ፤ ያኔ በረከት ስምኦን ነበረ፡፡

-እነ ታጋይ አበበ ካሴ ወንድነታቸው ሲኮላሽ ፤ በረከት ነበረ፡፡

በአጠቃላይ በረከት ስምኦን እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ በሁሉም ዘመን ነበረ፡፡ በሁሉም ግፍና ሰቆቃ ውስጥም ነበረበት፡፡ በረከት ያላየው ቦታ የለም፡፡

በመጨረሻ ግን አንድ ያላየውና የግድ ማየትና መሞከር ያለበት ቦታ አለ፡፡ ቂሊንጦ፡፡

Filed in: Amharic