>

ከታማኝ ተማሩ! (ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው)

ከታማኝ ተማሩ!

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው

አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ዛሬ ብዙ ነገር ተናግሯል። መክሯል። ምክሩ ለብሔርተኛው ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ ብሔርተኛ ነኝ ለሚለው ጭምር ነው። ታማኝ አማራ የለም ብለው አታካራ ውስጥ እንደሚገቡት አይደለም። ከጣሊያን አንስቶ እስከ ዛሬ በማንነቱ የሚቆስለውን ሕዝብ ቁስልም በግልፅ ተናግሯል።

ታማኝ ሌላ ትልቅ ቁም ነገር ተናግሯል። አማራ ክልል ተብሎ የተከለለው ትክክል እንዳሆነ፣ አማራው ክልል እንደሌለው ገልፆአል። አክቲቪስትና አርቲስት ታማኝ በየነ በዚህ ንግግር በግልፅ የተናገረው ብሔርተኛ ተብለው የሚፈረጁት የሚጠይቁትን ነው። ይህን ትህነግ/ህወሓት የከለለውን የሚቀበል የለም። አነስ ሲል ወልቃይት፣ ራያና መተከልን ይጠይቃል። ከፍ ሲል ደግሞ አማራ በሚኖርበት መላው ኢትዮጵያ መብቱ እንዲከበር ሲጮህ ነው የሚሰማው። ከጉራፈርዳ እስከ ጅጅጋ፣ ከወለጋ እስከ ቴፒና ጋምቤላ የሚኖረው አማራ በሀገሩ ተንቀሳቅሶ የመኖር መብቱን ተነፍጓል ብሎ የሚጮኸውን እንደ ፅንፈኛ የሚታይበት ጊዜ አለ።

“ውጣልኝ፣ ሀገርህ አይደለም” የተባለውን ድምፅ በመሆኑ “አማራ በሀገሩ ተፈናቀለ” በማለቱ “አማራ አማራ አትበል” የተባለ አለ። ታማኝ አማራ ድንበር የለውም ሲል የት እንደሚኖር፣ ለማንና ምን እንደሰራም ያውቃል፣ አይደብቅም።

ከብሔርተኛው ይልቅ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ ነን የሚሉት ለአማራው ደንብር አስቀምጠዋል። አማራ ብሔርተኛ የሚባለው አዲስ አበባ የአማራ ርስት ናት ይላል እንጅ አዲስ አበባ የሚኖረውን ሕዝብ ከአማራ ተሰድዶ የመጣ፣ መጤ ነው አይልም። ታማኝ አዲስ አበባ የሚኖረውን “ከአማራ ክልል ፈልሶ የመጣ ነው አላለም። መጤ፣ ባይተዋር አላደረገውም።

ታማኝ የተናገረው “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” እንደሚባለው ኢትዮጵያዊ ነኝ እያለ “አዲስ አበባ የሚኖረው አማራ ከአማራ ክልል ተሰድዶ የመጣ ነው” ለሚለው የአንድነት ኃይል ጭምር ነው። ታማኝ የተናገረው በሀገር ግንባታው ዘመን፣ በድንበር ጥበቃው ወቅት፣ በወራራ መከታው ጊዜ ብዙ ዋጋ ክፍሎ፣ ሀገር ገንብቶ፣ ሀገርን ታድጎ ሀገሬ ነው ብሎ የተቀመጠውን “ውጣልኝ፣ ሂድልኝ” ለሚሉት የዘመኑ ገዥዎች ነው።

ታማኝ ሕዝብ ማንነቴ ነው ያለውን አይደለህም ብሎ አልካደም፣ ታማኝ የሕዝብን ቁስል አልደበቀም። ታማኝ አማራው አዲስ አበባ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ……በመላ ኢትዮጵያ መጤ ነው እያሉ ለሚያፈናቅሉት ወይንም ለሚያፈናቅሉት መሳርያ ለሚሰጡት ተቃዋሚ ነን፣ አንድነት ሀይል ነን ለሚሉትም ጥሩ ምክር ሰጥቷል። ታማኝ አማራው ክሉሉ ኢትዮጵያ ናት ሲል፣ አማራውን “መጤ ነህ አትበሉት፣ አማራውን ውጣልን አትበሉት፣ አማራውን ድንበር አትከልሉለት፣ ወደ ሐገርህ ሂድ አትበሉት፣ ሐገሩ ኢትዮጵያ ናት” ነው ያለው። ቅኔ የሚገባው፣ እውነት የማይከብደው ካለ። ይማር! ከታማኝ ተማሩ! አትካዱ ትካዳላችሁ፣ ታመኑ ትታመናላችሁ!

Filed in: Amharic