>

ከድክመታችን ይልቅ የተደመረ ጥንካሬያችን ብዙ ዋጋ አለው!!! (ዮናታን ተስፋዬ)

ከድክመታችን ይልቅ የተደመረ ጥንካሬያችን ብዙ ዋጋ አለው!!!
ዮናታን ተስፋዬ
እነዚህ ሁለት ኢትዮጵያዊያን በሀገሪቱ እየተካሄደ ላለው የለውጥ እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። በሰው ሀገር ሆነው የወገናቸው ህመም እንቅልፍ ነስቷቸው አፈናው ያቆሰለውን ህዝብ መተንፈሻ መድረክ ፈጥረውለታል። በመረጃ እጦት በጭቆና አለንጋ መከራውን ያይየነበረውን ህዝብ ጆሮ እና አንደበት የሆኑ OMN እና ESAT አቋቁመው ለነፃነት ትግሉ ጉልህ አስተዋፅዎ አበርክተዋል!
ኢትዮጵያዊነትን ማንነቱ ያደረገው ታማኝም ሆነ ኢትዮጵያዊነት የዜግነት ማንነት ነው የሚለው ጃዋር ለሀገራቸው በተሰደዱበት ሆነው የማይተካ ሀገራዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል። ለሰብዓዊ መብት መታገል ማለት እንዴት እንደሆነ በተግባር አስተምረዋል። ለወገናቸው ነፃነት በየአደባባዩ ሰልፍ አስተባብረው ጮኸዋል፤ በእስር ለሚማቅቁ የነፃነት ታጋዮች የሰው ፊት እየገረፋቸው ገንዘብ አሰባስበው ጠበቃ ቀጥረዋል፣ የነፃነት ታጋዮች ቤተሰብ እንዳይበተን ረድተዋል፣ የታመሙ አሳክመዋል ….፤ የመንግስት ባለስልጣናትን ወንጀል አጋልጠዋል – አያሌዎች ያመኗቸው በዚህ እና መሰል የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸው የፈፀሟቸው ተግባሮች ነው። ብዙ ተከታይ ያፈሩት መሬት የወረደ ስራ በመስራታቸው ነው።
ጃዋርም ሆነ ታማኝ እንደማንኛውም ሰው ይሳሳታሉ። ፍፁማን አይደሉም። ሁለቱም የሚያደሉለት የፖለቲካ አመለካከትን ለማስፋፋት አንዱ ሌላውን ያስከፋ ድርጊት ፋፅመው ሊሆን ይችላል። ከአገዛዝ ቀንበር ለመውጣት የመረጡት የማታገያ ስትራቴጂ የተለያየ በመሆኑ የሚፈጠሩ ግጭቶች አልነበሩም ማለት ስህተት ይሆናል። ግን ከድክመቶቻቸው የሚልቀው በጎ አስተዋፅዖዋቸው ነው። ከሳቱት ይልቅ የጠቀሙን በስራቸው ውጤት ገዝፎ ይታያል።
ያም ሆነ ይህ እነዚህ ሁለት የሀገራችን ልጆች ለኢትዮጵያ እጅግ ያስፈልጓታል። አፋኝ ስርዓት ለመጣል በተለያየ የማታገያ ስልት ዛሬ ላይ ያደረሱን እነዚህ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከዚህ በኋላ አንድ ላይ ቢሰሩ የበለጠ የሚጠቀመው ህዝብ ነው። ከመረጡት የማታገያ ስልት የተነሳም የአንደኛው የድጋፍ መሰረት ለሌላኛው ድጋፍ ባይኖረውም – ሁለቱ ከዚህ በኋላ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ተስማምተው አንድ ላይ ቢሰሩ የድጋፍ መሰረታቸው ይሰፋል – ለህዝቡም የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ይሆናል።
እኔ ለሁለታችሁም ከፍ ያለ ክብር አለኝ። Jawar Mohammed & Tamagne Beyene እንደ አንድ ዜጋ የሁለታችሁ እምቅ አቅም እና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ተደምሮ ለኢትዮጵያ ብሎም ለምስራቅ አፍሪቃ የሚተርፍ ስራ ስትሰሩ ማየት ማገዝ ምኞቴ ነው። ከስሜት በላይ ከፍ ብላችሁ ለሀገር ግንባታ – ለዘላቂ የዴሞክራሲያዊ ስርአት በአንድ ላይ ብትሰሩ  ህዝብ ያተርፋል እናንተም ከአሁኑ በላቀ ሁኔታ ታሪክ በደማቁ ይዘክራችኋል።
አንድ ልመርቅ 
ጃዋር መሃመድና ታማኝ በየነበጋራ ይስሩ ሲባል አንዱን ካንዱ ማወዳደር አይደለም። ሁለቱም የየራሳቸው ጠንካራ ጎን እና ደካማ ጎን አላቸውና። አብረው ቢሰሩ ሲባል በቪዲዮው እንደምትመለከቱት የሁለቱ የማይናቅ ተፅዕኖ ፈጣሪነት እና ተደማጭነት ከግምት በማስገባት ነው! የሁለቱን የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት እምቅ አቅም በጋራ ለሀገር ጥቅም እንዲውል ነው።
ምን አልባትም በተለጠጠ የፖለቲካ ባህላችን ውስጥም ቢሆን አብሮ መስራት ለሁለቱም አዲስ ነገር አይመስለኝም። በሙስሊሞች የሃይማኖት ነፃነት ትግል ላይ የሁለቱ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አስተዋፅዖ እና አጋርነት በቪዲዮው ላይ መመልከት ይቻላል!
ኢትዮጵያ ለሁሉም ሁሉም ለኢትዮጵያ!
Filed in: Amharic