>
10:10 am - Sunday May 22, 2022

ሁለት ነጥቦች ከታማኝ የባሕርዳር ንግግር (መንግስቱ ሙሴ)

ሁለት ነጥቦች ከታማኝ የባሕርዳር ንግግር
መንግስቱ ሙሴ
 
1- አማራ ክልል የለውም!
2- የጅምላ ፍርጃ ይቁም!
የህወሓት እርኩስ አላማ ከሽፏል፣ ያስቀመጠችው ስርአት የሚጋሩ ግን አሁንም ጥንካሬ ስላላቸው ይህ ስርአት ማለትም “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የተባለ ዘረኛ ስርአት ሲወገድ እና በዴሞክራሲያዊ ስርአት የግለሰብ እና የወል መብትን በሚያከብር ሲተካ ችግሩ የሚወገድ ይሆናል!
 
ጆሴፍ እስታሊን በሶቪየት ሶሻሊስት እሪፖብሊክ የአንድ የአናሳ ብሄር ተወላጅ የሆነ የቦልሸቪክ መሪ ነበር።የጆርጅያው ተወላጅ  እስታሊን የብሄር ጥያቄን ለጥጦ የእስከመገንጠል መብት ሰጥቶ የራሱን ፓርቲ ያሳመነ እና አለማቀፍ የኮሚኒስት/ሶሺያሊስት ንቅናቄወችም እንዲቀበሉት ያደረገ ሰው ነበር። ይህን የእስታሊን ሀሳብ ግን ሁሉም ሳይሆኑ የጀርመን የሁለተኛው አለማቀፍ ሶሻሊስቶች እና የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የቱርክ ኮሚኒስት ፓርቲወች አልተቀበሉትም። እነዚያ የአውሮፓ አውራ ፓርቲወች ላለመቀበል ምክንያት የሆናቸው ሀገሮቻቸው ሰፋፊ የቅኝ ግዛቶች ስለነበራቸውም ነበር። በእርግጥ የእስታሊን ቲዮሪ በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩ ለነጻነታቸው ለሚያደርጉት ትግል ቀና ጎዳና ቢሆንም – እንደኢትዮጵያ ላሉ እና እንደነወያኔ/ኦነግ ላሉት ጠባብ ኀይሎች ግን አፍራሽ ሚና እንዲይዙ አድርጓል። ያም ሆነ ይህ እስታሊን እራሱ ቲወሪው በስራ ላይ ከዋለ ከ70 አመታት በኋላ የእርሱ እትብት የተቀበረባት ጆርጅያ የእርሱን ቲወሪ በስራ ላይ አውላ ከአባት ሀገር ተገንጥላ የእራሷን ግዛት መስርታለች።
ወደ እኛ ወደተነሳሁበት ስመለስ
ታማኝ በየነ ጥሩ እና እውነተኛ ቃል ተናግሯል። አማራ ክልል የለውም ክልሉ ኢትዮጵያ ነች። ልክ ነው ህወሓት ሰፍራ የሰጠችው ክልል ሶስት ከተባለው ክልል ውጭ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር አማራ ይኖራል። እናም ይህ አባባል ለአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያ ሀገሩ ናት የኔም ሊላት ይገባል የሚለውን ሀቅ ያሳያል። ግን ምንም እንኳን አማራ በሁሉም ኢትዮጵያ ቢኖርም መብቱ በህገመንግስት የተገፈፈ ሕዝብ ሆኖ እንጅ እንደአንድ የሀገሪቱ ዜጋ ተከብሮለት አይደለም። ለምሳሌ ሀረር ከተማን ህወሓት ለሀረሪ አስተዳደር ሰጥታለች። ብዙሀኑ የከተማዋ ነዋሪ ግን አማራ ነው። ይህ ብዙሀን ሕዝብ ግን ከፖለቲካው የታገደ ሕዝብ ነው። በብዙ የደቡብ፣ የምስራቅ እና የምእራብ ኢትዮጵያ ከተሞች አማራው ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛል። አስተዳደሮች ግን ለሌሎች የተሰጠ ነው። በነዚህ ሰፋፊ ቁጥር ባላቸው ከተሞች የሚኖረው ዜጋ ምንም እንኳን በሀገሩ መኖሩ ግልጽ ቢሆንም መብት አልባ ነው። ይህ ለ27 አመታት የተንሰራፋው የዘር ስርአት እና አወቃቀር በሀሰት እና በጅምላ የወነጀለውን አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ ሕጋዊ ጭቆና እያካሄደበት እስከ ዛሬ  ከተሰጠው ክልል ውጭ እንዳይመረጥ እና በአስተዳደር እንዳይሳተፍ በማድረግ ቀጥሏል። ይህን የተዛባ የአስተዳደር እና የመብት ገፈፋ ለማስቆም ሀገራዊ ድርጅቶች አንድም አቋም ክልልላዊነትን ከመቃወም ባለፈ አዲስ ሀሳብ የላቸውም ወይንም አልሰማሁም። ሀገራዊ እና የአንድነት ኀይሎች የክልልን እና ዘር ላይ የተመሰረተ ስርአትን ማፍረሻ አማራጭ ይዘው እስካልቀረቡ ችግር ቀጣይ መሆኑን ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ከሁሉም አትድረሱብን የሚለው አባባል በግልጽ ባይነገርም በሁሉም ክልሎች የሚታይ የሚዳሰስ እውነታ ነው። እናም እንደኔ ችግሩ በአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ያለ እና ስርነቀል መፍትሄ የሚሻ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። በሌሎች የተንሰራፋውን ይህ የሌላውን መብት መጋፋት፣ የአትድረሱብን አቋም በአንድ አካባቢ ብቻ ያለ ማስመሰል አይገባም ለማለት ነው። ባጭሩ ታማኝ በድፍረት ይህን ገጥሞታል። በእርግጥም አማራ ሀገሩም ሆነ ክልሉ ኢትዮጵያ እንጅ ህወሓት አጥብባ እና ሸራርፋ ለማጥፋት እንደሞከረችው ሊሆን አይችልም። የህወሓት እርኩስ አላማ ከሽፏል፣ ያስቀመጠችው ስርአትን ግን የሚጋሩ አሁንም ጥንካሬ ስላላቸው ይህ ስርአት ማለትም “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የተባለ ዘረኛ ስርአት ሲወገድ እና በዴሞክራሲያዊ ስራት የግለሰብ እና የወል መብትን በሚያከብር ሲተካ ችግሩ የሚጠፋ ይሆናል። የኔ ሀሳብ የአንድነት አቀንቃኝ የሆንን ሁሉ የስርአቱ ማብቃ ላይ ትኩረት ሰጠን ከታገልን ችግሩ በብርሀን ፍጥነት ይወገዳል የሚል እምነት አለኝ።
ታማኝ ገዥወች በሚሰሩት ጥፋት እና ወንጀል ሕዝብ ተጠያቂ ማድረግ አይገባም ይላል። ይህም እውነት ነው። እዚህ ላይ አማራ ጠላት ተብሎ ሲፈረጅ አማራ ባልሆኑ ገዥወች መሆኑ ግን ድርብርብ ጥፋት መሆኑን አሁንም የሚቀበል የለም። እስካሁን በሰማነው ሌጀንድም ሆነ እውነተኛ ታሪክ እኔ አማራ ነኝ ያለ ንጉስ አልነበረም። አልፎ ተርፎ መንግስቱ ኃይለማርያም የመራውን ወታደራዊ መንግስት በይበልጥም ቀዩ ሽብር በሰፊው በአማራ ላይ በተካሄደበቱ ስርአት መንግስቱን እና የእርሱን ዘመን የአማራ ብለው አሁንም የሚያደናቁሩትን እንዲህ እንደዛሬ ታማኝ እንዳደረገው ሊነገር ይገባል እናም ሕዝብ ሕዝብን አልበደለም የሚለው የሁላችን ስራ ሊሆን ግድ ነው። ይህን ስል ቀዳማዊ ኃይለስላሴም ሆኑ፣ መንግስቱ ከአማራነታቸው ይልቅ የሌሎች መሆናቸው ሲታወቅ በታሪክ መሪወች ኢትዮጵያዊ እና የኢትዮጵያ እንጅ የዚህ ወይንም የዚያ ተብለው አይታወቁም። አንድ ነገር በእርግጥ ለመናገር ነገስታቱ ልጆቻቸውን ሲድሩም ሆነ እነርሱ ለጋብቻ ሲቀርቡ ከተለያዩ አቻ የዘር መሳፍንት ወገን እንደሆነ በማስረጃ ማቅረብ ይቻላል።
Filed in: Amharic