>
4:47 pm - Tuesday May 17, 2022

የብሄር ፖለቲካን ስንገላልበው ፤ ለቅመን ፈትለን አደባባይ ስናሰጣው !!! (ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ)

የብሄር ፖለቲካን ስንገላልበው ፤ ለቅመን ፈትለን አደባባይ ስናሰጣው !!!
ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ
ገላልጠን—እንየው 1
የብሄር ፖለቲካ መሰረታዊ የሰው ልጅ ባህሪን የሚስት ኋላቀር ፖለቲካ ነው። የሰው ልጅ በርካታ ማንነቶችን አነባብሮ ባንድነት የያዘ ሆኖ ሳለ ብሄርን (ጎሳ ነው ትክክለኛ ትርጉሙ) ብቻ መርጦ ለፖለቲካ ድርጅት መጠቀም አያሳምንም። በሀይማኖትስ? በሴትነትስ? በቋንቋስ? በሞያስ? ፖለቲካ መነሻም መድረሻውም ሰው ነው። ሰው መሆን ይቀድማል። ፖለቲካ ሰው የግልና የጋራ ጥቅሙን አድቫንስ ለማድረግ በገዛ ፍቃዱ የሚደራጅበት እንጂ ከእናቱ ማህፀን የሚጠጋን እየፈለጉ፣ የአወላለድ ካርታን እያጠኑ፣ በአርባቀን እድል የሚወሰን ነገር አይደለም። የብሄር ፖለቲካ ሽል ፖለቲከኛ ነው። እጣፈንታው ቀድሞ ተወስኖለታል። ከዚህ የባሰ መሰረታዊ የሰው ልጅን ባህሪ መሳት የለም!!!
ገላልጠን እንየው 2
የብሄር ፖለቲካ ለክርክር፣ ለውይይት እና አሳምኖ ለማመን የማይመች፣ በሰጥቶ መቀበል ላይ የማይመሰረት መንጋነትን የሚያበረታታ በመሆኑ ለህግ የበላይነት፣ ለዴሞክራሲ ደንቃራ ነው። የብሄርህ አባል ህግ ጥሶ መሸሸጊያው ብሄር ነው። ከሀላፊነት መሸሺያ ጉያ ነው። በችሎታ፣ በፈጠራ እና የሰው ልጅ አዕምሮ ለሚደርስበት ክህሎት ቅድሚያ የማይሰጥ ፖለቲካ በመሆኑ ችሎታ ያላቸው እየተደበቁ፣ አፈጮሌዎች በስልጣን ጥማት ፈረስ ላይ ተፈናጠው የግል የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት ባለብሩህ አዕምሮ ግለሰቦችን በመድፈቅ ለብሄሩ ተቆርቋሪ እኔ ብቻ ነኝ በሚል አሳሳች ሚዛን ማስተዳደር ሳያውቁበት ለብሄሩ ጥፋትን ያመጣሉ።
ማሰብ ለግለሰብ እንጂ ለብሄር አይሰጥም። የግለሰብን የማሰብ፣ ባሰቡት አቅደው የመስራት የግል ራዕይ ላይ የብሄር ፖለቲካ አላግባብ ጣልቃ የሚገባ የነፃነት ፀር ነው!!!
ፈታትለን ስናየው 3
የብሄር ፖለቲካ የጎሰኝነት የስሜት ሰንሰለት ላይ የተንጠለጠለ አይዲዮሎጂ የለሽ ባዶ ፖለቲካ ነው። ጎስኝነት ከጋርዮሽ ስርዓት በፊት እንጂ ከጋርዮሽ  ስርዓት በኋላ እንድንኖር የማያስችል የስው ልጅን ግለሠባዊ እና ማህበራዊ እሤት የሚደፍጥጥ ያልዳበረ ስብስብ ነው።  ኢትዮጲያ ጎሣ እና ፖለቲካን በመቀላቀሏ በጥበትና  መርህ አልባነት የውንብድና ስብስብ እየተመራች ፍዳዋን አይታለች። ይሄ ሀገር የጎሳ ተወካይ ነን በሚሉ ለመዝረፍ በቋመጡ ሽፍቶች እና አንዘረፍም በሚሉ ሰው በሆኑ ዜጎች መካከል በሚካሄድ የሃስብ እና የተግባር ጦርነት እየታመስ ይገኛል። ጎስኝነት ሀስብ ስለሌው ሲሞገሥም ሲያሞግስም ያለቅሳል።
ጎሰኝነት ዳቦ ማምረት ሳይሆን ዳቦ ለመስረቅ ቃል መግባት ላይ የሚያተኩር የውንብድና ስብስብ። የእንትና ብሄር ብዙ ስለበላ ተራው የኛ ነው የሚል በደልን በካሳና በእርቅ ሳይሆን በሌላ በደል ለመክፈል የሚሰራ ቂል የያዘው ሠይፍ ነው። ይህ ውንብድና ህጋዊ የሆነባት ሀገር ደግሞ የኔና ያንተዋ ሀገር ነች። ጎሰኝነት የአፍንጫ ንፍጥ ነው። ከውጪ ለሚያየው ጸያፍ ለባለቤቱ ደግሞ የአፍንጫ ሎሽን የተቀባ የሚመስል። ጎስኝነት መመራት ካለበት በጎሳ መሪ እንጂ በፖለቲከኛም አይደለም። ፖለቲካ የጋራ እና አካታች ነው የብሄር ሲሆን አግላይና በፍረጃ የተሞላ ፍትህን ለራስ ወገን እንጂ ለሰው ልጅ በሞላ ለማጎናፀፍ የማይችል ያደርገዋል። ብሄርተኝነት እኛ እና እነሱ በሚል የልዩነት መሰረት ላይ ስለሚቆም ለዴሞክራሲ የማይመች ከፋፋይና ዘልዛይ ክፉ ደዌ ነው።
በታትነን ስናየው 5
በመንደርትኝነት የተሰባሰበ ቡድን ለዚህ ያበቃኝ ጭቆና ነው ይበል እንጂ ፀቡ ከጭቆና ጋር ሳይሆን ከጨቋኙ ማንነት ጋር ነው። በጭቆና ክፉነት ላይ የተመሰረተ ተግባቦት የለውም። የኔው ጅብ ይብላኝ ይልሃል። የአማራ ጭቆና የተባለው በትግሬ ጭቆና ተተካ። አማራ ላይ የተዘራው ጥላቻ ትግሬ ላይ እየበቀለ ዛሬ ወደመናየው አዙሪት እየገባን ነው። የጎሳ ፖለቲካ ከዚህ የበደል አዙሪት ወጥቶ በህግ ላይ የተመሰረተ ህብረት ለመሆን ይቸገራል። ፍርሃትን መንዛትና የተጠቂነት መንፈስን በማራገብ ግለሰብ የሚባለውን የፖለቲካ መሰረት ሽባ ያደርገዋል። ጭቆናው ይቀጥላል። አዙሪቱም እንደዚያው። የብሄር ፖለቲካ! የሃጠራዉ ፖለቲካ!!!
ስናፍታታው 6
የብሄር ፖለቲካ ስሌትና ግቡ የግል ጥቅምና ስልጣን ነው። ስልጣንን ከ110 ሚሊየን ህዝብ ጋር በውድድርና እራስን በማስመስከር ትግል ለማሳካት ከምደክም ምንትስ በተሰኘ መንደርተኝነት ፉክክሩን ከጥቂት ሚሊየኖች፣ መቶ ሺዎች ጋር በማድረግ እድልን ለማስፋት የሚደረግ መልቲና ብልጣብልጥ ቁማር ነው። አይዲዮሎጂውም ጠላትን በማራባትና በደልን በማከክ ፍርሃትና ተስፋቢስነትን እያስፋፉ ድሪቶ በድሪቶ ላይ መቀጣጠል ነው!!!
ከፋፍተን ገላልጠን ስናይ 7
የብሄር ፖለቲካ፣ የእኩልነት ፖለቲካ ሊሆን አይቻለውም። ብሄር “እኛ” በሚባል የራስ ስሜት እና “እነሱ” በሚል የጎሪጥ ጥርጣሬ ያዘለ ስሜት ላይ ነው የሚቆመው። የእኛ የሚለውን ወገን የመጨረሻ ጥቅም አሟጦ ለመጠቀምና ይህን በማንኛውም መንገድ ማስጠበቅ የብሄር ግብ። የብሄር ፖለቲካ ከሰው ልጅ የመልመድ፣ የመለወጥ፣ የመዋሃድ እና የመቀየጥ መሰረታዊ ሃቅ የሚያፈነግጥ ፀረሎጂክ አስተሳሰብ ነው።
 አባት እና እናትህ የተለያየ ብሄር ካላቸው አንተ የሌሊት ወፍ ነህ። ሁለቱም ብሄሮች ይጠራጠሩሃል። በብሄር/ዘር ፖለቲካ ፀብ ከመጣ ለልጅልጅ ይተላለፋል። የማንነት ፀብ ስለሆነ ቂም አጥፊውን ግለሰብ አይፈልግም። የዘር/ጎሳ አንድነት ብቻ ለቂም መወጣጫ ይበቃል። ይህ ያስፈራል። የጎሳ ፖለቲካ መጨረሻው ለማይታወቅ ቀውስ ይዳርገናል። በሀሳብና አስተያያት በመሰባሰብ፣ በርእዮተ አለም ላይ ፀብ ቢነሳ፣ ርእዮተአለሙ ሲቀየር ፀቡም ይከስማል። የኢህአፓና መኤሶን ፀብን አሁን ማን ያስታውሳል። የጎሳ ፀብ ቢሆን ግን ለልጅልጅ ይተላለፍ ነበር። እንንቃ!!!
ከፋፍተን ስናየው 8
ብሄርተኝነት እና የብሄር ፓለቲካ ወደ ዲሞክራሲ፣ ፍትህ እና እኩልነት ይወስደናል? የብሄር ፓለቲካን ህፀፆች ስናስታምም የስንት ንፁሀን ኢትዮጵያውያንን ህይወት እንገብራለን? ስንት ማፈናቀል፣ ስንት ፍረጃ፣ ስንት የጠላትነት ስሜት እናስታምማለን? ህዝባችንን አስተባብረን እንኳን የሚከብደንን ድህነት፣ ኋለቀርነትና ችጋርን መታገል ትተን የዘር ልዪነታችንን ላይ መሰረት አድርገን በጥላቻና በጥርጣሬ ስንጠላለፍ እስከመቼ እንኖራለን?
ብዝሃነትን ለማስተናገድ ብሄር ፖለቲካ ውጪ ሌላ አይነት አደረጃጀት የለም ያለው ማነው? ዋለልኝ መኮንን የተባለ በእድሜም በልምድም በትምህርትም ያልበሰለ የ24 አመት ልጅ ያለምንም የሃሳብ ሙግት የፃፈውን እስመቼ መልሰን መላልሰን መጠየቅ ተሳነን?
ይቺ ሀገር ብዝሃነትን እንድታስተናግድ የብሄር ፓለቲካ ግድ  አይደለም። ማንነትን፣ ባህልን፣ ቋንቋን ከማስተናገድ አንፃር ህገመንግስታዊ ስርዓት መገንባትና የህግ የበላይነትን ማስፈን ይበቃል። በህግ የእኩልነትን መሰረታዊ መርህ በማይናወፅ መሰረት ላይ ከተከልን ብሄርን የሙጥኝ የምንልበት ምንም ምክንያት የለም!
ለህገመንግስታዊነት መዳከምና ለሰብዓዊ መብት መናቅ፣ ለተቋማት መዳከምና ምክኒያታዊነት መጥፋት የብሄር ፓለቲካውና የተካሄደበት መንገድ የአንበሳ ድርሻ አለው። የብሄር መብትን በህግ የበላይነት ካስከበርን የሰው ልጅ ጉዞ ከሀገርና አህጉር እያለፈ ወደ አለማቀፋዊ ዜግነት እየተቀየረ ነው የሚሄደው።
በብሄር ፖለቲካ ምክንያት የደረሰ በደል በብሄርተኝነት መንገድ ማስወገድ ሳይሆን በትክክለኛ መንገድ መመከት ነው ወደ መተማመን፣ መዋደድ እና ወደ ህብረት የሚወስደን።
#ስንገላልበው እና #ለቅመን #ፈትለን #አደባባይ #ስናሰጣው 9
(ይብቃኝ ብዬ ነበር ይህ አርእስት፣ የጃዋር ነገር በአዲስ መልክ እንድቀጥል አደረገኝ) ተቀበል!!!
በጎጥ መሰባሰብ ድክመት ብቻ አይደለም።
በጎጥ የሚሰባሰቡ ሰዎች በመጀመሪያ ደካሞች ናቸው። በራሳቸው እግር መቆም ስለማይችሉ ነው የጎጥ ድጋፍ የሚያስፈጋቸው። ያም ሆኖ ግን በሌላው ላይ ስልጣንን ይፈልጋሉ። በጎጥ የመሰባሰባቸው ዋናው ምክንያትም ይሄው ነው። የነዚህ ሰዎች አደገኛነቱ ግን ጎጡን የሚፈልጉት ስልጣን በአቋራጭ ለመያዝ ብቻ ሳይሆን ጥፋት ሲያጠፉም ከሃላፊነትም ለመሸሽ ነው።ከመጀምሪያውም ከሃላፊነት ለመሸሽ ተዘጋጅተው ስለሚሄዱ የሞራል ገደብ የላቸውም።ለዚህ ነው በጎጥ የሚሰባሰቡ ሰዎች ብዙ ጊዜ እጅግ አስከፊም ወንጀል ለመስራት አይን የማያሹት።
ሃላፊነትን በግላቸው የሚወስዱ ግን በራሳቸው ጥንካሬና ድክመት እንጂ በጎጥ አይመጡም።
በግላቸው ተጠያቂነትን ስለሚቀበሉም ሁሌም የተሻለ ነገር ለማድረግ ነው የሚሰሩት። የሚጥሩት። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ስህተት አይሰሩም ሳይሆን ስህተታቸው ህዝብን ለደጋ አያጋልጥም በተጨማሪም በቀላሉ ይታረማል።
የፈለገ ጥሩ ለብሶ ቢመጣ ማዕረግ አለኝ ቢል፣ መስሃፍ ቅዱስ ወይም ዲግሪ ይዞ ቢመጣ ጎጥን ተደግፎ የሚመጣ ሰው ለሃላፊነት አይበቃም። መታመን የለበትም።
Filed in: Amharic