>
5:13 pm - Tuesday April 19, 0563

ተነግሮ የማያልቀው የነውረኛው በረከት ስምዖን ገመና! (አቻምየለህ ታምሩ)

ተነግሮ የማያልቀው የነውረኛው በረከት ስምዖን ገመና!  
አቻምየለህ ታምሩ
የሕወሓቱ ጆሴፍ ጎብልስ፤ የኢሕአፓው አንበርብርና የሻዕብያው በረከት ሰምዖን ባለፈው ሳምንት በሰጠው ቃለ መጠይቅ  «ጥረት የሚባል  ኮርፖሬሽን  መስርቼ  ለአማራ ሕዝብ ብዙ ነገር ሰርቻለሁ» በማለት እየደሰኮረ ነበር። እውነታው ግን ነውረኛው በረከት ሰምዖን  ኢትዮጵያን ይዟት ገደል ሲገባ የኖረው  የፋሽስት ወያኔ የጭካኔ አገዛዝ ምልክትና በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ሲፈጽሙ የኖሩ ወንጀለኞች አዛዥ እንጂ ተሳስቶም ቢሆን አንድም ቀን  የሕዝብ ወገን ሆኖ አያውቅም።
ከታች የታተመው ታሪካዊ ፎቶ ነውረኛው  ነውረኛው በረከት ሰምዖን ለአማራ ሕዝብ መሰረትሁት ያለው  «ጥረት ኮርፖሬሽን»  አንድ ኩባንያ የሆነው የዳሸን ቢራ ፋብሪካ «ለትግራይ ስቴዲዮም» ማስገንቢያ በአንድ ጊዜ ብቻ  የሰጠውን  42 ሚሊዮን ብር ቼክ የሚያሳይ ነው።
የበረከት ሰምዖኑ ዳሸን ቢራ ፋብሪካ «ለትግራይ ስቴዲዮም»   ግንባታ በአንድ ጊዜ ብቻ 42 ሚልዮን ብር  ሲሰጥ፤ የዳሸን ቢራ ፋብሪካ  መገኛ ለሆነችው  ለጎንደር ግን  አንዳች  ያደረገው ነገር የለም። የጎንደር ስታዲዮምና የእግር ኳስ ሜዳ በረከት ሰምዖንና የወልጀል ግብረ አበሮቹ አዲስ አበባ ከገቡ ጊዜ ጀምሮ አንዳች ለውጥ  አላደረጉም።  ዳሸን ፋብሪካ የሚገኝበት ታሪካዊቷ ከተማ ጎንደር ገጽታም እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ አልተካሄደበትም።  የስምዖን ልክ በረከት  ለትግራይ ስቴዲዮም  ግንባታ በአንድ ጊዜ ብቻ  የሰጠውን ያህል 42 ሚሊዮን ብር  «የአማራ» ለተባለ  ፕሮጀክት አንድም ቦታ ሰጥቶ አያውቅም።
ነውረኛው በረከት «ጥረት ኮርፖሬሽን  የሚባለውን ተቋም መስርቼ  ለአማራ ሕዝብ ብዙ ነገር ሰርቻለሁ» ሲለን የነበረው  «ለትግራይ ስቴዲዮም»   ግንባታና ለሌሎች የሕወሓት ፕሮጀክቶች አማራውን እያለበና እየዘረፈ ሲሰጥ የኖረውን ገፈፋ ነው። ትግራይ ውስጥ በዳሸን ቢራ ስፖንሰር አድራጊነት የተቋቋሙ በርካታ የንግድ ተቋማት አውቃለሁ። በትግራይ የመለስ ዜናዊ «ኤፌርት»  ኩባንያ ስፖንሰርነት ከተቋቋሙ  ድርጅቶች ቁጥር የማይተናነሱ  በበረከት ሰምዖን «ጥረት ኮርፖሬሽን» ስፖንሰር ተደርገው ስራ የጀመሩ ተቋማት አሉ።
ነውረኛው በረከት  ስምዖን ጥረት ኮርፖሬት  ስላሉት መኪናዎችም ብዙ ሲናገር ነበር። እነዚህ መኪኖች የተገዙት  ለአማራ ገበሬ ማዳበሪያ  እንዲያቀርቡ መሆኑንም  ነግሮናል። እፍረተ ቢሱ በረከት ይህን ሲናገር የጥረት መኪኖች ለአማራ ገበሬ ማዳበሪያ በነጻ ሲያራግፉ የኖሩ ያስመስላቸዋል። እውነታው ግን የጥረት መኪኖች  የማዳበሪያ አቅርቦት ገበያውን  በሞኖፖል ተቆጣጥረው  ከገበያ ዋጋ በላይ የአማራን ገበሬ  እያስከፈሉ  ኤፌርትና የትግራይ ባለሀብቶች ከውጭ ለትርፍ የሚያስገቡትን  ገበሬው የማይፈልገውን   የተቃጠለ ማዳበሪያ  በግድ የአማራ ገበሬ  እንዲገዛው እያራገፉ በአማራ ገበሬ ስቃይ ላይ በረከት ሰምዖንና የወንጀል ተባባሪዎቹ ለትግራይ ስቴዲዮም  ግንባታ የሚሰጡትን ገንዘብ ሲዘርፉ የኖሩ የግፍ ቋቶች ናቸው።
የነበረከት መኪኖች ገበሬውን ከማራቆት አልፈው እዳውን መክፈል ያልቻለውን ምስኪን የአማራ ገበሬና  መብታቸው ለመጠየቅ አደባባይ የወጡና ግፍ የወለዳቸውን የአማራ ልጆች  በትግራይ ወታደሮች እየታደነኑና እየተደበደቡ ወደ ማሳቃያ ቤት  የሚጋዙባቸው የጠላት ንብረቶች ሆነው ነበር  ላለፉት አስርት አመታት በአማራ መከካል የኖሩት።
ሌላው በረከት ሰምዖን  ለአማራ  አሳቢ እንደነበር  ማሳያ አድርጎ ያቀረበው  የጥረት ኮርፖሬት አካል የአማራ ብድርና  ቁጠባ ተቋም [አብቁተ] የሚባለውን በሱ የተቋቋመ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ባንክ ከሚያበድረው  ሁለት እጥፍ በላይ  ወለድ  ከአማራ ገበሬዎች የሚሰበስብና ብድሩም በተለምዶ የኤድስ ገንዘብ የሚባልለት ነው። የአብቁተ ብድር የኤድስ  ገንዘብ የሚባለው ብድሩና እዳው  ልክ እንደ ኤድስ ስለማይለቅ ነው። በረከት ሰምዖን ለአማራ አስቦ  እንዳቋቋመው የሚናገርለት አብቁተ በ1997 ዓመተ ምሕረት  ብድር መመለስ ያቃታቸውን የአማራ አርሶ  አደሮች ቤት  «ቅንጅትን መርጣችኋል»  በማለት  የቤታቸውን የቆርቆሮ ጣራ ነቅሎ የወሰደውን  የወንበዴ ድርጅት ነው።
ተነግሮ የማያልቀውን የነውረኛው በረከት ሰምዖን  ጉድ ወደፊት  ከሌሎች  ማስረጃዎች ጋር  በሰፊው እንመለስበታለን!
Filed in: Amharic