>
5:13 pm - Monday April 19, 8934

ለአንዳንድ ኦሮሞ ወገኖቼ!!! (ፋሲልየኔአለም)

ለአንዳንድ ኦሮሞ ወገኖቼ!!!
ፋሲልየኔአለም
“እኔ በመራሁት… እኛ በታገል ነው…” የሚሉት አነጋገሮች ብዙ መዘዞችን እንደሚያስከትሉ ከህወሃት የ27 አመታት የአገዛዝ ታሪክ እንደተማራችሁ አምናለሁ።  ለነጻነታቸው ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉ የኦሮሞ ወጣቶች መኖራቸውን ማንም አይክድም፣ ለእነዚህ ጀግኖች ምንጊዜም አክብሮትን መግለጽ ያስፈልጋል። ይሁን እንጅ አንዳንድ የኦሮሞ ሊህቃን አንዱን ታጋይ ሌላውን ተመልካች እያደረጉ የሚናገሩትን ከፋፋይ ንግግር ባለመቀበል  የእኩልነት ስርዓት የሚፈጠርበትን መንገድ መሻት እንደሚገባችሁ ማስታወስ እፈልጋለሁ። “የእኔነትና የእኛነት” አስተሳሰብ ለምን አደገኛ  እንደሆነ ለማብራራት ልሞክር፦
1ኛ- የኦሮሞ ህዝብ በታሪኩና በባህሉ ስልጣን ተጋርቶና አጋርቶ የሚኖር ህዝብ ነው፤ የገዳ ስርዓት ፍትሃዊ የሆነ የስልጣን ክፍፍል እንዲፈጠር ያደረገ ጥንታዊ ተቋም ነው። ( እንደ ግሪክ ዲሞክራሲ ሴቶችን በማሳተፍ በኩል ያለው እጸጽ እንደተጠበቀ ሆኖ)። በገዳ ስርዓት  አንድ ሰው ገኖ አይወጣም፤ እኔነት የለበትም፤ የሞጋሳና የጉዲፈቻ ስርዓትም በብሄር ኦሮሞ ያልሆነውን  አቅፎ ፣ ለስልጣን እስከማብቃት የሚያደርስ ግሩም ስርዓት ነው። ዛሬ የምንሰማው “ እኔነትና እኛነት” ከጥንታዊው የኦሮሞ ባህል ጋር አብሮ የማይሄድ እንደሆነ ይሰማኛል።
2ኛ- “ እኔነትና እኛነት” በባህሪያቸው አግላይ ናቸው፤ እኔነት እኛነትን ያገላል፤ እኛነት ደግሞ ሌሎችን ያገላል። ለምሳሌ አንድ ሰው “እኔ የኦሮሞን ትግል መርቼ ለውጤት አበቃሁ” ቢል፣ ትግሉን የመሩትን ሌሎችን ሰዎች ያገላል። “እኛ ኦሮሞዎች ትግሉን መርተን ለድል አበቃነው” ቢባል ደግሞ፣ ከኦሮሞ ውጭ ያለው ህዝብ አልታገለም የሚል እንድምታ ይፈጥራል። እኔነትም እኛነትም መገለልን እንጅ አንድነትን አያመለክቱም። የአንድ አገር ዜጎች ሆነን “እኛና እነሱ” የሚል ክፍፍል ከተፈጠረ፣ ሌላው ህዝብ ኦሮሞውን በጥርጣሬ እንዲመለከተው ያደርጋል። የኦሮሞ ህዝብ ደግሞ እንዲህ አይነት ክፍፍል እንዲፈጠር እንዳልታገለ አምናለሁ። የኦሮሞ ህዝብ ድንበር፣ ሃይማኖትና ቋንቋ ሳይገድበው ከሁሉም ህዝብ ጋር ተፋቅሮ የሚኖር ህዝብ መሆኑን አባቶችንና እናቶችን ጠይቆ  ወይም ታሪክ አገላብጦ መረዳት ይቻላል። አሁንም የሚያዋጣው ይኸው “ጋራነታችን” እንጅ “እኔነታችን” ወይም “እኛነታችን” አይደለም።
3ኛ- “እኔነት” የኦሮሞን ህዝብ እርስ በርሱ  እንዲከፋፈል የሚያደርግም ነው። አንዱ “ትግሉን የመራሁት እኔ ነኝ” ሲል፣ በስውር ሆኖ ትግሉን ሲመራው የነበረው ኦሮሞ መቼም ደስ ይለዋል አልላችሁም። እንዲህ አይነቱ አነጋገር በመሪዎች መካከል አላስፈላጊ የሆነ የ“እኔ ነኝ፣ አንተነህ”  ክፍፍል እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህ ደግሞ የኦሮሞን ህዝብ አንድነት የሚሸረሽር ብቻ ሳይሆን ትግሉን የሚያዳክምም ነው። አንድ ምሳሌ ላቅርብ፣ ከወራት በፊት ኦነግ “ትግሉን የምመራው እኔ ነኝ” አለ። የዲያስፖራ አክቲቪስቶች ተናደዱና “ቄሮንማ የምንመራው እኛ ነን “ አሉ። በዚህ የተበሳጩት አቶ ለማ መገርሳ  የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ  ደግሞ የኦሮሞ አክቲቪስቶችንና ታጋዮችን ይበልጥ አስቆጥቶ ነበር። ኦነግ “እኔ ነኝ” ባይል፣ አክቲቪስቶችም አቶ ለማም አይናገሩም ነበር ። ታዲያ ይህ መከፋፈል አይደለም? አሁንም አንዳንዶች “እኔ” ማለታቸውን ካላቆሙ፣ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጅ መሪዎች እርስበርሳቸው መጣላታቸው አይቀርም። ክፍፍሉ የሚያመጣው መዘዝ ደግሞ ከባድ ነው። ህወሃት ይህን ተርድቶ የኦሮሞን ትግል ለማዳከም ሊጠቀምበት እንደሚችል አስቡ።
4ኛ- “ትግሉን የመራሁት እኔ ነኝ” በሚለው ሰው አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች አላስፈላጊ የሆነ የስነልቦና የበላይነት እንዲሰማቸው ያደርጋል። በሌሎች አካባቢ ተወላጆች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ዞኖች በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች መካከል እንኳን  ክፍፍል እንዲፈጠር ያደርጋል። የአርሲ ልጆች “ትግሉ የተመራው በእኛ ነው” ሲሉ፣ የወለጋዎች ደግሞ “አይደለም፣ የትግሉ መሪ የእኛ  ሰው ነው” ብለው ይመልሳሉ። ሸዋዎችም፣ አጋሮችም ተመሳሳይ ክርክር ውስጥ መግባታቸው አይቀርም። ልዩነቱ ደግሞ በስልጣን ክፍፍል ጊዜ ይበልጥ ጎልቶ ይወጣል።  “እኔነት” እንዲቀር  ካልታገላችሁ በመካከላችሁ አላስፈላጊ መከፋፈል ሊፈጠር እንደሚችል አስቡበት። እስር ቤት እያለሁ አንድ የታዘብኩት ነገር ነበር፤ በእስር ቤቱ ውስጥ ታማኞችና የበላዮች አድዋዎች ነበሩ። ከአድዋ ውጭ ያሉት ትግሬዎች ብዙም አይታመኑም ነበር። የእኔነት ስሜት ተመሳሳይ  ነገር ባይፈጥር ከምላሴ ጸጉር ይነቀል። ሳይቃጠል በቅጠል!
5ኛ – “እኔነትና እኛነት” አምባገነንነት ይወልዳል። እኔነት የግለሰብ አምባገነንነትን ፣ እኛነት ደግሞ የብሄር የበላይነትን ይፈጥራል። በዚህ ዘመን ደግሞ ማንም አምባገነንነትንም ሆነ የብሄር የበላይነትን የሚቀበል የለም። የእኔነት መጨረሻው አምባገነንነት ነው። ይህ እንዳይፈጠር ከአሁኑ መታገል ያስፈልጋል።
6ኛ- “እኔ ወይም እኛ ታግለን ባመጣነው … “ በሚለው አነጋገር ጀርባ፣ “ጥቅም” የሚባለው ነገር ተሸሽጎ ይታየኛል። ህወሃትም እኔ በታገልኩት እያለ ነበር የሚዘርፈው፤ አሁንም “የታገለ ልዩ ጥቅም ያግኝ”  ከተባለ አልሸሹም ዘወር አሉ ነው። ሰዎች በችሎታቸውን ሲሾሙ እንኳን “ እኛ ታግለን ባመጣነው እነሱ ተሾሙ” የሚል አደገኛ ቅናት ይፈጥራልና ከአሁኑ ፈር አስይዙት።
በመጨረሻ፣ የዶ/ር አብይና የአቶ ለማ የጋራነት መንገድ እጅግ ተስማሚ በመሆኑ እሱን  እየተከተልን፣ በሰላም፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በብልጽግና የምንኖርበትን አገር እንገንባ።
Filed in: Amharic