>
6:22 pm - Monday May 16, 2022

ኢትዮጵያዊነትን በጠላትነት መፈረጅ ኢትዮጵያዊ አይደለም! (ሃይሉ አባይ)

ኢትዮጵያዊነትን በጠላትነት መፈረጅ ኢትዮጵያዊ አይደለም!
ሃይሉ አባይ
ይድረስ ለ ‘ብሄርተኝነት’ አቀንቃኞች:-
 
ትላንትን ለታሪክ በመተው ለዛሬ ፓለቲካ፣ የሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን ሱሪያችን ከፍ ቀበቷችንን ጠበቅ እናድርግ:: 
ኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያን ጥቅም ከሚያስቀድሙ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ጋር መርህን መሰረት አድርጎ ለጋራ አላማና ሃገራዊ ጥቅም ማበር ነው::
ኢትዮጵያዊነት ልክ እንደ ሃሣብ በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት ነው:: ተቀራርቦ በመስራት የሃሣብ ልዩነትን ማጥበብ ነው::
ሃሣብና ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ናቸው::
ኢትዮጵያዊነት ሲገዝፍ ልቤ በሐሴት ይሞላል:: ኢትዮጵያ ሐገሬ “ያነሰችውና የኮሠሰችው” በጎጠኞችና በጠባቦች የራስ ቅል ውስጥ ብቻ ነው:: ኢትዮጵያዊነት በጎሣ ፓለቲካ አይቀመምም:: በጎጥ ድስት አይቁላላም:: የጎሣ ምንነት በጎና ጥሩ ቢሆንም ኢትዮጵያዊ ማንነት ግን የበለጠና እጅግ ጥሩ ነው::
ማንኛውም ፓለቲከኛ በጥልቀት ማሰብና ማገናዘብን (critical thinking) ባህል ካደረገ፣ ግልፅ የሆነና በስነምግባር የታነፀ፣ ምክንያታዊ፣ ክፍት-አእምሮን ተላብሶና በማስረጃ የተደገፈ አስተሳሰብ ባለቤት የሆነ ፓለቲካና ፓለቲከኛ ከሃሣብ በላይ ሃሣብ ሆኖ፣ ሃሣብና እውነታን በውል ገምዶና አዛምዶ ሲራመድ ከሃሣብ በላይ ገኖ አሸናፊ ይሆናል::
ሃሣብን በነፃነት የማሰብ፣ ሃሣብን ከሌላው የመቀበል፣ በሃሣብ አንድነትና ልዩነት የመከባበር ነፃነትን አለመቀበልና መዋጋትኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው:: ሕግና የሕግ የበላይነት በነገሰበት ዓለም ወንጀልም ነው:: የሠው ልጅ በአስተሳሰቡ፣ በአመለካከቱና በሃሣብ ልዩነቱ የመኮነንና በጠላትነት መፈረጅና የክብር ሥሙን ጥቀርሻ መለቅለቅ ከአለማወቅና ደካማነት የዘለለ ድንቁርና ነው::
ፀረ-ኢትዮጵያዊነትም ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ጥላሸት እየቀቡ በራስ የቀለለና ገለባ በሆነ የራስ ቅል ሌሎችን መመዘን ነው:: ለምሣሌ ትላንት ጣሊያናዊው ጋሊሊዮ ኮንዶምን ሲፈጥር የተቃወመችውና ሲሞትም በግቢዋ እንዳይቀበር ያረገችው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የኮንዶም መጠቀምን ታስተምራለች::
መዘዝና ጦስን ያገናዘበ ፓለቲካ ፍፃሜው ድል ነው:: ስለዚህ የፓለቲካዊ ትግል ቁልፉ ፓለቲካዊ ሕብረት ነው:: የፓለቲካዊ ትግል መንገድ ሕብረ-ብሔራዊነት ነው:: ፓለቲካዊ ሕብረትም በመርህ አንድነት እንጂ በማይታረቅ ሃሣብ ልዩነት ላይ አይገነባም:: ፓለቲካዊ የመስመርና የሃሣብ ልዩነት በድርድር ይጠባል:: በሹኩቻ ግን ይደፈርሣል::
በሃሣብ ሃያልነት አምኖ ሃሣብን እያንሸራሸረ፣ ሃሣብን እየሞረደና እየሣለ፣ በሃሣብ ፍጭትና አሸናፊነት የሚያምንና የሃሣብ ፋብሪካ የሆነ ፓለቲካ ፍፃሜው ያማረና ብቸኛ የድል መንገድ ነው::
እራሱን ያገለለ ፓለቲካ መናኝና የታጠረ የህልም ገዳም ነው:: እራሱን ያገለለ ፓለቲካ ብቻውን የቆሞ ብቻውን የተቀመጠ፣ የራሱን ድምፅ መልሶ የሚሠማ፣ ለራሱ ብቻ የሚናገርና ከእራሱ ጋር ግብግብ የገጠመ ነው:: ይህ የዕብደት መጀመሪያና መጨረሻውም ነው:: ብቻውን የሚከራከር የሚያሸንፈው፣ ብቻውን የሚያለቅስ የሚያባብለው፣ ብቻውን የሚሮጥ የሚቀድመው የለም::
ኢትዮጵያዊ የፓለቲካ ሕብረት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ሕልውና ይበጃል:: ፓለቲካ በራሱ ሕብረ-ብሔራዊ መስተጋብር ነው::
በሐገራችን መከሠት ያለበትን መንግስታዊ ስርዓት ለመወሰን በቅድሚያ መብትና ነፃነት ሊኖረን ይገባል:: ለሕዝብ፣ ከሕዝብና በህዝብ አብላጫ ድምፅ ያልተወሰነን የመንግስት ፓለቲካዊ ቅርፅን ብቸኛ መንገድ በማድረግ በሕዝብ ላይ ለመጫን አንሞክር:: አምባገነንነትም ነው::
የሕዝብን ጥቅም ብልጦች ከእንግዲህ በልተው የሕዝብን መብትና ነፃነት በማፈን በአምሣያቸው የሚቀርፁበት የአምባገነኖች ስርዐት ያረጀና ያፈጀ የገደል አቋራጭ ነው::
የዋለ ያደረ ለቅሶ መርዶ እንጂ ቀብር አይሆንም:: ትላንትን ለታሪክ በመተው ለዛሬ ፓለቲካ፣ የሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን ሱሪያችን ከፍ ቀበቷችንን ጠበቅ እናድርግ::
ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ንብረት ናት!
ኢትዮጵያዊነት ያለ ቀሪ እኩል የምንካፈለው የጋራ ማንነት ነው!
እኔና ቤቴ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነን!
Filed in: Amharic