>
2:28 am - Saturday December 10, 2022

የሚጎረብጡ አንዳንድ የታሪክ “ማስረጃዎች”!!! (ፋሲል የኔአለም)

የሚጎረብጡ አንዳንድ የታሪክ “ማስረጃዎች”!!!
ፋሲል የኔአለም
ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የአገራችንን የፖለቲካ ችግር ከታሪክ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ቢሆንም በታሪክ ዙሪያ በመከራከር ፖለቲካውን መፍታት እንደማይቻል የሚናገሩት  ትክክል ይመስለኛል፤ ሁላችንም ታሪክን  እንደ ፍላጎታችን ከመተርጎም ተቆጥበን ለታሪክ አዋቂዎች ካልተውነው በስተቀር በአገራችን ታሪክ ላይ ተስማምተን ፖለቲካችንንም በዚሁ አንጻር የምንፈታው አይመስለኝም።  ፖለቲካችን ከታሪክ ጋር ለመፋታት አለመቻሉ ስቃያችን እንዲቀጥል ያደርገዋል። ለማንኛውም በእረፍት ጊዜ የምታነቡዋቸው ከመጽሃፍ ያገኘሁዋቸውን ሁለት ነገሮች ላካፍላችሁ።
አጼ ምኒልክ
ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ የደቡብ ኢትዮጵያን መሬት በጉልበት ቀምተው ለእርሳቸው ተከታዮች በማከፋፈል የደቡቡን ህዝብ ጭሰኛ እንዳደረጉት የሚያመለክቱ እጅግ ብዙ የታሪክ መጽሃፍት አሉ። አጼ ሚኒልክ መሬትን እየቀሙ ለተከታዮቻቸው መስጠታቸው እውነት ቢሆንም፣ “ይህን አሰራር የጀመሩት እርሳቸው ናቸው ወይ?” የሚለውን ጥያቄ ስናነሳ መልሱ ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። ለኦሮሞ ህዝብ ያላቸውን ልዩ ፍቅር በመጽሃፋቸው የገለጹትና “ኦሮሞዎች ጥሩ መሪ ቢኖራቸው አፍሪካን ይገዛሉ” በማለት ከ100 ዓመት በፊት በመጽሃፋቸው የገለጹት Father Martial De Salviac, The Oromo በሚለው እና አያሌው ቄኖ በተረጎመው መጽሃፋቸው መሬትን የንጉስ ንብረት ያደረጉት የመጀመሪያው ሰው አጼ ሚኒልክ ሳይሆኑ ከእርሳቸው አንድ መቶ አመት በፊት የኖሩትና ኢትዮጵያን በበላይነት የገዙት የኦሮሞው ጄኔራል ራስ ጉግሳ ናቸው ይላሉ። ጸሃፊው አጼ ሚኒሊክ ራስ ጉግሳ በከፈቱላቸው መንገድ ገብተው የራስ ጉግሳን  አላማ ተፈጻሚ እንዳደረጉ ገልጸዋል። ራስ ጉግሳ በአወጡት አዋጅ እንዲህ ይላሉ “ He ( God) has given it to me, Gugsa! I am the master of the soil; all land exalts me, and it is only I who dispenses it at my will. ..Those who don’t like me flee from my face as of this moment.” ጸሃፊው እንደሚሉት ይህ አዋጅ በኢትዮጵያ ውስጥ ማህበራዊ አብዮት ያስነሳ ነው። ይቀጥላሉ “This Oromo cleared away the ground , traced the path over which rolls, in our time, the triumphant chariot of Menelik II… Menelik II completed the work of the Oromo Gugsa …” እኝህን አማራ ጠል የሆኑና በኦሮሞ ፍቅር የነደዱትን የካቶሊክ ቄስ ለመጥቀስ የፈለኩት፣ አክራሪ ብሄርተኞች አምነው ሊቀበሉት ይችላሉ፣  የኢትዮጵያን ታሪክም እንደገና እንደሚመረምሩ ሊጎነትላቸው ይችል ብዬ በማመን ነው። አክራሪዎች ይህን መጽሃፍ ካነበቡ  በሁዋላ “ሰፋሪ ፣ ወራሪ ፣ መጤ” የሚሉትን ቃላት ለመጠቀም ድፍረቱ ይኖራቸዋል ብዬ አላስብም። እንደዚህ ቄስ አማራን የሚሳደብ ሌላ የካቶሊክ ሚሲዮን አላጋጠመኝም።
ኤርትራና ትግራይ
እውን የትግሬና የኤርትራ የዘር ግንድ አንድ ነው?
በቅርቡ የህወሃት ካድሬዎችና ህወሃትን እንቃወማለን የሚሉ የትግራይ ልጆች ሳይቀር “ ለኤርትራውያን እኛ እንቀርባለን” የሚል ፈሊጥ አምጥተው ነበር። ያው ከቋንቋ ባለፈ የጠቁሰት መረጃ ባይኖርም፣ እኔ ደግሞ አንድ ታዋቂ ምሁር የጻፉትን ልጥቀስና ፍርዱን ለእናንተ ልተው።
ከአጼ ዮሃንስ አራተኛ የሚወለዱት የልኡል ራስ መንገሻ ስዩም የልጅ ልጅ የሆኑት ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴ ገብረስላሴ ስለ ኤርትራ ሃማሴን የዘር ግንድ ሲናገሩ፣ “ በአሃማሴን አፈ ታሪክ ጥንታዊ አባት ምናብ በደንቢያ ይኖር እንደነበር፣ የርሱ ዘር ሚሮኒ ከደንቢያ ወደ ሃማሴን መጥቶ ፍሉቅ፣ አመሉቅ እና ጫሉቅ የተባሉትን እንደወለደና እነርሱም የኤርትራ ህዝብ አባቶች እንደሆኑ ይነገራል።” ይላሉ። ዶ/ር ዘውዴ ይቀጥሉና “ በአክሱም፣ በዛግዌ ዘመንና ከዚያም በሁዋላ ከትግራይ፣ ከቋራ፣ ከደምቢያ፣ ከወገራ፣ ከበለሳ፣ ከላስታና ከጎጃም፣ በአምደ ጺዮን ዘመን ከሸዋም ሳይቀር፣ ለወሰን ጥበቃ ተልኮ በሰራዬ፣ በአከለ ጉዛይ፣ በሃማሴን ሰፍሮ የነበረ ብዙ ሰራዊት እዛው ተዋልዶ እዛው ቀርቷል። ለምሳሌ በሰራዬ ዓዲ መንጎቲ እና ሎጎ ጭዋ፣ ጉዛይ ሎጎ ሳርዳ የሚባሉ ስፍራዎች ለጠረፍ ጥበቃ ከመሃል አገር በተለይም በአጼ ፋሲል ዘመን አካባቢ ሰራዊት የሰፈረባቸው እንደነበሩ በህዝብ ዘንድ ታምኖበት መኖሩ የተረጋገጠ ነው” በማለት ጽፈዋል። ሃማሴን የሚባለው የኤርትራ ህዝብ መነሻው ደንቢያ  ነው ማለት ነው።
ዶ/ር ዘውዴ ይቀጥላሉ– “ የዛግዌ መንግስት በ13ኛው ክ/ዘመን ሲፈርስ ከላስታና ከዋግ የይኩኖ አምላክን መንግስት ሸሽቶ ብዙ ህዝብ ከረን አካባቢ በቢለን ነዋሪ ሆነ። እንዲሁም በብዛት ወደ ሰራዬ መጥተው ከጥንት ጀምሮ ነዋሪ ከነበረው ከአትከመ መልጋ ጋር በመዋሃድ መላ አገሩን አገዎች እንደተቆጣጠሩት በአፈ ታሪክ ይነገራል።” በማለት ብሌን ስለሚባለው ብሄረሰብ ይናገራሉ። ብሌን የሚባለው የኤርትራ ብሄረሰብ አገው ነው ማለት ነው።
ዛሬ እንደርታ የሚባለው የትግራይ ክፍል የተመሰረተው ከሃማሴን በመጡ በደጃዝማች አስበሮም እና በወንድማቸው አርአዶም ነው። (ታሪካዊውን የአምባራዶም ተራራ ያስታዉሷል።) ሃማሴን ደግሞ ምንጩ ደንቢያ መሆኑን ቀደም ብለን አይተናል።
ሌሎቹ የኤርትራ ብሄረሰቦች አፋር፣ ጠልጣል፣ ሳሆና አሳውርታ ፣ ኩናማ ( ባዜን) ናራ ( ባሪያ) ከትግራይ ጋር የሚያስተሳስራቸው የዘር ሳይሆን የንግድ እና የባህል ትስስር ብቻ ነው። ራሻይዳዎች ከ150 አመት በፊት ከአረብ አገር መጥተው ኤርትራ የሰፈሩ ናቸው። በኒ አመሮች ደግሞ ቤጃዎች ናቸው። ፓሌራ የተባለው ጸሃፊ 95 በመቶ የኤረትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ የመጣ ነው ይላል።
የትግራይ ሊህቃን  “ኤርትራና ትግሬ ወንድማማቾች (እህትማማቾች) ናቸው” እያሉ ሌላውን ለማግለል የሚያደርጉት ሙከራ የታሪክ መሰረት ያለው አይመስለኝም። “ትግሬና ሃማሴን አንድ ነው” ቢባል እንኳን ሁለቱም ትግርኛ ተናጋሪዎች ስለሆኑ ትንሽም ቢሆን ታሪክ ያልቀመሰውን ሰው ለማደናገር ይቻል ይሆናል። ዘጠኙንም የኤርትራ ብሄረሰቦች አንድ ላይ ጨፍልቆ “እኛና ኤርትራውያን አንድነን” ብሎ በድፍረት መጻፍ ግን የግንዛቤ ችግር ካልሆነ ሌላ ሊባል አይችልም። ሃማሴንም ቢሆን የዘር ሃረጉ ከደንቢያ  እንጅ ከትግራይ የሚመዘዝ እንዳልሆነ ተወላጆቹ የሚያምኑ ከሆነ ከመቀበል ውጭ  የምናካሂደው ሌላ የዘረ መል ምርመራ የለም።  ዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴን በታሪክ ምንጭነት የጠቀስኳቸው የትግራይ ሰው ስለሆኑ፣ በዛም ላይ የአጼ ዮሃንስ የልጅ ልጅ ልጅ ስለሆኑ፣ ትግሬዎች እንዲያምኑ እንጅ ሌሎችንም ጸሃፍት መጥቀስ ሳይቻል ቀርቶ አይደለም።
Filed in: Amharic