ኢሳት
*በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የዘረፉና ያባከኑ ሰዎች ሜቴክን እየለቀቁና ማእረጋቸውን
እየለወጡ በሲቪል አስተዳደርነት እየተቀጠሩ ነው !
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ሜቴክ በአገሪቱ ውስጥ ላወደመውና ላዘረፈው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ዋና ተጠያቂ የሆኑ የቀድሞ ወታደራዊ መሪዎች ማእረጋቸውን እየተዉ በሲቪል ተቋማት ውስጥ እየተቀጠሩ ነው።
– የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የሆኑት ዶ/ር ሶሎሞነ ኪዳኔ ወደ ከንቲባነት ከመምጣታቸው በፊት የሜቴክ ዋና ተቋራጭ ነበሩ።
– ዶ/ር ሶሎሞን ኪዳኔ የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩ፣ መከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ገብተው ከተመረቁ በሁዋላ፣ ስኮላር ሽፕ ተሰጥቷቸው ወደ አውሮፓ ከተጉዋዙ በኋላ ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጭ በራሳቸው ጊዜ የፒ ኤች ዲ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል። ዶ/ር ሶሎሞን አልትራ ቴክ የሚባል ኩባንያ ከከፈቱ በሁዋላ ከሜቴክ ጋር ያለምንም ጫረታ በርካታ ስራዎችን ወስደው ከፍተኛ ገንዘብ ስብስበዋል። ዶ/ር ሶሎሞን አልትራ ቴክ ኩባንያቸውን ጓደኛቸው እንዲያስተዳድረው በማድረግ ወደ መንግስት ስራ የተመለሱ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ቢሮ ወደ ምክትል ከንቲባነት በፍጥነት ተሸጋግረዋል።
– ሌ/ኮሎኔል አሰፋ ዮሃንስ ከዶ/ር ሶሎሞን ኪዳኔ ጋር ቀጥተኛ የቢዝነስ ግንኙነት ያላቸው የሚቴክን የተለያዩ ኡንዱስትሪዎችን ሲመሩ የነበሩት ከሜቴክ እንዱስትሪዎች አንዱ የሆነውን የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ እንዱስትሪ ስራ አስኪያጅ የነበሩ የኮሎኔልነት ማእረጋቸውን ትተው አቶ ተብለው በሜቴክ የጥቅም አጋራቸው በዶ/ር ሶሎሞን አቅራቢነት በከንቲባው አቶ ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ ሃላፊ ሆነው በመሾም በሜቴክ ከፈጸሙት ከፍተኛ ጥፋት ለማምለጥ ሙከራ እያደረጉ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
ኮ/ል ወይም አቶ አሰፋ ዮሃንስ በኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ እንዱስትሪ ስር የሚገኙትን ሞጆ የሚገኘውን ኬብልና ዋየር ፋብሪካ፣ ታጠቅ የሚገኘው ትራንስፎርመር ፋብሪካ፣ ሰንዳፋ የሚገኘው ሶላር ፋብሪካ፣ መቀሌ የሚገኙት ኢንጂንና ራዲያተር ፋብሪካዎች፣ ሳሪስ የሚገኘው ኮምፓክት ሰብ ስቴሽን፣ እንዲሁም ህዳሴ ግድብ፣ ስኳር ፋብሪካዎች፣ ማዳበሪያ ፋብሪካውንና አዋሽ የሚገኘውን ተርማል በበላይነት መርተዋል።
እርሳቸው የመሩዋቸው ሞጆ የሚገኘው ኬብልና ዋየር ፋብሪካ በችርግ ከመተብተቡም በላይ ታጠቅ የሚገኘው የትራስፎርመር ፋብሪካ ደግሞ አገሪቱን ሊከሳራ ህዝቡን ደግሞ ለምሬት የዳረገ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ከ4 ያላነሱ ትራንስፎርመር አምራቾች ቢኖሩም ፓወር ኢንጂነሪንግ በሞኖፖሊ እንዲይዘው ተደርጎ ለኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን በብቸኝነት ያቀርባል። ሌሎች ኩባንያዎች ያመረቱትን የሚሸጡት በፓወር በኩል ብቻ ሲሆን፣ በዚህ የአየር ባየር ንግድ ከፍተኛ ገንዘብ ተዘርፎበታል።
ሜቴክ የሚሰራው ትራስፎርመር በፍንዳታ ዘይት ማፍሰስ የሚታወቅ ነው። ሰንዳፋ የሚገኘው ሶላር ፋብሪካ፣ ራዲያተር ፋብሪካ እና አዋሳ የሚገኘው ተርማል ፕሮጀክት በየሃገሩ የተጣሉ ፋብሪካዎች ያለምንም ማስረጃ እና ጥናት የተገዙ ሲሆን፣ በእነዚህም ከፍተኛ ገንዘብ እንደተዘረፈባቸው ምንጮች ገልጸዋል። እነዚህ ከፍተኛ የህዝብ ሃብት ፈሶባቸው የተገዙት ፋብሪካዎች አንዱም ስራ አልጀመሩም፤ ቴክኖሎጂው ያረጀ በመሆኑ፣ እቃዎች
ባለሙዋላታቸውና አዋጪም ስላልሆኑ ለወደፊቱም ስራ ይጀምራሉ ብለው እንደማያስቡ ምንጮች ገልጸዋል። መቀሌ የሚገኘው ኢንጂን ፋብሪካም ስራ መጀመር አልቻለም።
እነዚህን ፕሮጀክቶች በበላይነት ያለ ማንም ከልካይነት ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ሲመሩት የነበሩት ሌ/ኮሎኔል የአሁኑ አቶ አሰፋ ዮሃንስ የአዲስ አበባ ቴክኒክ እና ሙያ ቢሮ ሆነው መሾማቸው ግለሰቡን ሆን ተብሎ ከተጠያቂነት ለማዳን የተሰራ ሴራ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
ግለሰቡ በስራቸው ያሉትን ተቋሞች በሙሉ በዘመዶቻቸው ፣ በአካባቢ ልጆችና ከጥቅም ጋር በተገናኘ በመረጡዋቸው ሰዎች እንዲመሩ ማድረጋቸው ለሜቴክ ውድቀት አንዱ ምክንያት ሆኗል። ግለሰቡ ሜቴክ ካፈራቸው የናጠጡ ቱጃሮች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በውጭ አገር አካውንት እንዳላቸው በዚህም ተገምግመው እንደነበር የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል። ሌ/ል ኮሎኔል አሰፋ ዮሃንስ ሰራተኛው አነስተኛ
በሆነ ክፍያ የወር ወጪውን መሸፈን ተስኖት እርሳቸው 4 አዳዲስ ውድ መኪናዎችን በመንግስት ወጪ ገዝተው ይጠቀሙ እንደነበር፣ ባለፉት 7 አመታት በወር አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ወደ ውጭ አገር በመመላለስ ጊዜያቸውን የሚያጠፉ እንደነበሩ የሚገልጹት ምንጮች፣ አሁንም ከዶ/ር ሶሎሞን ጋር በመሆን በአዲስ አበባ መስተዳድር ውስጥ የቀድሞ አለቃቸውንና ወዳጃቸውን የጄ/ል ክንፈ ዳኘውን የጥቅም ሰንሰለት አላማ ለማስቀጠል መዛወራቸውን ይናገራሉ።
ከ500 ያላነሱ ሲቪል ሰራተኞች በሌ/ኮሎኔል አሰፋ ዮሃንስ ለተተኩት አዲሱ ማኔጅመንት በፋብሪካው ይደርስ የነበረውን በደል በዝርዝር ተፈራርመው አቅርበዋል። የሜቴክ አመራሮች በአሁኑ ሰዓት አብዛኛውን ሰራተኛ ያለ ክፍያ ለእረፍት እንዲወጣ በማድረስ ስራ አቁሟል በሚባልበት ደረጃ የደረሰ ሲሆን፣ ድርጅቱን የመከላከያና
ሲቪል በሚል ለመክፈል እቅድ እንቅስቃሴም ተጀምሯል። በጉዳዩ ዙሪያ የአዲስ አበባ ም/ል ከንቲባ ዶ/ር ሰሎሞን ኪዳኔንና ሌ/ኮ አሰፋ ዮሃንስን እንዲሁም ሌሎችንም ባለስልጣናት ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። ግለሰቦቹ የሚሰጡን መልስ ካለ በሚቀጥለው ዘገባችን ይዘር እንቀርባለን።