>

“ሰው መሆናችን ብቻ በቂ ነው፤ ደማችን አንድ ነው!!!” (የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ)

“ሰው መሆናችን ብቻ በቂ ነው፤ ደማችን አንድ ነው!!!”
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ

አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ብሔራዊ እርቅና መተማመን ያስፈልጋል!!!”

* “ላለፉት 27 ዓመታት ከገባንበት መከፋፈል፣ መጠፋፋትና የጨለማ ጊዜ እየወጣን ነው” 
በአለማየሁ አምበሴ
 
ሰሞኑን ከ15 ዓመታት የውጭ አገር ስደት በኋላ ወደ ሃገራቸው የተመለሱት የሰብአዊ መብት ተሟጋቹና የኢትዮጵያዊነት አቀንቃኙ አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ብሔራዊ እርቅና መተማመን ያስፈልጋል አሉ፡፡
አቶ ኦባንግ ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ወደ ሃገር ቤት የተመለሱት በዋናነት የጀመሩትን የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የበለጠ ለማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ላለፉት 27 ዓመታት ከገባንበት መከፋፈል፣ መጠፋፋትና የጨለማ ጊዜ እየወጣን ነው” ያሉት አቶ ኦባንግ፤አሁን የሚታየው ለውጥ የብዙዎች ደም ፈሶ፣ በርካቶች ለአካል ጉዳትና፣ ለስደት ተዳርገው ያመጡት እንደመሆኑ፣ ሁሉም ሰው ለውጡ እንዳይቀለበስ ሊጠብቀው ይገባዋል” ብለዋል፡፡  “ሰው መሆናችን ብቻ በቂ ነው፤ ደማችን አንድ ነው” ያሉት የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ፤ በዘር መከፋፈል ቀርቶ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር መሰባሰብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ “ከገባንበት የጐጠኝነት ፖለቲካ ወጥተን ወደተሻለው አገራዊ አንድነት አስተሳሰብ መሻገር አለብን” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው፣ “ቀጣይዋ ኢትዮጵያ ምን ትምሰል? ምን አይነት ኢትዮጵያን ነው ለአዲሱ ትውልድ የምናሻግረው?” በሚለው ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ማድረግና መወሰንም እንደሚገባ አሳስበዋል – አቶ ኦባንግ፡፡
ከ15 ዓመት በፊት በጋምቤላ ክልል 400 ያህል ሰዎች በግፍ መገደላቸውን በመቃወም ከአገር የወጡት አቶ ኦባንግ፤ በስደት ህይወታቸውም በኢትዮጵያውያን ላይ ሲፈፀሙ የነበሩ በደሎችንና ግፎችን በንቃት እየተከታተሉ፣ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሲያጋልጡ ቆይተዋል፡፡
“የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ” በሚል ያቋቋሙት ድርጅት፤ ከብሔርና ከጐሳ ይልቅ ሰው በመሆንና በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ሁላችንም መሰባሰብ አለብን የሚል አጀንዳ ይዞ ይንቀሳቀሳል፡፡ ድርጅቱ በየትኛውም አካባቢ የተፈፀሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ይጠቁማል፡፡
በሌላ በኩል፤ይሄው የአቶ ኦባንግ ድርጅት፤ “በለውጡ ሂደት ውስጥ የሲቪክ ማኅበራት ሚና ምን መምሰል አለበት’” በሚል ርዕስ፣ የሲቪክ ማህበራትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሚገኙበት ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ውይይት ያካሂዳል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉና ዶ/ር እንዳለማው አበራ በጉዳዩ ላይ ንግግርና ጥናታዊ ጽሁፍ እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡
Filed in: Amharic