>
4:42 pm - Wednesday January 18, 1595

በአዲስ ዘመን ዉጋጋን፤ ዘመናት የማይሽሩት ምስጋና!! ይድረስ፤ ለደራሲ፣ፖለቲከኛ፣ አክቲቪስትና ጋዜጠኛ፣ ኤርምያስ ለገሰ ዋቅጅራ  (ሃራ አብዲ)

በአዲስ ዘመን ዉጋጋን፤ ዘመናት የማይሽሩት ምስጋና!!

ይድረስ፤ ለደራሲ፣ፖለቲከኛ፣ አክቲቪስትና ጋዜጠኛ፣ ኤርምያስ ለገሰ ዋቅጅራ

(ሃራ አብዲ)

 

በጣሙን ለማደንቅህ፣ በስራዎችህ አስተሳሰቤን ላነጽከዉና በሙሉ ልብ ከተሰጡ ማንኛዉንም ጉዳይ ከግብ ማድረስ እንደሚቻል አብዝተህ በባህሪህ ያስተማርከኝ ታላቅ ሰዉ፤ ኤርምያስ ለገሰ፤ እንኩዋን ለአዲሱ አመት እግዚአብሄር ከነቤተ-ሰቦችህ በሰላም አደረስህ!

የዛሬዉ ጽሁፌ ራሱን ችሎ የሚቆም ሳይሆን የጥሪ ወረቀት ተደርጎ ይቆጠርልኝ።

በ ሀገራችን ዉስጣዊ የፖለቲካ ግንዛቤ ረገድ፤ የብዙ ሺሆችን አይን የገለጠዉን የኤርምያስ ለገሰ ዋቅጅራን ስራዎች (የህትመት ስራዎቹንና አሁንም የሚሰጠዉን አገልግሎት) ለማድነቅና እርሱንም ለማመስገን የምንችልበትን መንገድ ሳስብ ብቆይም፤ እስከአሁን ድረስ ተግባራዊ ሳላደርግ ቆይቻለሁ።

ይህ በእንዲህ እያለ፤ መስፍን የተባለ ወገናችን( በግል አላዉቀዉም) በፊስ ቡክ ላይ ኤርምያስን ሰለብሬት ማድረግ እንደሚገባና እስካሁን ስለኤርምያስ የተባለ ብዙ ነገር አለማየቱን በመግለጽ ያሰፈረዉን አስተያየት ስመለከት የኔም ሃሳብ አገረሸብኝ።

በዚህ ጽሁፍ መክፈቻ፤ በዉስጤ የነበረዉን ሃሳብ፤ እርሱ ከሃሳብነት አዉጥቶ በፌስ ቡክ ላይ ለታዳሚ በማቅረቡ እኔም ሃሳቤን እንዳጋራ ስሜቴን ጫር ያደረገዉን መስፍንን ( ሙሉ ስሙን አልያዝኩምና ይቅርታ) በጣም ላመሰግንና ሃሳቡን ወደ ፊት በማምጣቱ እዉቅና ልሰጠዉ እፈልጋለሁ።

መስፍን ይህን ጽሁፍ ካነበብክ፤ የበኩልህን ሃሳብ ታጋራን ዘንድ እጋብዝሃለሁ።

እንግዲህ ኤርምያስን «እንዴት ባለመልኩ እናመስግነዉ» ብዬ ሳስብ የተሰማኝ እንዲህ ነበር።

በተለያዩ ድረ-ገጾች ላይ በተመሳሳይ ጊዜያት፤ ለምሳሌ፤ ለሶስት ተከታታይ ቀናት  ወይንም ሳምንት ለሚሆን ጊዜ:- 

 –መጽሀፎቹን ያነበብን፣

 –በኢሳት ቴሌቭዢንና ሬዲዮ ስራዉ በሚያቀርባቸዉ ተወዳጅ ዝግጅቶቹ የምናደንቀዉ፣

ከሌሎች የህወሃት ስርአት ቤተኞች እጅግ በተለየ መልኩ የሀገሩ ጥቃት ያንገበገበዉ መሆኑን የተረዳን ወገኖች

አድናቆታችንን የምንቸርበትና ኤርምያስም የሚበረታታበት  መድረክ መፍጠር ቢቻል፤ የሚል ነበር።

(የምንሸልመዉም ነገር ካለ በሙሉ ልብ እተባበራለሁ። የድረ-ገጽ ክፋቱ፤ ለሰርፕራይዝ አለመመቸቱ ፦)

ከሶስት ቀናት እስከ ሳምንት ጊዜ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ያሰመርኩበት ደግሞ፣ እንደሚታወቀዉ የሀገራችን ሁኔታ በፍጥነት መለዋወጡን ተከትሎ ብዙ ትኩረት በሚስቡ ነገሮች በተለያየ አቅጣጫ መሳብ (scattered መሆን) ስላለ፣ አድናቂዎቹ እድል እንድናገኝ በማሰብ ነዉ።  

የተሻለ ሃሳብ ያላችሁ ብትገልጹልኝ በደስታ እቀበላለሁ።

ኤርምያስ ለገሰን የማመስገን ፤ስራዎቹን የማድነቅና የዚህን ታላቅ ጀግና ዝና ላልሰማዉ የማሰማት ሃላፊነት፤ የሚሰማን ኢትዮጵያዉያን እንደተመቸን ከያለንበት እንንቀሳቀስ!  የተለያዩ ድረ-ገጾችን፤ ዩ-ቲዩብ ቻናልና ፌስ ቡኩን ሁሉ ከዛሬ ጀምሮ በምስጋና እናጨናንቀዉ!!!!!

ትኩረታችሁ አብሮኝ እንዲዘልቅ ቶሎ ብዬ «ወደ ገደለዉ ልግባ» ኤርምያስ ለእኛ ማነዉ?

የተለያዩ ግለሰቦች ብዙ አስደናቂ ተጋድሎዎች ያደርጋሉ። ኤርምያስ ያደረገዉን የሚያደርጉ ግን በጣት የሚቆጠሩ ብርቅዬዎች ናቸዉ። ፍላጎቴ የአንዱን አስተዋጽኦ በማግነን የሌላዉን ማሳነስ አይደለም። እዚህ ላይ ማሳየት የምፈልገዉ ፣ኤርምያስ፤ የኢህአዴግ ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ ሆኖ በስልጣን ወንበር ላይ ተቀምጦ በነበረበት ወቅት፣ እንደማንኛዉም ባለ ጊዜ «ጸባዩን አሳምሮ» ከፍተኛ የስልጣን መሰላል ላይ ለመንጠላጠልና ሃብት ለማጋበስ ሲችል ተቃራኒዉን የመረጠ ልባም የሀገር ባለ ዉለታ ነዉ። ረዘም ላለጊዜ ራሱን ሰጥቶ፤ መረጃ በመሰብሰብ፣በስራዉ ምክንያት ከሚያገኛቸዉ በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ከሚገኙ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር የሚያደርገዉን የስራ ግንኙነትም ይሁን የግል መዝናኛ ጊዜዉን የትግራይ ነጻ አዉጭዎቹን ደባና ሸር ፈልፍሎ ለማዉጣት እና ሀገሩን ከመዳፋቸዉ ለማስለቀቅ ህዝባችን ለሚያደርገዉ ትንቅንቅ ወደር የማይገኝለት ስራ ለመስራት ተጠቅሞበታል። የሀገሩን ገዳዮች ዱካ እየተከተለ ግዳያቸዉን በማስረጃ አስደግፎ ለኢትዮጵያ ህዝብ ግንዛቤ ያስጨበጠ ጀግናችን ነዉ!! እዉነት ነዉ ።በሚሰሩት ስራ መቀጠል ሳይችሉ እየቀሩ ወይንም ወያኔ በአንድም በሌላም ምክንያት ጭዳ ሊያደርጋቸዉ ሲያስብ «እግሬ አዉጭኝ» ብለዉ በስደት የሚኖሩ ፤ወያኔ በሀገራችንና በህዝባችን ላይ የጻፈዉን የሰቆቃ መድብል አንድ፤ሁለት ብለዉ መቁጠር የሚችሉ እጅግ በርካታ ግለሰቦች የመኖራቸዉን ያህል፤ የሚያዉቁትን እስካሁን ለህዝብ ይፋ ያላደረጉ «ጎመን በጤናዎች» ሞልተዋል ።ኤርምያስ «የመለስ ትሩፋት፤ ባለቤት አልባ ከተማን»ና «የመለስ ልቃቂት»ን ለመጻፍ ያሰባሰባቸዉ ሰነዶች፣በሰንጠረዥ የተደገፉ ማስረጃዎችና ጭንቅላት የሚያዞረዉ የዘረኞቹ አረመኔነት የተገለጠባቸዉ የግድያና የዘረፋ ዶክመንቶች በሆነ አጋጣሚ በእጁ ላይ እንዳሉ በወያኔዎች መረብ ወድቆ በነበር፤ ምን ሊያደርጉት ይችሉ ይሆን?የሚለዉን መጻፍ ቀርቶ አላስበዉም! ይህ ግንዛቤ ብቻዉን ኤርምያስን ብዙ የሰራ ግን ጥቂት የተነገረለት ጀግና (unsung hero) ያደርገዋል። ኤርምያስ የነበረዉ አደጋ «risk» ሳይጠፋዉ ፤ሆኖም እጅግ ተጠንቅቆ ከእንቁ የከበረዉን መረጃ በእጃችን አስገብቶአል ። ከእንግዲህ፤ ማንም ሀገራችንን እንደፈለገዉ ጨቁኖ፤ ህዝባችንን እያሰረና እየገደለ በላያችን ላይ አይነግስም።የዲሞክራሲ ስርአት በሀገራችን እንዲገነባም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ተማምለን በአንድነት እንድንቆም በእዉነትና በእዉቀት አስታጥቆናል።  ኤርምያስ፤መስማት፤ማንበብና መረዳት የነበረብንን የአፓርታይዱን አገዛዝ ክርፋት እንድንረዳ አይንና ጆሮአችንን የከፈተ የነጠረ ፖለቲከኛና  ባለ ወርቅ ብእር ደራሲም ነዉ። «የመለስ ልቃቂትን ካነበብኩ በሁዋላ፤ እንደ ቀድሞዉ መሆን አልተቻለኝም። ለኤርምያስ በትህትና የምሰጠዉ አንድ ሁለት  አስተያየት ቢኖር (ተምኔዉ ካመስጋኝነት ወደ አማከሪነት አትበሉኝና)

1, የመለስ ልቃቂትን ከልሰህ «የኢትዮጵያ ፖለቲካ 101, የህወሃት አፓርታይድ አገዛዝና ለትዉልድ ያተረፈዉ ጠንቅ» የሚል የመማርያ መጽሀፍ በማድረግ በከፍተኛ የትምህርት ተቁዋማት ዉስጥ በካሪኩለም ተቀርጾ መጭዉ ትዉልድ እንዲማርበት ከመንግስት ጋር እንድትወያይበት።( እንኩዋን ይህ ለልባችን የቀረበዉን አንድ ትዉልድ የበላ በአንድ አናሳ ቡድን  የተፈጸመብን ሰቆቃ ይቅርና በአጋም በቀጋ የማይዘመዱንን የነሌኒንና የነማኦን ፖለቲካ በግድ ስንጋት ኖረናል)

2, መጽሀፍትህን ያላነበቡ እጅግ በርካታ ዜጎች ይኖራሉ። ሀገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በመጽሀፍቱ ዉስጥ የሰፈሩትን እዉነታዎች ማወቅና ለበቀል ሳይሆን መጭዉን ጊዜ የተሻለ ለማድረግ የዜግነት ድርሻዉን ሊወጣበት እንዲችል በትረካ መልክ በመገናኛ ብዙሃን፤ በድረ-ገጽ ቢለቀቅ የሚል ነዉ።

የዛሬዉ ጽሁፌ ራሱን ችሎ የሚቆም ሳይሆን የጥሪ ወረቀት አድርጋችሁ ቁጠሩት ያልኩት በአግባብ ነዉ። ኤርምያስ ለገሰን የማመስገን ፤ስራዎቹን የማድነቅና የዚህን ታላቅ ጀግና ዝና ላልሰማዉ የማሰማት ሃላፊነት የሚሰማን ኢትዮጵያዉያን፤ እንደተመቸን ከያለንበት እንንቀሳቀስ!  የተለያዩ ድረ-ገጾችን፣ ዩ-ቲዩብ ቻናልና ፌስ ቡኩን ሁሉ በፍቅርና በምስጋና እናጨናንቀዉ!!!!!በአዲስ ዘመን ዉጋጋን ፤ዘመናት የማይሽሩት ምስጋና ብዙ ላልተዘመረለት ጀግናችን ለኤርምያስ ለገሰ ዋቅጅራ ይድረሰዉ!!!

ብርሀናቸዉ ጋራ ያዞረንን፣ የወገን ስቃይና የሀገር አይሆኑ መሆን እንደ እግር እሳት የሚያቃጥላችዉን ዉድ ወገኖቻችንን የማከባበርና ዉለታቸዉን የማንረሳ መሆናችንን የመግለጽ ባህል ማዳበር ጀምረናልና የቻላችሁ ሁሉ ያለመቆጠብ ኤርምያስን ለማመስገን ብእራችሁ ይፍጠን ስል በትህትና እጋብዛችሁአለሁ።  

ለኤርምያስ የግሌ ምስጋና ገና «u» ብሎ ጀመረ!!

እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና ህዝብዋን ይባርክ። እንደ ኤርምያስ ያሉ ጀግኖች ይብዙላት!

መልካም አዲስ አመት!!!

ሃሳብና አስተያየታችሁን ልትለግሱኝ ለምትፈልጉ hara.abdi@gmail.com በሚለዉ የኢ-ሜይል አድራሻዬ እገኛለሁ።

 

Filed in: Amharic