* እነ ኡስታዝ አቡበከር ላይ ወንጀል የፈበረኩት….
* ደመቀ መኮንን ለማጥመድ የተጣለው መረብ
ይህንን ጽሑፍ ዛሬ የማዘጋጀቴ ሰበብ ወንድማችን ኡስታዝ አቡበከር፣ ከአርቲስት ታማኝ በየነ ጋር በመሆን ደሴ ከተማ ላይ በመገኘት ንግግር በማድረጋቸው ነው፡፡ ዓቢይ ምክንያቹን ግን መጨረሻ ላይ አስቀምጫለሁ፡፡ በጢጣው ኮሌኔል እንጀምር፡፡
-አንድ-
እስከ 2003/4 ዓ.ም. (በትክክል ባላስታውሰውም) ድረስ ዋና ተልእኮው ግጭት መፍጠር የሚመስል ተግባር ውስጥ የተሰማራ አንድ ኮሌኔል ነበር፡፡ ጢጣ የወታደር ካምፕ ውስጥ የሚኖር፡፡ አሁን የወሎ ቴሪሼሪ ኬር ሆስፒታል የሚሠራበት፡፡ ይህ ሰው የምሥራቅ አማራ (ከአፋር ክልል የተወሰኑ ዞኖችን ጨምሮ) የብሔራዊ ደኅንነት ተጠሪም ኃላፊም ነበር፡፡ አብረውት የሚሠሩ በመከላከያ ሥር የነበሩ የደኅንነት ሠራተኞችም ነበሩ፡፡ ብዙ ጊዜ አይስምሙም ነበር አሉ፡፡
ይህ ኮሌኔል ውስኪ ከመጠጣት እና ካራምቡላ ከመጫወት ባለፈ ዋና ተልእኮው የሚመስለው ለዘመናት አብሮ፣ ተዋዶ፣ ተፋቅሮ የኖረውን የደሴን ሙስሊምና ክርስቲያን ማጣላት ነበር፡፡ የብዙ ሙስሊም ዑለማዎችን ቤት፣ ሱቅ፣ ይገኙበታል የተባለን አድራሻ እያንኳኳ ብዙ ነገር ለመሸረብ ሞክሯል፡፡ እንደው አብሮ አደግ፣ ጎረቤት ክርስቲያን ወንድምና እህት ጋር ለማጋጨት ብዙ ጣረ፡፡ በዚህ በኩል ምንም ጠብ ሳይልለት ቀረ፡፡ አልተሳካለትም እንጂ!
የዞኑን እና አንዳንድ የከተማውን አመራሮችን ስም በመጥቀስ ለብዙዎች መጥፎ መጥፎ ዜና ነዛ፡፡ የሃይማኖት ግጭት ለመቀስቀስ፡፡ የዞኑን አስተዳደሪ (የአሁኑ የኢቢሲ ሥራ አስኪያጅ) የሚሊኒየሙ መጥፎ መሪ አስብሎ ደብዳቤ አስጽፎ ወደ ክልል አስላኳል፡፡ ለነገሩ አስተዳዳሪው በክርስቲያኑ ሕዝብም ዘንድም ቤተክርስቲያኑን እንዳይሠራ አድርገዋል በሚል የተጠሉ ነበሩ፡፡ ምናልባት ይሄንንም ቅስቀሳ ያደረጉባቸው ይመስለኛል-የጢጣው ቡድን፡፡ ከሁለት ያጣ ጎመን ሆኑ፡፡
በወቅቱ የክልሉ የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደግሞ አቶ ከበደ ጫኔ ነበሩ፡፡ ሁኔታውን ያውቁ ነበር አሉ፡፡ የሆነው ሆኖ የጢጣው ኮሌኔል ባሰበውና ባቀደው ልክ ባይሆንም የተወሰነ ግጭት ተፈጠረ፡፡ ግጭቱን የደሴ ከተማ ነዋሪ አይረሳውም፡፡ የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን መቃረቢያ የሚሆን ከከተማው በስተምሥራቅ በኩል አዝዋ ተራራ ላይ ተሠራ፡፡
በወቅቱ በተፈጠረው የሙስሊምና የክርስቲያን ግጭት ቤተክርስቲያኑም ሳይሠራ ቀረ፡፡ የሰው ሕይወትም ጠፋ፡፡ ለሚሊኒየሙ መታሰቢያ የሚሆን የከተማው መስተዳድር ያሠራው፣ ደሴ ፒያሳ ላይ ሊተከል የነበረው የንጉሥ ሚካኤል ሀውልትም ሳይተከል ቀረ፡፡ ተንታ ተተከለ፡፡ ይባስ ብሎም ከፒያሳ እስከ አራዳ ጫፍ አይጠየፍ መታጠፊያ ድረስ የነበረው ንጉሥ ሚካኤል ጎዳና የሚለው ተለውጦ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ጎዳና ተባለ፡፡ እንግዲህ የአርሴማ ቤተክርስቲያንም ጉዳይ፣ ሃውልቱም፣ የጎዳናውም ሥያሜ ሦስቱም ከንጉሥ ሚካኤል ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ንጉሡ፣ ክርስቲያን ከሆኑ በኋላ የአካባቢው ሙስሊሞችን ስለበደሉ የከተማውን ሙስሊምና ክርስቲያን ለማጋጨት የማቀጣጠያ ችቦ (ክብሪት) እንዲሆኑ የጢጣው ቡድን ሌት ከቀን ጣረ፡፡ ተልእኮዉን ሲጨርስ፣ ኮሌኔሉ ከዚያ አካባቢ ተነስቶ ወደ አፋር ከተዛወረ፡፡
በዚያን ወቅት ደሴ ከተማ የነበሩ አንዳንድ የጸጥታና የፖሊስ አመራር አሁንም እዚያው አሉ፡፡ በወቅቱ እንደዚያ ዓይነት ችግር ሲፈጠር የማን አባት ገደል ገባ ከማለት ያለፈ በጎ ተግባር የሌላቸው፡፡ ምናልባትም አብረው አቀናባሪ ባይሆኑ ነው? አንድ መረጃ ሰብሳቢ የነበረ ዘመዴ ሁኔታዉን በሚመለከት ደሴ ፉርቃን መስጂድ ያየዉን ታዝቦ እንዲህ ብሎኝ ነበር፡፡ ቃል በቃል ለመጥቀስና “አይ ‘ቲቸር’ ምርቅና መረቁ ተደባልቆ ምኑ ይለያል?” ነበር ያለኝ፡፡ ጎልማሳና ዘመዴ ቢሆንም መምህሩም ስለነበርኩ ነው-‘ቲቸር’ ማለቱ፡፡
(በአጋጣሚ እኔም ጉዳዩን በቅርበት እከታተለው ነበር፡፡ ለመከታተሌ ዋና ምክንያቱ ደግሞ ነፍሱን ይማረውና ወዳጄ ብርሃኑ ገበየሁ ዶክትሬት ዲግሪውን የሚሠራው “Trajectories of Tolerance” በሚል ርእስ በተለይም የሃይማኖት መቻቻል ሆኖ የሚያጠናውም ወሎን ነበር፡፡ በወቅቱ እየሆነ የነበረውን ጉዳይ በስልክም በአካልም እንወያይ ስለነበር ነው፡፡ ብርሃኑም በወቅቱ ትንሽም ግጭት ቢፈጠር እንኳን ደሴ ይመጣል፤ አብረን ሁኔታዎችን እንከታተላለን፤እንወያያለን፤እንጨቃጨቃለን፡፡)
-ሁለት-
በሙስሊምና ክርስቲያኑ መካከል ከላይ የቀረበውን ሴራ ካለቀ በኋላ ከእንደገና ሌላ ወጥመድ ተዘረጋ፡፡ ሙስሊሙን ኅብረተሰብ መከፋፈል፡፡ በመካከሉም ግጭት መፍጠር፡፡ አህባሽ በኋላ ሼህ ኑሩ ከሸዋበር መስጊድ ሲመለሱ ተገደሉ፡፡ የግዲያውን ዘጋቢ ፊልም አሁን የተዘጋው ኢኤንኤን (ENN) ቴሌቪዥን ፈቃድ ተሰጥቶት የነበረው ሰው ደሴ መጥቶ አዘጋጀ፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ተላለፈ፡፡
አሳዛኙ ነገር የጢጣው ኮሌኔል በየቤታቸው ሌት ከቀን ሲመላልስባቸው የነበሩት ሙስሊም ወንድሞቻችን ኋላ ላይ እንዲሁ በሐሰት ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ኮሌኔሉ ምን ምን እንዳደረገ፣ ምን እያወራ ማን እንዲታሠር እንዳደረገ አይታወቅም፡፡ አንዳንዱ ሴረኛ የሚደግፍ መስሎም ለወንጀል ክስ የሚሆን ድርጊት ያቀነባብር ይሆናል፡፡ በአገራችን ምን ያልተሠራ መንግሥታዊ ድራማ አለ? ሁለቱን ብቻ ላንሳ፡፡
አንዱ አቶ ደመቀ መኮንን ይመለከታል፡፡ ኢሕአዴግ፣ እንደ መንግሥት ሃይማኖታዊ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንደመታቀብ አሕባሽ የሚባል ቡድንን ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ወሀቢያ የሚል ቡድን በሐሳቡ በመሳልና በመፍጠር የእስልምና እምነት ተከታዮችን በግልጽ የመከፋፈል ድርጊት ውስጥ ገባ፡፡ ለነገሩ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትንም እንዲሁ ሞክሯል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን አክራሪና ጽንፈኛ ቡድን ነው በማለት ከሲኖዶሱ ጋር ለማጋጨት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ፓርቲው በወቅቱ ያወጣቸው የነበሩትን “አዲስ ራዕይ” የሚባሉ የፓርቲው ርእዮተ ዓለም መጽሔቶችን መመለከት ይበቃል፡፡
ለማንኛውም ደሴ ከተማ አካባቢ ላይ ከፍተኛ የወሀቢይ መዋቅር እንዳለ ተወራ፡፡ እንደውም የሽብር ድርጊትም ውስጥ እንደተሰማራ በሰፊው ተለፈፈ፡፡ አሸባሪዎችme አፍጋኒስታን ድረስ ተልከው እንደሰለጠኑ ተነገረ፡፡ ይባስ ብሎም ወረሂመኖ፣ከኮሬብ ወደ በሽሎ ወንዝ ገደማ፣ አቶ ደመቀ መኮንን ድጋፍ የሚያደርጉለት ‘ሙጃሂዲን’ ሥልጠና እንደሚያደርግም ውስጥ ለውስጥ ወሬ ተነዛ፡፡
በመቀጠል ከሼህ ኑሩ ግዲያ ጋር በተያያዘ የአቶ ደመቀ መኮንንን የቅርብ ዘመድ ናቸው የተባሉ የመቅደላ ፋርማሲ ባለቤት ታሰሩ፡፡ በእኔ ግምት የታሰበው የሚመስለኝ፣ ከስም ማጥፋቱ ባለፈም አቶ ደመቀ በወቅቱ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ኋላም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ስለሆኑ ዘመዳቸው የተባሉትን ሰውዬ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው አንድ ነገር ቢሉ/ቢያደርጉ ከወጥመድ ለማስገባትም የተሸረበ ሴራ ይመስላል፡፡
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው አቶ ደመቀ መኮንን ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ በግጨው ጉዳይ የሕዋሃት ጥርስ ዉስጥ መግባታቸው ነው፡፡ በዚህን ዓመት ከክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድርነት ወደ ፌደራል መጡ፡፡ በዚሁ ዓመት አቶ አባይ ጸሐዬ ከሱዳን ጋር ያለውን ድንበር የተፈራረመበት ስለሆነ “አቶ ደመቀ ለሱዳን መሬት ሽጠዋል” የሚለው ወሬም መነዛት ተጀምሯል፡፡ የሴራው ድራማ ቀጥሎ አቶ ደመቀ ክርስቲያኖችን የሚያጠፉ፣ አገርን የሚያወድሙ ጽንፈኛ ሙጃሂዲኖችን ለማሰልጠን ድጋፍ ያደርጋሉ ማስባል ተጀመረ፡፡ ዘመዳቸውም ከሼህ ኑሩ ግዲያ ጋር ተያይዞ ታሰሩ፡፡
-ሦስት-
በወቅቱ ከተፈጹሙት ድራማዎች ሁለተኛው ደግሞ እነ ኡስታዝ አቡበከርን የሚመለከት ነው፡፡ በጢጣው ኮሌኔል የሚመራው የደኅንነት ቡድን ሰላምና ጸጥታ እንዲኖር በተዋቀረ መሥሪያ ቤት ሥር ሆኖ ተልእኮው ግን ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ በሕዝብ ውስጥ ዉጥረት ማስፈን እንደነበር ከላይ ተገልጿል፡፡ ነገሩ ልክ ጆርጅ ኦርዌል፣1984 ፣ በሚለው ልቦለዱ ዉስጥ እንደሳለው “የሰላም ሚኒስቴር” ተብሎ በአገሪቱ ኦሺኒያ፣ በገዥው ፓርቲ ‘ቢግብራዘር’ የተቋቋመው መሥሪያ ቤት ዋና ተልእኮው ጦርነት ማወጅ እንደሆነው ሁሉ የዚህ ኮሌኔል ተልእኮም ያው ነበር፡፡
ኮሌኔሉ ከአካባቢው ከለቀቀ በኋላ ኢሕአዴግ አህባሽና ወሐቢያ የሚል የሐሳብ ቡድን ፈጥረ፡፡ ወሃቢያ ያላቸውን አሸባሪ አላቸው፡፡ እውነታው ግን፣የኢሕአዴግ ከፍተኛ ሹማምንትም ጭምር የሚያውቁት፣ እነ ኡስታዝ አቡበከር (በአጠቃላይ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው) ቅንጣት ታክል እንኳን ወንጀል አለመፈጸማቸውን ነው፡፡
እንደውም ለእነዚህ ሹማምንት ራስ ምታት የሆነባቸው የኮሚቴው ፍጹም ሰላማዊ መሆን እና ምን ዓይነት ወንጀል ላለመሥራት የሚያደርገው ጥንቃቄ ነበር፡፡ ወንጀል ሲጠፋ መንግሥት የወንጀል ድርጊት በራሱ አዘጋጅቶ እነሱ እንደፈጸሙት በየሚዲያው አስተጋባው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ እንጥቀስ፡፡
አንዱ፡- ኮሚቴው ከአረብ አገር (ከሳዑዲ አረቢያ ይመስለኛል?) ሰው አስመጥቶ ስለ አክራሪነትና ሽብር ለማስነሳት ቀስቃሽ ወረቀቶችን መርካቶ አኑዋር መስጊድ ሲበትን ተይዞ የእለቱ እለት ማታ ወደ አገሩ እንደተላከ (deport እንደተደረገ) መንግሥት ያሠራጨው ዜና ነው፡፡
እርግጥ ነው አንድ ሰው ከዉጪ መጥቶ ወረቀት በትኗል፡፡ እርግጥ ነው ተይዞ የዚያው ቀን ማታ ወደ አገሩ ተልኳል፡፡ ምሥጢሩ ግን ሌላ ነው፡፡ ሰዉየውን ያስመጡት እነ ኡስታዝ አቡበከር ሳይሆኑ መንግሥት ነበር፡፡ መንግሥት አስመጣው፤ መንግሥት ወረቀት እንዲበትን አደረገው፡፡ መንግሥት ማታ ላይ በአውሮፕላን አሳፍሮ በሰላም ወደ አገሩ ላከው፡፡ አበቃ፡፡ እዉነቱ ይሄ ነው፡፡ ለእነ ኡስታዝ አቡበከር አንድ ወንጀል ተፈጠረላቸው ማለት ነው፡፡
በነገራችን ላይ ከዚህ ድራማ አቀናባሪ ይልቅ ማንም ጀማሪ ጸሐፊ የተሻለ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለዉም፡፡ ወንጀል ሲፈጽም የተያዘ፣ለዚያዉም ወንጀሉን ብቻ ለመፈጸም ከሌላ አገር የመጣን ሰው ወደ አገሩ አይላክም፡፡
መንግሥት የፈጠረውን ሁለተኛውን ወንጀል እንመልከት፡፡ አርሲ፣አሳሳ ላይ የተፈጸመውን፡፡ መንግሥት የሆኑ ሰዎች ፖሊሶች ላይ ተኩስ በመክፈት ፖሊሶችን ገድለዋል በማለት ሰዎችን ገደለ፤አሰረም፡፡ እዉነታው ግን መንግሥት ሰበብ ፈጥሮ የገደላቸው ሰዎች እንጂ የሞተ ፖሊስ አለመኖሩ ነው፡፡ እንደሞቱ የተወራዉ የፌደራል ፖሊሶች ናቸው፡፡
ፕሮፓጋንዳው በአካባቢው ስለነበረው ሁኔታ ቀድሞ መረጃ የደረሰዉ የፌደራል ፖሊስ በአካባቢዉ በመገኘት የወንጀል መከላከል ሥራ ዉሥጥ እንደተሰማራ ወንጀል ለመፈጸም የተዘጋጁ ሰዎች በተኮሱት ጥይት የፌደራል ፖሊሶች ሕይወታቸው እንዳለፈ ግጭቱ ተፈጠረ በተባለበት ቀን ማታ ላይ በዜና ተነገረ፡፡ የአካባቢዉ ሰውም የሞተው የፌደራል ፖሊስ (ከአዲስ አበባ የሔደ) ነው ስለተባለ ሞቶ የቀበሩት ፖሊስ የለም፡፡ እነ አቡበከር ግን ተከሰሱበት፡፡
( በአሳሳዉ ድራማ የሞተ የፌደራል ፖሊስ ካለ፣ ስሙንና አድረሻዉን፣ እስኪ እንደዉ ጠቁሙኝ? የመረጃዉንም ተአማኒነት ለማስተባበልም ሆነ ለማጠናከር ይረዳል፡፡)
ኢሕአዴግ ስለፈጠራቸው ወንጀሎቹ ያዉ የበለጠ ደግሞ ቀደም ሲል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ (አሁን ላይ የተደመሩ ስለሆነ) እዉነቱን ሊነገሩን ይችላሉ፡፡ እሳቸዉ ሳያዉቁ የሚፈጸም ነገር ስለማይኖር፤ ያዉቁም ስለነበር፡፡ ከዚያ ውጭ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሲራጅ ፈጊሳም የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት አባል ስለነበሩ እንዲህ ዓይነቶቹን ድርጊቶች ያውቃሉ፡፡ በእርግጥ ሌሎችም የሚያዉቁ አሉ፡፡
እነዚህ ድርጊቶች የተፈጸሙት አቶ መለስ ዜናዊ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደነበሩ ነው፡፡ መረጃዎቹን የነገረኝ “ወፍ” ነው፡፡ መረጃዉን እንጂ ምንጩን ላለመንገር ሲሉ ሺማግሌዎች “ማን ነገራችሁ?” ሲባሉ “ወፍ ነገረኝ” እንዲሉ እኔንም የነገረኝ ወፍ ነው፡፡ ከነገረኝ አንድ ሁለት ዓመት ሆኗል፡፡
በቅርቡ ደሴ ለዚያውም ተመልሶ ሸዋበር መስጊድ አካባቢ ችግር ለመፍጠር የተደረጉትን ጥረቶች ስናይ ከጀርባ ሆኖ የሚያሽከርከር ሊኖር እንደሚችል ለመገመት የሚያስችሉ አንዳንድ ምልክቶች አሉ፡፡ ኮምቦልቻ ከተማም ላይ እንደዚሁ፡፡ በተለይ ኮምቦልቻ ከተማ ላይ ያለውን ሁኔታ እነ ኡስታዝ አቡበከር እገረ መንገዳቸውን በቅርቡ የተፈጠሩትን ችግሮች ትኩረት በመስጠት ሰዎቹን አስታርቀዋቸው፣ ሁለቱንም ወገን አዉፍ አባብለው ቢያስታርቋቸው ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ ምክንያቱም ስለሁኔታው በቅርቡ በከተማዉ በመገኘት እንደተረዳሁት በአፋጣኝ መፍትሔ ይሻል፡፡
ሌላው ለዚህ ጽሑፍ መነሻው ምክንያት “ወደፊት ኢትዮጵያን የሚያሰጋት የእነ ኡስታዝ አቡበከርና አህመድን ጀመል የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነዉ” የሚል ይዘት ያላቸውን ጽሑፎች መልቀቅ የጀመሩ የበረዶው ዘመን ሰዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ በመታዘቤ ነው፡፡ ስንት ጊዜ ሕዝብን ለማሳሳት ይሞክራሉ በሚል፣ብስጭት ቢጤ፡፡ ቀደም ሲል የሸረቡትን ተንኮል ላጤነ ሰው እንዲህ ዓይነቱ የህልም ሟርት ምን እንደሆነ ይገባዋል፡፡
የጢጣው ኮሌኔል አሁን በዚያ አካባቢ የለም፡፡ አዲስ አበባ ካራምቡላ ሲጫወት ይውላል አሉ፡፡ ከሌላ የጢጣው ኮሌኔል ዓይነት ሰዎች እራሳችንን እንጠብቅ፡፡ ምክር ሁሉ ለበጎ ላይሆን ይችላል፡፡ ኮሌኔሉን ደሴ በነበርኩበት ጊዜ በመልክም በስምም እውቀዋለሁ፡፡ በወቅቱ የምሠራው ደሴ ስለነበር፣እሱ ከጢጣ መጥቶ ዉስኪ የሚጠጣበትና እኔም ቡና (አንዳንዴም ምሳና እራት የምመገብበት) የምጠጣበት ላሊበላ ሆቴል ስለነበር ነው የማውቀው፡፡ በስህተት እንኳን ሰላም መባባላችንን አላስታውስም፡፡ ከላይ ስለኮሌኔሉ የጻፍኩትን መረጃ ያደረሰኝ በወቅቱ ጧት ማታ ሰይጣናዊ ምክር ለመስጠት ከመረጣቸው ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ያኔም የኮሌኔሉን ምክር አልተቀበለውም ነበር፡፡