>
5:18 pm - Thursday June 15, 3122

ቆመንልሀል ያለውን ህዝብ አንገቱ ላይ  የቆመው ብ.አ.ዴ.ን!!! (የሽሀሳብ አበራ)

ቆመንልሀል ያለውን ህዝብ አንገቱ ላይ 
የቆመው ብ.አ.ዴ.ን!!!
የሽሀሳብ_አበራ
* አብራችሁኝ ስሩ! አርሙኝ! እንተራረም! አማራ ዳግም አንገት አይደፋም! ሲል የነበረው ብአዴን አንገት ሚያስደፋ መግለጫ አውጥቶ ጠፋ፡፡
 
 በ 27 ዓመታት ውስጥ የብአዴን መግለጫ እንደከሰሞኑ ወርዶ አያውቅም፡፡ጭራሽ እንደ ሰፈር ባልቴት አትሙኝ ይበል፡፡የብአዴን ጉዳይ አይመለከታችሁም፡፡በማይመለከታችሁ ሀሳብ ከመስጠት ተቆጠቡ  ብሎ መግለጫ ማውጣት ያውም በዚህ ወቅት ህዝብ  ከሚመራ ፖርቲ አይጠበቅም፡፡
 …
የኢህአዴግ  ጉባዔ ልማታዊ መንግስትን ማጠናከር የሚል መሪ ቃል ቋጥሯል፡፡ብአዴንም እነ አብዮታዋ ዲሞክራሲ አቀንቃኞችን ለመጠበቅ እንዳሰበ መግለጫው በግልፅ ያሳያል፡፡
የብአዴን ነገር ችላ የሚባል አይደለም፡፡ የመግለጫው እንድምታ ግልጽ ነው፡፡ ልለወጥ ነው ያልኳችሁን ትቸዋለሁ የሚል ነው፡፡
ሀ) ሊቀመንበሩ አቶ ደመቀ መኮንን እና ም/ሊቀመንበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አማራ ከአሁን በኋላ አንገቱን አይደፋም ብለው በባህርዳር ሰልፍ ላይ ቃል ገብተዋል፡፡ ህዝቡም አምኗቸዋል፡፡ ልጆቹ ናቸውና ማመኑ ተገቢ ነበር፡፡
ለ) አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የወልቃይት ጉዳይ ብንሸሸው ብንሸሸው አላመለጥነውም ብለው የአማራ ጥያቄዎች በሙሉ የብአዴን ጥያቄዎች መደረጋቸውን ገልጠው ነበር፡፡
መ) ከጥቂት ሳምንታት በፊት ማዕከላዊ ኮሚቴው በሰጠው መግለጫ ከአሁን ወዲያ መመሪያዬ የአማራ ብሄርተኝነት ነው ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲም ጨርሶ መጣል ወይም መሻሻል ያለበት መሆኑን እወያይበታለሁ ፤ የክልሎችን አከላለልም የምቀበለው አይደለም…ወዘተ የሚል ቃል ሰጥቷል፡፡
አማራው ይህን ሁሉ ቃል መዝግቧል፡፡ አምኗልም፡፡ ያመናችሁ የመታመን ሪኮርድ ስላላችሁ ሳይሆን ልጆቹ ስለሆናችሁ ነው፡፡
የበቀደሙ መግለጫ አሳፋሪና ልፍስፍስ ነው፡፡
1) ቃላችሁን አክብሩ 2) ቃላችሁን አክብሩ 3) ቃላችሁን አክብሩ
፤ ይኸው ነው፡፡
ህዝቡ እንደሚፈልገው ፤ ቃል እንደገባችሁት መሆን ያለባችሁ ትክክሉ ያ ስለሆነ ብቻ አይደለም፡፡ ይህን ቃላችሁን አጥፋችሁ ብታፈገፍጉ ልጅነታችሁም ጥያቄ ውስጥ ስለሚገባ ነው፡፡
አማራው የድሮ ዘመን ቁማርተኞች መጫወቻ እንድታደርጉት አይፈቅድም፡ ፡
ለግንዛቤ እንዲረዳችሁ መግለጫውን አያይዤዋለሁ:-
በወቅታዊ ጉዳዮች ዙረያ ከብአዴን የተሰጠ መግለጫ
 
የተከበራችሁ የክልላችን ህዝቦች
የተከበራችሁ የብአዴን አባላትና ደጋፊዎች
የተከበራችሁ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች
በአገራችን የተፈጠረው የለውጥ እንቅስቃሴ የነፃነትና የዲሞክራሲ ውጤቶችንናድሎችን እያጎናፀፈን ይገኛል፡፡ በክልላችንም ሆነ በአገራችን እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ባለቤት በዋነኛነት ህዝቡ ነው፡፡
በአገራችን የፖለቲካ ስነ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ ዜጎች የመሰላቸውን ሃሳብ በነፃነት የሚያራምዱበት ዲሞክራሲያዊ መድረክ እንዲመቻችና በህብረተሰባችን የተፈጠረው የለውጥ ተስፋ ቀጣይነት እንዲኖረው ብአዴን ከመላው ህዝብና ከሌሎች ለውጥፈላጊ ሓይሎች ጋር በመሆን የማይተካ ድርሻ እየተወጣ የቆየ መሆኑ ለማን ምግልፅ ነው፡፡ በቀጣይም ይህ የተጀመረው ለነፃነት፣ ለማህበራዊ ፍትህ መረጋገጥና አገራችንን ወደ ተሟላ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር የሚደረገው ትግል መሰረት እንዲይዝ ብአዴን በቁርጠኝነት እየታገለ እንደሚጓዝ በድጋሚ ያረጋግጣል፡፡
የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ለበለጠ ድልና ውጤት እንዲበቃ ሌሎች ተፎካካሪ ሃይሎችም ሆነ ፖለቲካዊ ቡድኖች የበኩላቸውን ገንቢ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ብአዴን በፅኑ ያምናል፡፡ ማንኛውም ፖቲካዊ አጀንዳ ያለው ቡድንም ሆነ ግለሰብ የሌሎችን መብት በማክበር ህግና ስርዓትን ተከትሎ በመሰለው መንገድ ሃሳቡን የመግለፅ መብቱ የተከበረ መሆኑ በተደጋጋሚ የተገለፀ ጉዳይ ነው፡፡ በቀጣይ ይህ ዜጎች ሃሳባቸውን በመሰላቸው መንገድ በክልልም ሆነ በአገር ደረጃ የማራመድ መብታቸው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ብአዴን ያምናል፡፡
ይህ እንደተጠበ ቀሆኖ‹‹በፍቅር እንደመር በይቅርታ እንሻገር›› በሚል መሪ ቃል አዲሱን አመት እያከበርን ባለንበት በዚህ ወቅት የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ አወንታዊ በሆነ አቅጣጫ ወደፊት እንዳይራመድ የሚያደርጉ የቆየውን የጥላቻ ፖለቲካ የሙጥኝ በማለት የሚንቀሳቀሱ፣ በህዝብ ትግልና መስዋዕትነት የተገኘው ይህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ተስፋ እንዲጨልም፣ በተለይም የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችን ነፃ እንቅስቃሴ ተገቢነት በሌለው አካሄድ ለመገደብ ጥረት የሚያደርጉና እኔ ያልኩትን ብቻ ተቀበሉ የሚሉ አካላት እንዳሉ በተግባር ተስተውሏል፡፡
በተለይም በክልሉ ውስጥ የሚካሄድን የግብይት እንቅስቃሴ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በማደናቀፍና የግብርና ምርታችን ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ አርሶአደሩንንና መላህዝባችንን በሚጠቅም መንገድ እነዳይሸጥና የኑሮ ውድነት ችግርም እንዲባባስ የሚያደርግ እንቅስቃሴ እየተስተዋለ ይገኛል፡፡
ከዚህም ሌላ ህግና ስርዓትን ባልተከተለ መንገድ በለውጥ ሃይል ስም ተሸፍኖ የመንግስት አገልግሎ መስጫ ተቋማትን ስራ በማደናቀፍ ለውጡን በብቃት እየመሩ የሚገኙትንና ህዝባዊ ተቀባይነት ያላቸውን የድርጅታችንን አመራሮች ከድርጅቱ አሰራር ውጭ በኃይል ለመቀየር የሚደረግ ሙከራ በአንዳንድ ቦታዎች እንዳለ ተስተውሏል፡፡
ህዝባችን ለፍትህና ለዲሞክራሲ ታገለ እንጂ ስርዓት አልበኝነትን ለማንገስ መስዋዕትነት አልከፈለም፡፡ ይልቁንም የክልላችንም ሆነ የአገራችን ህዝቦች ለለውጥ የታገሉትና መስዋዕትነት የከፈሉት የህግ የበላይነት የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ስር እንዲሰድና ከዚሁም ህብረተሰቡ በዘለቄታው መብትና ጥቅሙ እንዲከበር፣ ዜጎች በፈለጉት ቦታ በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ ንብረት የማፍራትና በሰላም የመኖር መብትና ነፃነት እንዲከበር እንጅ ሃገራችንን መልሶ የአፈናና የዲሞክራሲ እስር ቤት ለማድረግ አይደለም፡፡ ስለሆነም አሁን በተለያዩ ቡድኖችና አካላት እየተፈጸሙ ያሉት መሰረታዊ የህዝባችንን መብት የሚጋፉ፣ ደህንነትን ለአደጋ የሚያጋልጡና ዲሞክራሲን የሚያጠቡ ተግባራት ፈጽሞ ተቀባይነት የላቸውም፡፡
የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፍ፣ ንብረት የሚያወድም ድርጊት በክልላችንም ሆነ በሌሎች የሃገራችን አካባቢዎች አልፎ አልፎ ሲፈፀም የቆየ ሲሆን ሰሞኑን ደግሞ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ጉባ ወረዳ አልምሃል በተባለ አካባቢ ለስራ ፍለጋ በሄዱ የክልላችን ነዋሪዎች ላይ አሰቃቂና አስነዋሪ በሆነ መልክ ግድያ ተፈፅሟል፡፡ በህዝቦች መካከል ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅር እንዲሰፍን መላየ ሃገራችን ህዝቦች ሌት ተቀን በሚተጉበት በዚህ ወቅት እንዲህ አይነት ርካሽ ተግባር መፈጸም መዋረድና ከሰው በታችነት መሆኑን በመገንዘብ ብአዴን ድርጊቱን በጥብቅ ያወግዛል፤ ጉዳት በደረሰባቸው ወገኖች የተሰማውን ልባዊ ሃዘንም ይገልጻል፡፡ የዚህ ድርጊት ፈፃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ይህንን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እንዲፈፀም ስምሪት የሰጡ አካላት ጭምር በህግ እንዲጠየቁ ብአዴን ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር እየሰራ የሚገኝ ሲሆን የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስትም በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡና ተጨማሪ ጥፋት እንዳይፈጸም ያደረግ ዘነድ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡ በክልላችን ውስጥም ዜጎችን በማንነታቸው ወይም በያዙት ፖለቲካዊ አቋም ላይ ተመስርቶ የሚከናወነውን ማንኛውንም ጥቃት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ በሚፈፅሙ ሃይሎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ አመራር እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን ህግ የማስከበር ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፣ አንዳንድ ወገኖች የብአዴን አመራሮችን እውነታ በሌለው መረጃ ላይ በመመስረት የተወሰኑትን የለውጥ ሃይል ሌሎችን ደግሞ ፈፅሞ የለውጥ አደናቃፊ አድርገው ከብአዴን ግምገማና አቋም ውጭ የውስጥ አዋቂ በመምሰል የጀመሩት ዘመቻ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ብአዴን ያምናል፡፡
 እነዚህ ወገኖች ማህበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ ሁሉን የመገናኛ አውታሮች በመጠቀም በማይመለከታቸው ጉዳይ የብአዴንን አመራር ስም የማጥፋትና የመከፋፈል ስራ አጀንዳ አድርገው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ስንመለከት ነገሩ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” የሚሉት አይነት ሆኖብናል፡፡
ድርጅታችን የራሱ የሆነ ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ስርዓትና አመራር የሚመድብበትና የሚያወርድበት ግልጽ አሰራር አለው፡፡ በዚህም ለይ በመመስረት በቅርቡ በድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ለይ እርመጃ የወሰደ ከመሆኑም በላይ ከዛም በታች በየደረጃው በአለው አመራር ለይ ማስተካከያ አየተደረገ ይገኛል፡፡ ከዚያ ውጭ በሆነ መንገድ አመራሩን በተለያየ ቡድን እየመደቡ የሌለ ስም እየሰጡ አንዱን ወገን የለውጥ ሃይል አድርጎ በሃላፊነት እንዲቀጥል ሌላው ወገን ደግሞ ጥርግርግ ብሎ ከሃላፊነት እንዲወገድ የሚካሄደው ግፊትና ዘመቻ ተገቢነትና ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
ከድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ያለውን አመራራችንን በተጨባጭ ለህዝብ እያበረከተ ካለው አስተዋጽዖ ይልቅ በትውልድ ቦታና በዘር ሃረግ በመከፋፈል፣ እንዲሁም ስም በማጥፋት፣ የለውጡን ጤናማ ግስጋሴ በሚጎዳ አኳኋንና ለለውጥ መሪዎች እንቅስቃሴ ሓይል በማያሰባስብ መንገድ መፈረጅና ማብጠልጠል እየተስተዋለ ነው፡፡
 ህዝብ ለማገልገል የተሰማራ ማንኛውም አመራር ሥራ ሲሰራ ሊያጠፋ ወይም ሊሳሳት ይችላል፡፡
በአመራር እድሜ ዘመን የተፈጠረንና የታረመን ችግር ሁሉ ከዓመታት በኋላ እየቆፈሩ አሁን ለደረስንበት የይቅርታና የመደመር መርህ በማይመጥን ሁኔታ የአመራርን ስም እየጠቀሱ እስከ ቤተሰቡ ድረስ ለማሸማቀቅ መሞከር ዘመናዊውን የዲሞክራሲ እሳቤም ሆነ ነባሩን የሃገራችንን የጨዋነት እሴት ፈጽሞ የሚሸረሽር ድረጊት መሆኑን ብአዴን ያምናል፡፡
ስለሆነም በክልላችንም ሆነ በአገራችን እየተካሄደ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ተጠብቆና ዘላቂ ሆኖ አገራችንን ወደ ዳበረ ዲሞክራሲ ለማሸጋገር ይቻል ዘንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ፤የፖለቲካ አክቲቪስቶችና የብዙሃን መገናኛ ባለሙያዎች የበኩላችሁን ገንቢ ሚና እንድትወጡ ብአዴን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡
መላው የክልላችን ህዝብ፣ የብአዴን አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም ሕግ በማስከበር ሥራ ላይ የተሰማራችሁ አካላት፤ ይህ በህዝባችን ግፊትና በድርጅታችን መሪነት የተቀጣጠለው የለውጥ እንቅስቃሴ ለውጤት እንዲበቃ ሰላማዊ፣ ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ ትግል በማካሄድ በክልላችን ሰላም ለማስፈን፣ የሕግ የበላይነት ለማስከበር እና የዜጎችን በነፃነት የመንቀሳቀስና ንብረት የማፍራት መብት እንዲረጋገጥ የተለመደውን ህዝባዊ ቁርጠኝነት ተላብሳችሁ እንድትንቀሳቀሱ፤ በአሉባልታና ሆን ተብሎ በሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ሳትዘናጉ ህዝባችን ማጣጣም የጀመረው የነፃነት መንፈስ በምንም ሃይል እንዳይቀለበስ ከጎናችን በመሰለፍ ትግላችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ድርጅታችሁ ብአዴን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡
በፍቅር እንደመር በይቅርታ እንሻገር!
መስከረም 2011 ዓ.ም
ባ.ዳር
Filed in: Amharic