የአገራችንና የህዝባችን ጉዳይ ያገባናል ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ ያወጡት መግለጫ!!!
* በአዲስ አበባ ከተማና በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታየዉ ግጭትና አለመረጋጋት ባስቸኳይ መቆም አለበት!!!
የአገራችንን ፖለቲካ፤ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወት በበላይነት ለመቆጣጠር ህወሃት/ኢህአደግ ለ27 አመታት የዘረጋውን አፈናና ጭቆና ለመታገል መላው ህዝባችን ከፍተኛ የህይወት ፤ የአካልና የንብረት መስዋዕትነት ሲከፍል ቆይቶአል።
በተለይ በወጣቱ መሪነት ከ2006 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት አመታት በኦሮሚያ ፤ በአማራና የተቀሩት የአገራችን ክፍሎች ሲቀጣጠል በነበረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ወቅት ቁጥራቸው በሺዎች የሚቆጠር ወጣቶች ባዶ እጃቸውን ከታጠቁ ሃይሎች ጋር ሲፋለሙ ውድ ህይወታቸውን አጥተዋል። በነዚያ ወጣቶች ላይ የተፈጸመው ግዲያ፤ አፈናና ፤ ሰቆቃ ያስቆጣቸው የለውጥ ሃይሎች ከራሱ ከኢህአደግ ውስጥ ወጥተው አገራችንንና ህዝቦቿን ለመታደግ የሚያስችል እርምጃ ባይወስዱ ኖሮ ከዳር እስከዳር በመቀጣጠል ላይ የነበረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል፤ ውጤቱም ምን እንደሚሆን መገመት ከባድ ነው ።
ከሰሞኑ በአዲስ አበባና አንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች እየተስተዋሉ ያሉ የፖለቲካ አመለካከትን መሠረት ያደረጉ የሚመስሉ ነገር ግን ከበስተጀርባቸው መላው አገራችንና ህዝባችን ተስፋ ያደረገውን የለውጥ ሂደት ለማሰናከል ተግተው የሚሠሩ ሃይሎች የሚያቀነባብሩት ሴራ ስለመሆኑ መገመት የማያስቸግሩ ግጭቶች ተቀስቅሰው የዜጎችን ህይወት እስከመቅጠፍ መድረሱን የሚያረጋግጡ መረጃዎች በሰፊው እየቀረቡ ናቸው። ህዝባችን ለአመታት በከፈለው መስዋዕትነት ከምንጊዜውም በላይ ተስፋ የሚሰጥ አዲስ የለውጥ አየር በአገራችን ምድር በሰፈነበትና አገር ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ እግር ከወርች ታስረው የነበሩትም ሆነ አገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ቀደም ሲል በሽብርተኝነት ጭምር የተፈረጁ ፖለቲካ ድርጅቶች፤ አክቲቪስቶችና ሚዲያዎች ወደ አገራቸው ተመልሰው ለውጡን ወደ አስተማማኝ ምዕራፍ ለማሸጋገር የየራሳቸውን ድርሻ ለመወጣት እንቅስቃሴ እያደረጉ ባለበት በዚህ የታሪካዊ ወቅት እንዲህ አይነት ግጭት መቀስቀሱ ማንኛውንም ቅን የአገሪቱን ዜጋ እጅግ የሚያሳስብና የሚያሳዝን ክስተት ሆኖአል።
በዚህም የተነሳ የአገራችንና የህዝባችን ጉዳይ ያገባናል በማለት አገር ውስጥና ከአገር ውጭ ስንንቀሳቀስ የነበርን ስማችን ከዚህ በታች የተዘረዘርን የፖለቲካ ድርጅቶች:-
የኦሮሞ ፈደራሊስት ኮንግረስ (OFC)
የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባር (ODF)
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ( OLF)
የኦሮሞ አንድነት ነጻነት ግንባር (UFIO)
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ለአንድነት -(OLF-T)
ሰማያዊ ፓርቲ እና (Blue Part)
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንዲነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ (PG7)
መስከረም 6 እና 7 ቀን 2011 ዓም ተሰብስበን የግጭቱን አሳሳቢነትና የደረሰውን የጉዳት መጠን ከገመገምን በኋላ ግጭቱን የቀሰቀሱትም ሆነ በግጭቱ በመሳተፍ በሰው ህይወት፥ አካልና ንብረት ላይ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን በጽኑ እንደምናወግዝና የግጭቱ ተዋንያንና ከበስተጀርባ ሆነዉ ግጭቱን ያስተባበሩ የዉጭና የአገር ዉስጥ ሀይሎች ከዚህ ድርጊታቸዉ በአስቸኳይ እንዲታቀቡ ለማሳሰብ ይህንን መግለጫ በጋራ ለማውጣት ተስማምተናል። ዛሬ አገራችን ዉስጥ በመካሄድ ላይ ያለዉ ተስፋ ሰጪ የለዉጥ እንቅስቃሴ ከላይ የተጠቀሰው አሳዛኝ ግጭት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶችን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በከፈለው የህይወትና የአካል መስዋዕትነት የተገኘ ለውጥ ነው።
ስለዚህ ወጣቱ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በራሱ መስዋዕትነት የተገኘውን ይህንን ተስፋ ሰጪ የለውጥ ጅምር ለመቀልበስ ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ሆነው ለውጡን ለመቀልበስ ተግተው ለሚሠሩ ሃይሎች መሣሪያ እንዳይሆን ማሳሰብ ተገቢ ነው።
በዚህ አስቸጋሪ የለውጥ ወቅት አገራችንን የመምራት ከባድ ሃላፊነት የወደቀባቸው የመንግስት አካላትም የአገርንና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ሲሉ እንዲህ አይነት አደገኛ ችግሮች ከመከሰታቸዉ በፊት የመከላከል እርምጃ እንዲወስዱና በመካሄድ ላይ ባለው ግጭት እጃቸው ያለበትን ሃይሎች በአስቸኳይ አጣርቶ ለህግ የማቅረብ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማሳሰብ እንወዳለን።
ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ እዉን ሆኖ የምናየዉ የፖለቲካ ምህዳር ዜጎች የፖለቲካ አመለካከታችዉን ህጋዊና ሠላማዊ በሆነ መንገድ ለመግለጽ የሚችሉበት፥ ከወከባና ከአፈና የጸዳ አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበት ደግሞም ለዘመናት የታገልንለትና ሁላችንንም ማስተናገድ የሚችል የፖለቲካ ምህዳር ነዉ። ይህንን በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘ ዕድል በመጠቀም ልዩነቶቻችንን በውይይትና በድርድር ለመፍታት የሚያስችለንን ዲሞክራሲያዊ ባህል ማዳበር ከሁላችንም የሚጠበቅ አገራዊ ሀላፊነት ነዉ። ከዚህ ውጪ “እኔ ያልኩት ካልሆነ” በሚል ኋላ ቀር አስተሳሰብ ልዩነቶችን በሃይል ወይም በጉልበት ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ማናችንንም የማይጠቅሙና ይልቁንም ሁላችንንም አገር አልባ ሊያደርገን ወደሚችል የመጠፋፋት ፖለቲካ ሊወስዱን እንደሚችሉ አዉቀን የዚህችን ለዘመናት የአምባገነኖች መፈንጪያ የሆነችዉን አገራችንን የፍትህ፥ የነጻነት፥ የዲሞክራሲና የእኩልነት ተምሳሌት እናድርጋት።
በመጨረሻም ከላይ ስማችን የተዘረዘርነው የፖለቲካ ድርጅቶች በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን በአፋጣኝ ለመቆጣጠና በአገራችን እየታየ ያለውን የለውጥ ሂደት ለማስቀጠል በህዝባችን ከፈተኛ መስዋዕትነት የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የመጣውን የነጻነት አየር የሚበክል ማናቸውም አይነት ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆም ለማድረግና ለሰላም፤ ለመረጋጋትና ለህዝቦች አብሮነት በጋራ እየተመካከርን ለመሥራት ተስማምተናል።
በመካከላችን ያሉ የፖለቲካ ልዩነቶች በሠላምዊና በሠለጠነ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ የሚስተናገዱበት ምህዳር እንዲጠናከር የበኩላችን አስተዋጾ ለማድረግ ተስማምተናል።
ለውጡን ለማደናቀፍ ከውስጥም ሆነ ከውጪ ሆነው እየሠሩ ያሉ ሃይሎች በመካከላችን የሚታየውን ልዩነቶች ተጠቅመው ለውጡን እንዳይቀለብሱ አባላቶቻችንና ደጋፊዎቻችንን ከጎናችን እንዲቆሙ ጥሪያችንን እጋራ እናቀርባለን።
የለውጡ ሃይል የሆነው ወጣቱ የህብረተሰባችን ክፍል በየአካባቢው ግጭትንና ሁከትን ከሚቀሰቅሱ ተግባራት እንዲታቀብ አደራ እንላለን!!!
መስከረም 7 ቀን 2011 አዲስ አበባ