>
1:18 pm - Friday May 20, 2022

እውነት እውነቱን እንነጋገር!!! (ሚልዮን አየለች)

እውነት እውነቱን እንነጋገር!!!
ሚልዮን አየለች
”ምነው በእንቁላሉ በቀጣሽኝ እንዳለው”
በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሞት እና እንግልት ለማስወገድ ቆምጨጭ ያለ አመራር ስንጠብቆ እለት እለት ጆሮአችን በሚያባብሉ እና በሚያማልሉ ቃላት እየተሞሉ ሞታችንን ግን የሚያስቆም ጠፋ።
አሁን ላይ የኢትዮጶያ ህዝብ እንደ ከብቱ ጆሮው ብቻ የሰባበት የሚያስፈልገውን ነገር በተመረጡ ቃላት እየሰማ ያለበት ከድርጊት እርቆ ተስፋ የቆረጠበት ነው።
ቁርጠኝነቱ ከነበረ በዜጎች ላይ እየተፈፀመ የዘለቀውን ሞትና እንግልት ለማስቆም ገና ድሮ በተቻለ ነበር። ምነው በእንቁላሉ በቀጣሽኝ ኑሮ እንዲል ልጁ ከጎለመሰ በኋላ በሬ ባልሰረቀ ነበር።
የዶክተር አብይ አመራር በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን መጎሳቆል፣ሞት እና ስደት ለምን ማስቆም ተሳነው? አስቀድሞ በኦጋዴን ሰዎች ተገድለው የኦሮሞና የኦጋዴን ፀብ ነው በማለት ይህንንም የለኮሱት የለውጥ ኃይሉን የማይፈልጉት ሴረኞች ያመጡት እሳት ነው ብለውን ከቀድሞ ነፍሰ በላ የኦጋዴን ክልል መስተዳደር ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ እርቁን አሳዩን ውሎ ሳያድር እርቁም ሳይደርቅ የአብዲ ኢሌ አንባ ገነንነት በዜጎቻችን ላይ የፈፀመው ዘግናኝ ድርጊት በአብያተ ክርስቲያን ላይ የፈፀመው አስነዋሪ ምግባር ከእርቁ በኋላ ተከትሎ መጣ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ሁሉ ሳይሆን በፊት ማስቆም አይቻልም ነበረ ወይ?
ይቀጥልና በሀዋሳ ነዋሪዎች መካከል በሁለት ማህበረሰቦች የእርስ በእርስ ግጭት ዜጎች ከእነ ነፍሳቸው ሲቃጠሉ መግደል ጀግንነት መስሏቸው ከገደሉት ከሚያቃጥሉት እሬሳ ጋር ፎቶ ሲነሱ በአደባባይ አየን ይህንን አስነዋሪ ድርጊት የፈፀሙትን ወንጀለኞች ከምን እንዳደረስናቸው ሳይታወቅ እና ፍርዱን በአደባባይ ሳንሰጥ መግደል መሸነፍ ነው የሚለውን ዲስኩር መስማት ጀመርን። ሻሸመኔ ላይ በተዘጋጀው ለዘረኘነት አቀጣጣዩ ጃዋር መሀመድ አቀባበል ላይ የአንድን ንፁህ ዜጋ ክብሩን ገፈው በህብረት ደብድበው ዘቅዝቀው ከሰቀሉት በኋላ ባጠፉት ጥፋት ጀግንነት ተሰምቷቸው ሰልፊ የሚነሱትን አረመኔዎች ህጉ ምን አደረጋቸው? የሰማነውም ያየነውም የለም።ብዙ ብዙ ለመናገር የሚቀፍ ለመስማት የሚከብድን በዚህ ወቅት አይተናል ግን ድርጊቱን ከማውገዝ የዘለለ ተግባር ተደርጎ አልሰማንም አላየንም በዚህም የዜጎች ደህንነት የመኖር ነጳነት የነገው በሜጫ የመገደል ባለ ተራው እኔ እሆን ይሆን? በማለት ስጋት ውስጥ ገብቷል።
ነውር የፈፀሙትን ያስፈፀሙትን ገዳዮችንም አስገዳዮችንም በአደባባይ ብንቀጣ ኑሮ ዛሬ ላይ በቡራዩ እና በአዲስ አበባ የተፈፀመው ጋጠወጥ ድርጊትን ከምንጩ ባጠፋን ነበር።ብዙ ጊዜ እንዳልነው የህግ የበላይነት የሌለባት ሀገር ዜጎች በህግ ተዳኝቶ መፍትሄ አገኛለሁ የሚል ስነ ልቦና ይጠፋባቸውና ፍትህን በራሳቸው እጅ ለማምጣት ይጣደፋሉ ይህ ደግሞ የበዛ እልቂት በሀገሪቷ ላይ ያደርሳል በዚህም በኢትዮጵያ ላይ ያለመረጋጋትና ሁካታ ሲሰፍን አንቀፅ ፴፱ ለማንሳት የሚሯሯጡ ክልሎች በር እንከፍትላላቸዋለን።ለዚህ ነው በእንቁላሉ ቶሎ መቅጣት ይልመድብን የምንለው።
Filed in: Amharic