>

በፈጠራ ታሪክ የኢትዮጵያን ባለውለታ አትጥሉ!! (ፈለቀ ማሩ)

በፈጠራ ታሪክ የኢትዮጵያን ባለውለታ አትጥሉ!!
ፈለቀ ማሩ
በትላንትናው ምሽት አቶ ጃዋር LTV ላይ ስለ የአኖሌ ሐውልት ትክክለኛ ስለመሆኑ ተናግሮ ነበር እኛም ትክክል የምንለውን እንዲህ እንናገራለን፦
 
በዘመነ መሳፍንት ብትንትኗ ወጥቶ የነበረችው ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ በሚጣር ጊዜ የአርሲ ሕዝብ በተደጋጋሚ አልገብርም ብሎ ስላስቸገረ አጼ ምኒልክ በ1878 ዓ/ም ወደ አርሲ ዘምተው የአርሲ ሕዝብ እንዲገብር አድርገው ሕዝቡንም እንዲያስተዳድሩ አጎታቸው ራስ ዳርጌን ሾመው ተመለሱ፡፡ ይህንንም ተከትሎ አንዳንዶች አጼ ምኒልክ በዘመቻው ወቅት የሴቶችን ጡትና የወንዶቹን ክንድ አስቆርጠዋል በሚል ያለ ስም ስም ያለ ግብር ግብር ሰጧቸው፡፡ የዛሬ መቶ ዓመት መለስ ብለን ግን ለዚያ ዘመን ትልቅ መረጃ የሆኑትን ጸሐፊ ትዕዛዝ የሚል ሹመትን ባነገቡ ሰዎች የተጻፉቱን ዜና መዋዕሎች ስንመለከት አንድም ቦታ አጼ ምኒልክ አልገብርም በሚሉ ቦታዎች ላይ እጅና ጡት ቆርጠው ቀጡ የሚል ጽሑፍ አይገኝም፡፡ እውነት ይህ ነገር ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ጸሐፌ ትዕዛዞች ይዘግቡት ነበር ምክንያቱም በዚያ ዘመን አልገብርም ብሎ ላስቸገረ አካባቢ የሚደረግ ዘመቻ እና ቅጣት ትክክለኛም ምክንያታዊም ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ለሌላው ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ የተደረገው ሁሉ ይጻፍ ይገለጽ ነበር ነገር ግን ታሪኩ አልተደረገምና አልተጻፈም፡፡
የአጼ ምኒልክን በጎነት ላለማየት ጥቅማ ጥቅምና ውሸት ልቦናቸውን የሰወረው ሰዎች በዘመናችን እንዳሉ ሁሉ ድሮም እንደሚኖሩ ግልጽ ነው፡፡ የአጼ ምንልክን ስራ እየነቀፋ መጥፎ ስራን ሰሩ እያሉ በመዘገብ የተጠመዱ ማርቲያክ ዳ ሳልዲክ እና ጁልየ ቦረሊ የተባሉ ሁለት የአውሮፓ ጸሐፊያን ነበሩ፡፡ ታዲያ እነዚህ ጸሐፊያን አርሲ በጦርነቱ ጊዜና ከጦርነቱ በኋላ መጥተው ያዩትንና መረጃ አሰባስበው ያገኙትን ነገር እያንዳንዳቸው በመጽሐፍ አሳትመውት ነበር ነገር ግን በሁለቱም መጽሐፍ ላይ እንደ ዜና መዋዕሎቹ ሁሉ አንድም ቦታ የሴቶችን ጡት የወንዶችን እጅ ስለመቆረጥ የሚያወራ ምንም ጉዳይ የለም መቼስ እንዚህ ጸሐፊያን ለምኒልክ አድልተው ይህን ጉዳይ ሳያነሱት ቀሩ ልንል አንችልም፡፡ እሺ ይሄን ሁሉ እንተወውና እውነት ይህ ታሪክ ተፈጥሮ ቢሆን ከጸሐፊያን ቢያመልጥ እንዴት ከስነ ቃል አመለጠ መቼስ እኛ ኢትዮጵያዊያን ታሪክን አንበበን ከተራደናው በላይ በግጥም የያዝነው ይብልጣል በዚህም መሠረት ቹርሊ የተባሉ የጣሊያን ሊቅ የኦሮሞ ሕዝብ ስነቃልበሚል ጥናታቸው በአርሲ ወረራ ወቅት በአርሲዎች የተገጠሙ አያሌ ግጥሞችን እንጉርጉሮዎችን አሰባስበው አሳትመዋል ነበር፡፡ ነገር ግን አንድም ቦታ ስለ ጡት ስለ እጅ መቆረጥ የተጻፈ ነገር አላካተቱም፡፡ ታዲያ ለዚህ ሐውልት መሰራት ምክንያት የሆነው ታሪክ ከየት መጣ?ቢባል መልሱ የውሸት ፈጠራ ነው።አማራን ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር እያባሉ ስልጣናቸውን ለማርዘም ሰዎች የፈጠሩት የክፋት መርዝ ነው።
በጣልያን ጋሪባልዲ በጀርመን ደግሞ ቢዝማርከን የመሳሰሉ ኃያላን የሀገር አንድነታቸውን ለማስከበር የተከተሉት አማራጭ አጼ ምኒልክ ከተከተሉት መንገድ እጅግ የከፋና ጭካኔ የተሞላበት ነበር፡፡ አብርሃም ሊንከን ደግሞ እንገነጠላለን ያሉትን የአሜሪካን የደቡብ ግዛቶች ወደ ተባበረችው አሜሪካ ያስገባው
በዴሞክራሲ ሳይሆን በጦርነት በኃይል በተወሰደ እርምጃ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ ዘመን ጋሪባልዲ፣ ቢዝማርክ፣ አብርሃም ሊንከንም በሀገራችው ትልቅ ክብር የሚሳጣቸው ባለውለታ ናቸው፡፡
እኛም ጋር ሀገርን እንደ ሀገር የሚያስብ እምዬ ምኒልክን ያከብራል ባለውለታዬ ናቸው ይላል ምክንያቱም ሀገርን አንድ ለማድረግ መሳፍንቶች ከፋፈለው ሊበትኗት የነበረችውን ኢትዮጵያ በአንድነቷ ጸንታ እንድትቀጥል አድርገዋል። ክልልን እንደ ሀገር የሚያስብ ደግሞ የውሸት ሐውልቱን ተሸክሞ ይኖራል ፡፡
ምንጭ፦ ታሪከ ዘመን ዘ ዳግማዊ ምኒልክ ጸሐፌ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴ
Filed in: Amharic