>
11:10 am - Wednesday November 30, 2022

‹‹አማራንና ኦሮሞን ለማጋጨት በተለያዩ ኃይሎች ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፤ የማይሳካ ሙከራ ነው!!›› አቶ ለማ መገርሳ፣የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

‹‹አማራንና ኦሮሞን ለማጋጨት በተለያዩ ኃይሎች ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፤ የማይሳካ ሙከራ ነው!!››

አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች የባንክ ሒሳብ ስምንት ሚሊዮን ብር ተገኝቷል!

አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች በፖለቲከኛነት ሽፋን በሆነ አጋጣሚ መድረክ ላይ ሲወጡና የመገናኛ ብዙኃን ሲያገኙ የሚያስተላልፉዋቸው መልዕክቶች ሕዝብን የሚያቀራርቡና አንድነትን የሚፈጥሩ ሳይሆን ሕዝብን የሚከፋፍሉ፣ የሚያለያዩና የሚያቃቅሩ በመሆናቸው ከዚህ በኋላ እንደማይታገሳቸው የኦሮሚያ መንግሥት አስታወቀ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ፣ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ላይ ሰሞኑን በደረሰው ግድያ፣ የአካል ጉዳትና ዘረፋን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ግለሰቦች መድረክ ሲያገኙ የሚያስተላልፉዋቸው መልዕክቶች ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጩ፣ የሚያቃቅሩ፣ የሚለያዩና አገርንም ሊበታትኑ የሚችሉ ናቸው፡፡ ማንም ግለሰብ በተፈጠረው አጋጣሚ ሕዝብን እንዲያቃቅር፣ እንዲለያይ፣ እንዲከፋፈል፣ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳሳና እንዲቀሰቅስ መሆን እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡

እሳቸው በደረሳቸው መረጃ መሠረት በቡራዩ አካባቢ የተፈጠረው ግድያ፣ አካል ማጉደልና የዘረፋ ምክንያት በአንዲት የስድስት ዓመት ሕፃን ልጅ ግድያ በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት እንደሆነ ቢሆንም፣ ድርጊቱና የደረሰው ጉዳት ግን አሳፋሪና አፀያፊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በድርጊቱ በመሳተፍ የተጠረጠሩ ከ200 በላይ ግለሰቦችና ድርጊቱ ተፈጽሞባቸዋል የተባሉ የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቁመው፣ በተጨማሪም ከኦሮሚያና ከፌዴራል የተውጣጣ የፀጥታ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ የምርመራ ሥራው በሰፊው እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ በርካታ ግለሰቦች መኖራቸውንና 300 የሚሆኑት ወደ ቀዬአቸው መመለሳቸውን ተናግረው፣ ሁሉም እንደሚመለሱና ቤታቸው የፈረሰባቸውና የተቃጠለባቸው እንደሚተካላቸው የክልሉ መንግሥት ኃላፊነት እንደሚወስድ አክለዋል፡፡

በተጀመረው የምርመራ ሥራ የወንጀል እንቅስቃሴው ቀደም ብሎ የተጀመረ መሆኑን፣ ድርጊቱን ፈጻሚዎች የሰሌዳ ቁጥር በሌላቸው ተሽከርካሪዎች እየተንቀሳቀሱ የማደራጀት ሥራ ይሠሩ እንደነበር አመላካች ነገር መገኘቱን አቶ ለማ አስታውቀው፣ ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም በአሰላ ከተማም በመንቀሳቀስ በብሔርና በሃይማኖት ለማጋጨት ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ ሕዝቡ ተባብሮና አንድ ሆኖ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ችግሩ ሳይደርስ በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በቡራዩ ከተማና አካባቢውም ቢሆን ተመሳሳይ ድርጊት በመፈጸም፣ ሕዝቡ ተረጋግቶና ተስማምቶ በሰላም እንዳይኖር ጥረት ያደረጉ ኃይሎች የተሳካላቸው ቢመስላቸውም፣ የፈለጉትን ግን አለማግኘታቸውን አክለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን ብሔር ተኮር ነጥቦችን እንደ አጀንዳ በመያዝ፣ ብሔር ከብሔር ጋር ለማጋጨት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹በተለይ ኦሮሞንና አማራን ለማጋጨት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፤›› ያሉት አቶ ለማ፣ ይኼ ሊኮነን የሚገባ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ይኼንን አውቆ መጠንቀቅና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ትብብር ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ‹‹ለውጥ ለማምጣት ሁላችንም እየጣርን፣ ከባህላዊ አስተዳደር ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስተዳደር ለመሸጋገር ከፍተኛ መስዋዕትነት እየተከፈለ ነው፤›› በማለት ብሔር ብሔረሰቦች ተባብረው እንዲኖሩ፣ ሁሉንም የምትጠቅምና እኩልነትና ፍትሕ የሰፈነባት አዲሲቷን ኢትዮጵያን ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግሥትም ብዙ ርቀት በመሄድ በርካታ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት ወቅት፣ እንደዚህ ዓይነት ድርጊት መፈጸምና ወደ ችግር ለመክተት ጥረት ማድረግ በግልጽና በአደባባይ ሊኮነን እንደሚገባ አቶ ለማ ተናግረዋል፡፡

ከስድስት ወራት በፊት ኢትዮጵያ በምን ዓይነት ችግር ውስጥ እንደነበረች እንደሚታወቅ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ‹‹ኃይል ይብቃን፣ በጠብመንጃ መተዳደር ሰለቸን፤›› ብሎ ሕዝብ በአደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን ካሰማ በኋላ፣ ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ሲደረግ፣ ‹‹ተቻችሎና ተከባብሮ መኖር ካቃተ በእውነቱ አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ገፍተው ገፍተው ወደማንፈልግበት ሁኔታ ሊከቱን የሚፈልጉ ሰዎች (አካላት) አሉ፤›› ያሉት አቶ ለማ፣ መቻቻል ጥቅሙ ለራስ ሲባል እንጂ ለመለያየት አንድ ቀን በቂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ግለሰቦች በየመድረኩና በየመገናኛ ብዙኃን ሕዝብ እንዲለያይ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ በመሆኑ፣ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ቆም ብለን ይኼ ፖለቲካ እያደገ ነው? ወይስ ወደኋላ እየሄደ? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት አለብን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከ30 ዓመታት በኋላ ወደ 1960ዎቹ ልንመለስ ነው? ወይስ እያደግን ነው?›› የሚለው ላይ በጥሞና መወያየትና መነጋገር እንደሚያስፈልግም አክለዋል፡፡

ሁሉም ካልተቻቻለ ሁሉንም ልትጠቅም የምትችል አንዲት ኢትዮጵያ መፍጠር እንደማይቻል ጠቁመው፣ አንድነትን የሚጎዱ ነገሮች ሁሉም ሊያወግዟቸው እንደሚገባ አስምረውበታል፡፡ ከምንም በላይ ሕዝቡ ማውገዝ ያለበት የብሔር ብሔረሰቦችን አጀንዳ እያነሱ አንደኛው ወገን በሌላኛው ወገን ላይ የሚያሳያቸውን ጥላቻዎች መሆኑን አክለዋል፡፡

ግለሰቦች በሚያራምዱት የጥላቻ ፖለቲካ ለማያስፈልግ ነገር የሚያነሳሱ ተግባራትና የቃላት ውርወራዎች ሕዝቡን የሚለያዩ፣ አገርን የሚበታትኑና ሊወገዙ የሚገባቸው ወንጀሎች መሆናቸውን አቶ ለማ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ሲል ከፍተኛ ዕርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን፣ በተለያዩ ምክንያቶች አገር ጥለው የወጡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገራቸው ገብተው በነፃነት እንዲወዳደሩ በሩን መክፈቱን አስታውሰዋል፡፡ እንደ መንግሥት ከፍተኛ ሸክም እንዳለው አቶ ለማ ገልጸው፣ ይኼ የተደረገው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሲባል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በየቦታው ሰላማዊ ሠልፍና ስብሰባ የሚጠራው ብዙ አካል መሆኑንና ግርግሩና ገበያው መድራቱን የተናገሩት አቶ ለማ፣ ‹‹የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ፣ ገበያ የሚወጣ ገዥና ሻጭ ብቻ ሳይሆን፣ ሌባም ተቀላቅሎ ይወጣል፤›› በማለት፣ ሕዝቡ መጠንቀቅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የሚደግፈውን፣ የሚቀበለውንና የሚናገረውን መለየትና ማወቅ እንዳለበት አክለዋል፡፡ ተቀላቅለው የሚወጡ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ መፈክሮችና ዓርማዎችም ሊጎዱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ለሚያደርጓቸው ማናቸውም ነገሮች ኃላፊነት መውሰድ መቻል እንዳለባቸው የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ለድጋፍም ሆነ ለመቀበል የሚወጡ ደጋፊዎቻቸው የሚያደርጉት ነገር ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳርን ማስፋት ማለት ሕዝብን ማቀራረብ እንጂ ማቃቃርና ለእኩይ ተግባር እንዲሠለፍ ማድረግ ባለመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም አክለዋል፡፡

‹‹አንዳንድ ስህተቶች ቢኖሩም እንኳን እኛ ፖለቲከኞች የሕዝብ መሪ እስከሆንን ድረስ፣ ሥራችንና ተግባራችን ሕዝብን ማቀራረብ ነው፤›› ያሉት አቶ ለማ፣ ከመለያየትና ከመከፋፈል፣ የጥላቻ ፖለቲካ ከመዝራት፣ የሚያቀራርብ፣ አንድነትን የሚያጠናክር፣ ሰላምን የሚያመጣና ጉርብትናን የሚያጠናክር አጀንዳ መያዝ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ይኼንን ሳይዙ ወደ መድረክና ሚዲያ መውጣት ተገቢነት የሌለውና ፋሽን ያለፈበት ፖለቲካ መሆኑን አክለዋል፡፡ አንዱን ወግኖ በሌላው ላይ የሚነዛ የጥላቻ ፖለቲካ የትም ስለማያደርስ፣ ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ሄዶ ሄዶ ሁሉንም ስለሚጎዳ ይኼ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ከአሁን በኋላ ለኢትዮጵያና ሕዝቧ እንደማይጠቅምም አስታውቀው፣ የማንም መብት በማንም ሊገፋ ስለማይችል፣ ተከባብሮና ተቻችሎ በሰላም መኖር ተቀዳሚ ተግባርና መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ብዙ ውድመቶች የሚደርሱት በሽግግር ወቅት ለመሆኑ በ1960ዎቹ እና በ1980ዎቹ የደረሱት ውድመቶች ምሳሌዎች መሆናቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ አሁንም ቢሆን መንግሥት ባይለወጥም ከተለመደው ኋላ ቀር ነገር ወደ ዘመናዊና ዴሞክራሲ ሥርዓት ለመሸጋገር በሚደረገው ሪፎርም፣ ሁሉም ኃላፊነት በመውሰድ ያለምንም ኪሳራ መምራትና መሸጋገር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋም ኃላፊነት እንዳለበት አክለዋል፡፡ ከራስ፣ ከብሔርና ከጎሳ በላይ በማሰብ ለጋራ ጥቅም በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አቶ ለማ ተናግረዋል፡፡

ላለፉት አራትና አምስት ዓመታት የነበሩትን የፍትሕ ዕጦት ከግምት ውስጥ በማስገባት ብዙ ነገሮች ለቀቅ መደረጋቸውን ተናግረው፣ በየጊዜው የሚታዩት ጥፋቶችና ምልክቶች በጊዜ ካልተቀጩ ሄደው ሄደው ሕዝብን የሚጎዱ ስለሆነ ሁሉንም ነገር በማባበል መሥራት ስለማይቻልና መንግሥትም ሕግን የማስከበር ግዴታ ስላለበት፣ አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ የኦሮሚያ መንግሥት በተለይ ከቡራዩ ጥቃት በኋላ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑንና ከፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆንም በጋራ እየሠሩ መሆኑን አክለዋል፡፡

ሕግ ካልተከበረ ንፁኃንና ጉልበት የሌላቸው ደሃ ሕዝቦች ደማቸው በከንቱ ፈሶና ሕይወታቸው አልፎ ሊቀር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በነበረው ሁኔታ መቀጠል ተጠያቂነትን ስለሚያስከትል፣ ዕርምጃ እንደሚወሰድና ሕዝቡም ተባባሪ መሆን እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ ይኼ ካልተደረገ አገሪቱ የወሮበላዎች መፈንጫ ሆና ስለምትቀር፣ እዚሁ እንዲገታ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚደረግ አጠንክረው ገልጸዋል፡፡

የለውጡ ባለቤት የሆነው ወጣቱ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለው ለውጡ ባለበት እንዲቆም ሳይሆን፣ ቀጣይነት ያለው እንዲሆንና አገርን ጠቅሞ ተጠቃሚ እንዲሆን በመሆኑ፣ በሰከነ አዕምሮና ኃላፊነት በሰፈነበት ሁኔታ፣ ሁሉንም ነገር ግራና ቀኝ ማየት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የፖለቲካ አጀንዳም ሆነ ሌላ ፍላጎት ካለው ወጣቱ አጀንዳውንና ሐሳቡን ወደ መድረክ በማቅረብ ፊት ለፊት መነጋገርና መፍታት እንደሚቻልና ጊዜውም ለዚህ አመቺ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ምኞታቸውን በአቋራጭ ለማሳከት የሚጥሩ ግለሰቦች ካሉ ተሳስተዋል፤›› ያሉት አቶ ለማ፣ የሚጠቅማቸው ሰላማዊ የሆነች አገርና ሰላማዊ የፖለቲካ ንግግር ሲኖር ብቻ በመሆኑ፣ ሁሉም ኃላፊነት በተሞላበት መንፈስ መሥራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

‹‹በኦሮሚያ ያሉ ሕዝቦች የእኛው ሕዝቦች ናቸው፤›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በሃይማኖትና በዘር አንድ ሆነው በማንነት ሳይከፋፈሉ እንዲሠሩና ሕግን በማስከበርም በጋራ ከክልሉ መንግሥት ጋር እንዲሠሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በቡራዩ የተፈጠረው ችግር ባልታሰበና በድንገት በመሆኑ የፀጥታ ኃይሎች እስከሚደርሱ ጉዳት መድረሱንና ጉዳት የደረሰው በየሠፈሩና በየጢሻው በመሆኑ ቶሎ በቁጥጥር ሥር ሊውል አለመቻሉን ጠቁመው፣ መንግሥት ዕርምጃ የሚወስደው ጉዳት ባደረሱት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በተዋረድ በሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎችም ጭምር መሆኑን አቶ ለማ አስታውቀዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ በቡራዩ ከተማና በአካባቢው በተፈጸሙ ጥቃቶች እጃቸው አለበት ተብለው ተጠርጥረው ከተያዙ ግለሰቦች የባንክ ሒሳቦች ውስጥ ስምንት ሚሊዮን ብር መገኘቱን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ፡፡ የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ማክሰኞ መስከረም 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ማምሻውን በሰጡት መግለጫ፣ ለጥፋት ከተንቀሳቀሰው ኃይል ቡድን 99 አባላት መካከል ስድስቱ ሦስት ክላሽኒኮቭ ጠብመንጃዎችና ስምንት ሽጉጦች፣ ሁለት ተሽከርካሪዎች፣ የባንክ ሒሳብ ደብተሮች፣ በተጨማሪም የቡራዩ ከተማ መሬት አስተዳደር ሐሰተኛ ማኅተም ይዘው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ግለሰቦቹ እጅ ላይ ሐሰተኛ ገንዘብ መያዙን አክለዋል፡፡

ሰዎችን በመግደልና በዝርፊያ ተጠርጥረው ከተያዙት ከ200 በላይ ግለሰቦች ላይ ምርመራው እየተጠናቀቀ በመሆኑ በ23 ተጠርጣሪዎች ላይ በፍርድ ቤት ክስ እንደሚመሠረት፣ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን አድኖ ለመያዝ ፖሊስ በክትትል ላይ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ከኅብረተሰቡ ጋር በመወያየት ከ300 በላይ ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያቸው እንደሚመለሱ ማድረጉን ገልጸው፣ ንብረታቸው የተዘረፈባቸውም እየተመለሰላቸው ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ጄኔራል ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል መስከረም 5 እና 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የደረሰውን ሞት፣ አካል ጉዳት፣ ንብረት ዘረፋና ውድመት አስመልክተው እንደተናገሩት፣ በቡራዩ ከ300 በላይ ተጠርጣሪዎችና ከአዲስ አበባ ደግሞ ከ200 በላይ ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል፡፡ በቡራዩ አካባቢ የተፈጸመው ወንጀል ከአዲስ አበባና ከሌላ ቦታ ወጣቶችን ገንዘብ በመስጠትና በመመልመል ያሰማሩ አካላት አሉ፡፡ በቡራዩ የተገደሉ ሰዎች ብዛትን ኮሚሽነር ዘይኑ ባይናገሩም፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፣ 23 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በቡራዩና አካባቢው የደረሰውን ግድያ፣ አካል ማጉደልና የንብረት ዝርፊያ ለመቃወም፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተነሳ ሰላማዊ ሠልፍ ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ተደርጎ ነበር፡፡ ሕዝቡ በአራት ኪሎ፣ በፒያሳ፣ በመርካቶ፣ በመስቀል አደባባይ፣ በፍል ውኃና በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የተቃውሞ መፈክሮችን በማሰማት የሁሉም መዳረሻ ለማድረግ ወዳሰቡት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እያመሩ ሳለ፣ ከመስቀል አደባባይ በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታልና ከፍልውኃ ወደ ብሔራዊ በሚወስደው መንገድ ላይ፣ አምባሳደር ሐራምቤ ሆቴል አካባቢ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት በመፈጠሩ፣ የአምስት ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ኮሚሸነር ዘይኑም የአምስት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን አረጋግጠው፣ ችግሩ የተፈጠረው የተወሰኑ ሰዎች የአንድ ወታደር ጠብመንጃ በመንጠቃቸው የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ችግሩን የፈጠሩት ኅብረተሰቡን ለማሸበርና ችግሩ ተባብሶ እንዲቀጥል ለማድረግ የተሰማሩ ኃይሎች መሆናቸውንና ቦምብ ጭምር ይዘው እጅ ከፍንጅ የተያዙ መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡ በተለይ በፒያሳና በመርካቶ ዝርፊ ለመፈጸም የተሰማሩ ጭምር በፖሊስ ተለይተው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ የተጀመረው ለውጥ እንዳይሳካ የሚፈለጉ ቡድኖች ሰፊ ዕቅድ ይዘውና ተዘጋጅተው የፈጸሙት መሆኑንም አክለዋል፡፡ ተፈጥሮ በነበረው ረብሻና ብጥብጥ ፖሊስና የፀጥታ ኃይሉ ተረባርቦ በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን ጠቁመው፣ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስም በመጠቀም ችግሩ ወደ ብሔር ግጭት እንዲሸጋገር ለማድረግ የተሰማሩ ግለሰቦች ያሉበት መሆኑን፣ ኅብረተሰቡ ሊገነዘብ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ወጣቱ መታለል እንደሌለበትና ሰለባ ከመሆን ራሱን መጠበቅ እንዳለበትም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ አንድም ሰው ላይ ጉዳት እንዲደርስ እንደማይፈልግና ‹‹መገዳደል ይብቃን›› ብሎ ወደ ሰላም በመሄድ ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ እኩይ ተግባር ያላቸው እንደማያዋጣቸው አውቀው ወደ ራሳቸው እንዲመለሱ አሳስበዋል፡፡ በተፈጸመው ወንጀል ላይ ትስስር ያላቸው በሙሉ ፖሊስ በማሰስ ለሕግ እንደሚያቀርብና ከዚህ በኋላ አስፈላጊውን ዕርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል፡፡

የሕግ ጥሰትና የሥርዓት አልበኝነት ባህሪ ያላቸውን ድርጊቶች እንደማይታገሱ የገለጹት ደግሞ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔና የደኢሕዴን ሊቀመንበር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ናቸው፡፡ በቡራዩ የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ስለሞቱ ሰዎች፣ ተጎጂዎች፣ ደኅንነታቸው ተጠብቆ ስለሚቀጥልበት ሁኔታ ራሱን የቻለ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጉዳዩን በፍጥነት ለመቅረፍና መልሶ ለማቋቋም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ድርጊቱንም አውግዘዋል፡፡

በቡራዩ የደረሰውን ግድያ፣ አካል ማጉደልና ንብረት ዘረፋ በመቃወም ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ የወጡ ሰዎች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ መንግሥት ሕዝቡን እየጠበቀ አይደለም፡፡ የደኅንነት ተቋም ሠራተኞች ወንጀሉ ከመፈጸሙ በፊት ደርሰው ማክሸፍ ነበረባቸው ብለው፣ ድርጊቱ በተጀመረበት ዕለትም በአካባቢው ፖሊስ ፍጥኖ መድረስ ሲገባው ባለመድረሱ ጉዳቱ ሊባባስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የአንድ አገር ዜጎች በመሆናቸው፣ ተዘዋውረው የመኖርና ንብረት የማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብት እያላቸው፣ እንዲህ መደረጋቸው አሳዛኝ መሆኑን፣ መንግሥትም ሕዝቡን ከደረሰበት አደጋ አለማትረፉ አሳፋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁንም መንግሥት ወንጀለኞችን መያዝ ብቻ ሳይሆን በአስቸኳይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስድና ዋስትና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ማክሰኞ መስከረም 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በወጣው መግለጫ ከአሁን በኋላ መንግሥት ሕገወጥነትንና ሥርዓተ አልበኝነትን እንደማይታገስ እስታወቆ፣ የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ አስፈላጊውን ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡

Filed in: Amharic