>

ፍቅርና ህግ በዶ/ር አብይ አስተዳደር (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

ፍቅርና ህግ በዶ/ር አብይ አስተዳደር

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ (ኮተቤ  ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ)

ዜጎችን በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በትህትና መምራት መልካም ነገር ቢሆንም  የህግ የበላይነት ግን ሊከበር ይገባል፡፡ ስለሆነም ሰዎችን በፍቅር መምራት እና ማስተዳደር የተገባ ቢሆንም የሰው ልጅ ሁል ጊዜ በፍቅር ሊመራ አይችልም እናም የህግ የበላይነት እንዳለ ማሳወቅ ተገቢ ነው፡፡

ሰው ፍቅርን በሚያሳይበት ማንነት የከፋ ባህሪንም ስለሚያሳይ  ሰው ከባህሪው ውጭ በሆነ ማንነት ሲንቀሳቀስ በህግ ሊገዛ እንደሚችል ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ የሰው ባህሪ ለኃጢያት የተመቸ ነው፡፡ በምድር ላይ በሚያደርገው ምልልስ ህግ እስካላረቀው ድረስ ፍቅርና ይቅርታ ብቻውን በሁሉም ሰው ላይ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም ምክንያቱም ሰው የተያዘበት እና ሊያዝበት የሚያስችሉ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡

ለሃያ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ለተፈጸሙት በደሎች ወንጀለኞች ይቅርታ ሳይጠይቁ ይቅርታ ተደርጎላችኋል ማለት የይቅርታን ትርጉም የሚያሳጣው ይመስለኛል፡፡ በተበዳይና በበዳይ መካከል በዳይ በተበዳይ ላይ ያደረሰውን በደል ተገንዝቦ በሰራው ስራ ተጸጽቶ በጥፋቱ ቀጥሎበት እያለ ይቅርታ አድርገናል ማለት አንድም ተበዳይ አቅም አልባ ነው ወይም የህግ ስርዓቱ በዳይን ለፍርድ ሊያቀርበው አልቻለም ማለት ነው፡፡ የተበዳይን ህመም በዳይ ካልተሰማው፡ በዳይ በወንጀሉ ካልተጸጸተ ይቅርታ ፍሬ አልባ ነው፡፡ ለሃያ ሰባት ዓመታት አሰቃቂ ወንጀሎችን ፈጽመው አሁንም በተላላኪዎች ወንጀልን መፈፀም ቀጥለውበት እያለ በይቅርታ ማለፍ የይቅርታን ትርጉም የሚያሳጣው ይመስለኛል፡፡

ዶ/ር አብይ አህመድ ስልጣን ከያዘበት ግዜ ጀምሮ የሚናገራቸው ቃላት የፍቅር፣የይቅርታ፣የመደመር መሆናቸው መልካም ሆነው እያለ መደመር ለማይችሉና፣ ፍቅር ለማያውቁ፣ ይቅርታ ለሌላቸው ሰዎች የህግን የበላይነት ማሳየት አስፈላጊ ነው ብየ በአያሌው አምናለሁ፡፡ ስለዚህ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ለተፈጸሙና እየተፈጸሙ ለሚገኙ አሰቃቂ ወንጀሎች ድርጊት ፈጻሚዎች እና አስፈፃሚዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፡፡

Filed in: Amharic