>
5:50 pm - Wednesday January 26, 2022

ህወሀት ስጋው አልቆ፡ ደሙን ጨርሶ ዛሬም  በእጅ አዙር ትንቅንቁን ተያይዞታል!!! (መሳይ መኮንን)

ህወሀት ስጋው አልቆ፡ ደሙን ጨርሶ ዛሬም  በእጅ አዙር ትንቅንቁን ተያይዞታል!!!
መሳይ መኮንን
የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባዔ በጂማ እየተካሄደ ነው። ጠ/ሚር አብይ አህመድ አስደናቂ የሆነ ንግግር ማድረጋቸውን ትርጉሙን ካካፈሉኝ ወዳጆቼ ተረድቼአለሁ። ቀሲስ ኤፍሬም በፌስ ቡክ ገጻቸው የዶ/ር አብይን የዛሬ ንግግር እንዲህ ቀንጭበውታል
«እሳት ውስጥ ቆመን፣ ስድቡን ሁሉ ችለን፣ ትግሉን ከዳር አድርሰነዋል። ኦሮሞ ከለቅሶ መውጣት አለበት። …. ይህ አገር ያለ ኦሮሞ አገር መሆን አይችልም። ለኦሮሞ ኢትዮጵያ ብቻ ትጠበዋለች። አፍሪካንም መገንባት ይችላል ብለን ተነሥተናል። … ረጅም መንግድ እንድንሄድ ከፈለጋችሁ ይቺን አገር የመገንባት ኃለፊነት እንዳለብን እንወቅ። …. አድዋ ላይ ማን ነው ያሸነፈው? … ይህንን አገር ለማን ትተን ነው የምንመለሰው? አንመለስም»
“ከዚህ በኃላ በኦሮሞ ህዝብ ስም መነገድ የለም። ኦሮሞ የሞተላትን ሃገር ጥሎ ወዴትም አይገነጠልም። ኦሮሞ ከኢትዮጵያ ውጭ ሃገር የለውም አይኖረውም። ኢትዮጵያ ብዙ አባቶቻችን ከአድዋ ጀምሮ ዋጋ የከፈሉባት ሃገራችን ነች። አንዳንዶች ጠዋት ስለ አንድነት አብሮነት እያወሩ ማታ ሃገር ስለማፍረስ ይዶልታሉ። መደመር እንደዚ አይደለም።የኦሮሞ ህዝብ ወላዋዮችን ይጠየፉል። የምትበተን ኢትዮጵያ ይለችም። ኦሮሞ ባህሉ ማቀፍ እንጅ ጥላቻ ዘረኝነት አይደለም። “
ጠ/ሚር አብይ ሌላም ድንቅ ንግግራቸውን ተከታትዬአለሁ። ኦሮሞ ወላዋይ አይደለም ብለዋል። ጠዋት ስለአንድነት እያወሩ ሌሊት ልዩነትን የሚጎነጉኑትን ግለሰቦችና ድርጅቶችን እስከዶቃ ማሰሪያቸው ነገሯቸው የሚያስብል ነው። በኦሮሞ ስም የሚነግዱትንም ተዉ አይበጅም ብለዋል። እንግዲህ ሙሉ ትርጉሙ እስኪደርሰን መጠብቅ ግድ ነው። ዶ/ር አብይ በሰሞኑ የፈንግጪው ፍለጪው ፖለቲካ ደስተኛ እንዳልሆኑ ከንግግራቸው መታዘብ ይቻላል። የቡራዩ ተፈናቃዮችን በጎበኙ ጊዜ ንዴታቸውን እንኳን መደበቅ አልቻሉም። ”ይሀው ደማቸውን ጠጡ” ሲሉ ድንግጥ ነው ያልኩት። የጨለማው ዘመን እድምተኞች በሚፈጽሟቸው የጥፋት ተግባራት ምን ያህል ስሜታቸው እንደተነካ በግልጽ መረዳት ይቻላል።
በጂማው የኦህዴድ ጉባዔ ላይም ያን ስሜታቸው በቀላሉ ከፊት ገጻቸው ይነበባል። በፎቶ ግራፉ ላይ እንደሚታየውም ዶ/ር አብይ በሰሞኑ የጥፋት ህይሎች መረን የለቀቀ ጭካኔያዊ ተግባር የተነሳ ደስታ ርቋቸዋል። እልህም ይታይባቸዋል። በፍቅርም ይሁን በህግ እነዚህን የትውልድ ስንክሳሮችን አደብ ማስገዛት አለባቸው። ምንም እንኳን እሳቸው የፍቅሩንና የሰላሙን መንገድ የሚመርጡ ቢሆንም ፍቅርና ይቅርታ ለማይገባው አርጩሜ እንደሚያስፈልገው የሚጠፋቸው አይመስለኝም። ምከረው ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው እንዲሉ። ወይም ለእምቢተኛ በሚገባው ቋንቋ አናግረው እንደሚባለው።
ዶ/ር አብይ ቢቆጡ ልክም ናቸው። ስሜታቸው ቢጎዳ ያለምክንያት አይደለም። ደስታ ከፊታቸው ቢርቅ ሊያስገርም አይገባም። በጠንካራ ቃላት ቢጋረፉም አይፈረድባቸውም። ወደ ገደል ልትገባ ከአፋፉ የደረሰችን ሀገር በፍቅርና ይቅርታ ከመለሷትና ኢትዮጵያውያንም በተጀመረው የለውጥ ሂደት የምስጋና ቃል ከአፋቸው ወጥቶ ሳያልቅ በዘር ፖለቲካ ያበዱ ጥቂት ጽንፈኞች ወደኋላ ሊመልሱ እንቅልፍ አጥተው ማደራቸው የሚያሳዝንም የሚያሳፍርም ነው። ለፍቅር ጀርባቸውን የሰጡ፡ አንድነትን የሚጠየፉ፡ ጥላቻ መፈክራቸው የሆነ፡ ልዩነትን እንደምግብ የሚወስዱ የትውልድ ድዊዎች ጥምረት ፈጥረው የተነሱባት ሀገርን መምራት በእርግጥ ከባድ ነው።
 ለዶ/ር አብይና ለመንግስታቸው የተደቀነው ፈተና ቀላል የሚባል አይደለም። ህወሀት ስጋው አልቆ፡ ደሙን ጨርሶ፡ በአጥንቱ በቀረበት በዚህን ወቅትም ቤተመንግስት ለመግባት የሚያደርገውን የእጅ አዙር ትንቅንቅ በቅርበት እየታዘብን ነው። የመንፈስና የዓላማ ልጆቻቸው የሆኑ የዘመኑ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞችም የጥፋት ሰይፋቸውን እያፏጩ ተነስተዋል። ኢትዮጵያ በአጭሩ መንታ መንገድ ላይ ቆማለች። ወይ እንደኮሶ ሽሮላት መርዘኛውን የጎሳ ፖለቲካ ትገላገለዋለች። አልያም………..
በነገራችን ላይ የጠቅላይ አቃቤ ህግ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ሰሞኑን ከቀልባቸው ያሉ አልመሰለኝም። የተቀመጡበትን ወንበር፡ የያዙትን ሀገራዊ ሃላፊነት የሚቃረን፡ ፍጹም ወገንተኛ የሆነ፡ ስሜት የሚጋልበው አስተያየት በተደጋጋሚ ሲሰጡ እየታዘብን ነው። የሚሉት ነገር እውነት እንኳን ቢሆን ለወንበርና ሃላፊነታቸው ክብር ሲሉ ከእንደዚህ ዓይነት ግልብ አስተያየት እንዲቆጠቡ ከአጠገባቸው ያሉ ወዳጆቻቸው ቢመክሯቸው ጥሩ ነው። ጽናታቸውን፡ አይበገሬነታቸውን፡ ነገሮችን ለማርገብ በሚሰነዝሯቸው ሚዛናዊ መልዕክቶቻቸው የሰጠናቸውን የክብር ቦታ የሚያደበዝዝ ነገር እያየሁባቸው ነው። ከእሳቸው የማይጠበቁ ቃላትን ስመለከት ፌስቡክ ገጻቸው ተጠልፎ መስሎኝ ነበር። ኦቦ ታዬ እርሶዎ የሁሉም ነዎት። ስለሁላችንም እንዲሰሩ ይጠበቃሉ።
በተረፈ ኢትዮጵያን ለማዳን ይሉኝታ ያልሸበበው ግን ደግሞ የሰከነ እንቅስቃሴ በስፋት መደረግ ከሚያስፈልገበት ጊዜ ላይ መድረሳችንን ልብ ይሏል። የዘር ፖለቲካውን የሚያራግቡ ወገኖች አነጣጥረው እያጠቁ ያሉት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ነው። እነዶ/ር አብይና አቶ ለማ ላይ ዘመቻ የከፈቱትም የኦሮሞ ልጆች ከኢትዮጵያም የተሻገረ አህጉራዊ ህልም ይዘው በመነሳታቸው ነው። እነሱ ወደታች ወደ መንደር ፖለቲካ ሲወርዱ እነዶ/ር አብይ ወደላይ ከፍታውን በመጀመራቸው ነው:: እነዚህ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች በጠባቧ ዓለም ውስጥ የራሳቸውን ጎጥ እያደራጁ ሀገር ሊያጠፉ፡ ድምሩ ዜሮ በሆነ የፖለቲካ ቁማር ላይ ተጠምደዋል። ለዚህ እንቅፋት የሆነባቸው አንደነት፡ ኢትዮጵያ የሚሉ ነገሮች ናቸው። እነዚህን ማፈራረስ ዋናው ተግባራቸው ነው። ይህን የምናስቀረው እኛ ነን። ለዚህ ደግሞ አቅሙም ወኔውም አልከዱንም። የእነዶ/ር አብይ መንገድን በማጠናከር ኢትዮጵያን ማዳን የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳችን፡ ተግባራችን ነው።
ኢትዮጵያን እግዚያብሄር ይጠብቃት!
Filed in: Amharic