>

የሆነው ይህ ነው (አቤል)

የሆነው ይህ ነው

አቤል ዘ ሃገረ ኢትዮጵያ

ሰኞ እለት ጠዋት ሁላችንም ያየነው ሰልፍ በከተማችን ነበር፡፡ሰኞ እለት ከሰአት የሰፈሬ የፈረንሳይ ለጋሲዮን ልጆች ከቡራዩ ለተፈናቀሉ ወገኖች ገንዘብ እያሰባሰቡ ነበር፡፡ገንዘብ ልብስ የንጽህና እቃዎች ተሰብስቦ በተሰበሰበው ገንዘብ ምግብ ተሰርቶ ማክሰኞ እለት ለተፈናቃዮቹ የምሳ ግብዣ ተደረገ፡፡

ማክሰኞ ማታ ላይ ሰፈሩ ከወትሮው ቀዝቀዝ ያለ ድባብ የነበረው ቢሆንም ኳስ ለማየት ወጣሁ፡፡እዚያው ሰፈር የሚገኝ ባር ተቀምጬ የባርሴሎና ከፒ ኤስ ቪ እንዲሁም ኢንተር ከቶተንሃም ጨዋታ ተከታተልኩ፡፡ጨዋታዎቹ 1:55 ጀምረው 3:45 ላይ ተጠናቀቁ፡፡ወደ ቤቴ ለመግባት ሳኮበኩብ ከ10 የሚበልጡ ፖሊሶች ወደ ባሩ ተንጋግተው ገቡ፡፡”ና ውጣ!!” የሚል ተደጋጋሚ ጩኸት እና ዱላ ተከተለ፡፡ጥፊ ቦክስ ካልቾ የእንጨት ዱላ የጎማ ዱላ ሁሉም ዘነቡ፡፡በር ላይ የቆመው የፖሊስ ፓትሮል ላይ በጥድፊያ ጫኑን፡፡ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተላክን…በዱላ እንደተጫንን በዱላ ወረድን፡፡መኪናው ሌሎችን ሊያመጣ ተመልሶ ወጣ፡፡በግማሽ ሰአት ውስጥ ከ30 በላይ ወጣት በፖሊስ ጣቢያው በበርካታ ፖሊስ ተከብበን ተገኘን፡፡

እናቴ ከቤት ትደውላለች ግን አላነሳውም፡፡ምክንያቱም ሌሊቱን ሙሉ ፖሊስ ጣቢያ በር ላይ ቆማ ከማደር በቀር ምንም ልታረግ እንደማትችል አውቃለሁ፡፡ወንድሜ ልምጣ ወይ አለኝ፡፡እሱም ቢመጣ አብረን ከመታሰር በቀር ምንም ጥቅም ስለሌለው ‘አንተም እንዳትመጣ ለማዘርም እንዳትነግራት’ አልኩት፡፡ ከምሽቱ 5:30 አካባቢ የወረዳው ፖሊስ ኮማንደር ከሌላ የፌደራል ፖሊስ ኮማንደር እና ብዙ ፖሊሶች ጋር መጣ፡፡ቢሮ ገብተው ለደቂቃዎች ተወያዩና ሄዱ፡፡ጫማ ፍቱ ተባለ፡፡ካቴና መጣ፡፡የተወሰኑ ሊያመልጡ ይችላሉ የተባሉ ሰዎች ጥንድ ጥንድ ሆነው ታሰሩ፡፡አዳሪ መሆናችን ታወቀ፡፡

አንድ ሌሊት ሙሉ ንፋስ እየጠጣን እያወራን እየሳቅን አደርን፡፡መቼም ከአራዳ ልጅ ጋር እንኳን እስር ቤት የሰሀራ በረሃን ብታቋርጥ ሙቀቱ ሳይሆን ሳቁ ነው የሚገልህ፡፡የሌለ ፍተላ የለም፡፡ቀስ እያለ ህመሙ የሚሰማውን ዱላ እና ሃይለኛውን የፈረንሳይ ብርድ በገራሚ ጨዋታዎች ረሳነው፡፡ ጠዋት ኮማንደሩ ተመልሶ መጣ፡፡”ከአረቄ ቤት የተያዛችሁ እዚህ ጋ ተሰለፉ!” “ከሺሻ ቤት የተያዛችሁ እዛ ጋ!” “ከቅምቀማ ቤት ስትቀመቅም የተያዝክ እዚህ ጋ” ” ከመንገድ ላይ የተያዛችሁ በዚህ በኩል!” ከቤታቸው የተያዙ ለብቻቸው ተደረጉ፡፡ምዝገባ ተጀመረ፡፡ የመንግስት ሰራተኛ ካለህ ለብቻ ተባለ፡፡ለብቻችን ተቀመጥን፡፡

ከዚህ በፊት በወረዳው ፖሊስ በበጎ ተግባር የሚታወቁ ተፈቱ፡፡አንዳንዶችም በልመና እና በማስረዳት ተፈቱ፡፡እኔ ከመንግስት ሰራተኞች ጋር ነኝ፡፡ኮማንደሩ የኛን መታወቂያችንን ደጋግሞ እያየ ሌሎች ተጭነው ወደ ክፍለ ከተማው ፖሊስ ጣቢያ ተላኩ፡፡እኔን በተመለከተ አንድም መላጣ መሆኔ ሁለትም የመስሪያ ቤት መታወቂያ መያዜ ሶስትም ከወረዳው ፖሊሶች አንዳቸውም ከዚህ በፊት አይተውኝ እንደማያውቁ መናገራቸው እንድፈታ እድል ሰጥቶኛል፡፡

ከዚያ ወዲህም አፈሳው ቀንም ማታም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከቤታቸው የሚያዙም በዝተዋል፡፡እኔም 12 ሰአት ቤት ገብቼ እስከ እንቅልፍ ሰአት የETVን እና የፋናን ዜና ሳይ እያመሸሁ ነው፡፡ የአፈሳው አላማ እኔ እንደገባኝ በከተማዋ በቀጣይ ሊከሰት ይችላል ተብሎ ለተገመተ ችግር መጠቀሚያ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ስራ የሌላቸው፥ ሱስ ያለባቸው እና ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ ያለባቸውን ወጣቶች ከመንገድ ማጽዳት ነው፡፡በሂደቱ ግን በጣም ብዙ ሰላማዊ ወጣቶችም ተይዘዋል፡፡በሌላ መልኩ በፍጥነት ወደ ፖለቲካው እየተሳበ ያለውን የአዲስ አበባ ወጣት ማስደንገጥ እና ዶ/ር አቢይ ኮስታራ መሆን እንደሚችል ማሳየትም አላማው ይመስለኛል፡፡

ባለፉት 5 ወራት እንደተለመደው መግረፍ ያልቻሉ ጥቂት ‘አፍቃሪ ዱላ’ ፖሊሶችንም ማስደሰት አንዱ አላማ ሊሆን ይችላል፡፡ ለማንኛውም ፖሊስ ያሰራቸውን ሰላማዊ ወጣቶች በፍጥነት እንዲፈታ እጠይቃለሁ፡፡አብዛኞቹ በአፈሳው ሰአት እና ቦታ መገኘታቸው ብቻ ነው ጥፋታቸው፡፡ለሌሎች መጠቀሚያ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ ወጣቶችም በምክር እና ማስተማር እንጂ በዱላ እና በሀይል እንዳይያዙ አሳስባለሁ፡፡

Filed in: Amharic