>

ቡራዩ ከተማና አካባቢው በዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃትና ሀላፊነታችን (አበጋዝ ወንድሙ)

ቡራዩ ከተማና አካባቢው በዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃትና ሀላፊነታችን

አበጋዝ ወንድሙ

ቡራዩ ላይ የደረሰው የህይወት መጥፋትና መፈናቀል እጅግ አሳዛኝ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። አንድም ዜጋ ከማንነቱ ጋር በተያያዘ  ጥቃት ሲደርስበት እንደ ሰው፣ እንደ ዜጋ ሊያመን ይገባል።

ቡራዩ ላይ የተከናወነውን ግድያና የህዝብ በገፍ መፈናቀል ፣ባለፉት አመታት ሀገራችን ውስጥ እየታየ ካለው መጠነ ሰፊ ግድያና መፈናቀል ልዩ የሚያደርገው ነገር ቢኖር አዲሱ ባለተራ አካባቢ መሆኑ ብቻ ይመስለኛል።

ባለፉት 27 አመታት አንድ ከሚያደርጉን እሴቶችና ዜጋዊ ትስስር ይልቅ ልዩነታችን ላይ ያቀነቀነ ፖሊሲ በመላው ሀገሪቱ ውስጥ በመነዛቱ የሀገራችን ህዝብ በየጊዜው በሚቀሰቀሱ ግጭቶች አማካይነት እንግልት፣ ሞትና ከቀዬው መሰደድ፣ ዕጣ ፈንታው ይመስል የዚህ ሰለባ ሲሆን ቆይቷል።

ጉራ ፈርዳ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣አማራ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልል፣ ቁጥሩ ይለያይ እንጂ ዜጎች የዚህ መርገምት ሰለባ የሆኑባቸው ስፍራዎች ናቸው።

በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ፣ በአካባቢ ህብረተሰብ በበጎ አድራጊ ድርጅቶችና በመንግስትም እርጥባን ጭምር አየታገዙ  ኑሮአቸውን ! እንዲገፉ የተገደዱ 1.5 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ሲኖሩ፣ በተለይ ድቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ውስጥ ያለውን ብጥብጥ በመሸሽና እንዲሁም ከኤርትራ መንግስት አፈና በመሸሽ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ 920,000 በላይ ስደተኞች ይገኛሉ።

ይሄን ያህል ሃገራዊ እዳ የተሸከምን መሆኑን በመዘንጋት በሚመስል መልኩ፣ ህዝባችን ላይ በቡራዩ የደረሰውን ጥፋት ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል እሽቅድምድም ተገብቶ ጣት መቀሳሰር በእጅጉ አሳፋሪ ነው።

ድርጊቱን ማንም የተደራጀ የወሮበላ ቡድን ይፈጽመው ወይንም ግለሰቦች  ፈጸሙት የሁሉም ሃላፊነት መሆን ያለበት፣  ያለ አንዳችም ማንገራገር ድርጊቱን ማውገዝና የመንግስት አካላት ጉዳዩን በአስቸኳይ መርምረው በወንጀሉ የተጠረጠሩትን ለፍርድ ያቀርቡ ዘንድ ጫና ማሳረፍ ነው።

ይሄ እስኪሆን ድረስ ደግሞ የተጎዱትን ወገኖች  ባካባቢው ካለው ህዝብና የመንግስት አካላት ጋር በማቀናጀት ሊደረግ የሚቻለውን ጊዜያዊ ድጋፍ ለማድረግ  መረባረብ፣ በሂደትም ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ኑሮአቸው የሚመለሱበትን መንገድ ለማመቻቸት መስራት ነው።

በዘላቂነትም አንድ የሚያደርጉንና የሚያስተሳስሩን እሴቶችን ማጎልበት ላይ በመስራት ሌላ ቡራዩ እንዳይከሰት የዜግነት ግዴታችንን መወጣት፣ በትንሹም ቢሆን ቡራዩ ላይ እንባቸው የፈሰሰ ወገኖችን ለማበስ ስለሚረዳ ትኩረት ብንሰጠው የተሻለ ነው።

 

አበጋዝ ወንድሙ

Filed in: Amharic