>
5:14 pm - Friday April 20, 8992

ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢህአዴግስ አፋኝነቱን ይቀይራልን ? 

ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢህአዴግስ አፋኝነቱን ይቀይራልን ? 
መሳይ መኮንን
 ፖሊስ የምርመራውን ሂደት ጨርሶ ውጤቱን እስኪያሳውቅ መጠበቁ የተሻለ በሆነ ነበር። እንደቀድሞው የህወሀት አገዛዝ የነበረው ዓይነት የፖሊስ የውሸት ድራማ አሁን እናያለን ብዬ አልጠብቅም። ነገር ግን  ከጥቃቱ ጀርባ ያለው ‘አከሌ ነው’ የሚል ጆሮ የሚያደነቁር ጩሀት ስሰማ ”የሚካዔልን ግብር የበላ ያስለፈልፈዋል” የሚለው አባባልን አስታወሰኝ።
 በእንዲህ ዓይነት ድራማ ህወሀት 27 ዓመት ኖረበት። ጡጦ የሚጠባ ህጻን ማሳመን አቅቶት ከእነአሳፋሪ ታሪኩ መቀሌ ተወሸቀ። አሁን ደግሞ ተረኛ ነን ብለው ለራሳቸው የንግስና አክሊል ደፍተው የሚጮሁ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች በሚዘዉራቸው ሚዲያዎችና በግል መድረካቸው ለቡራዩ ዕልቂት የጦስ ዶሮ ፈልገው ለማላከክ ዳገት እየቧጠጡ፡ ድንጋይ እየፈነቀሉ ሳያቸው አሳዘኑኝ።
ግጥምና ዜማ ቀይረው በሌላ አዲስ ስልት ቢመጡ ለጊዜው ይደመጡ ነበር። ከህወሀት ድራማም ያነሰ፡ ደረጃውን ያልጠበቀ፡ አማተር ስክሪፕት ጽፈው ማይክ ጨብጠው ሲደሰኩሩ ”ግድየለም ለፖሊስ ምርመራ እድል እንስጥ” ከማለት ውጪ ሌላ ማለትም አያስፈልግም። እነበረከት ስምዖን በኢቲቪ ድራማ ጽፈው ራሳቸው እየተመለከቱ ሲዝናኑ፡ ራሳቸው የጻፉት ድራማ ለራሳቸው አሳምኗቸው እውነት ብለው ተቀብለው ሲኖሩ እንዳልነበር የዛሬዎቹ አክሮባቲስቶችም በጻፉት ድርሰት እየፈነደቁ፡ ሲቦርቁ እያየን ነው።
የዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመምጣቱ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ ብሄር ጾታና ሀይማኖት ሳይለይ “የለውጥ ሀይል” ለሚባለው ስብስብ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ሰጥቷል። በዚህ የድጋፍ መአበል የአዲስ አበባ ህዝብ ፈር ቀዳጅ ሚና ከመጫወት ባለፈ በሰኔ 16’ቱ የቦንብ ፍንዳታ የህይወት መስዋእትነት መክፈሉ የቅርብ ጊዜ ትውሳት ነው።
ዶክተር አብይ መድረክና ማይክ ባገኙባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ መላው የኢትዮጵያን ህዝብ በእኩልነት ለማስተዳደር እና ወደ ዴሞክራሲ እያመራን እንደሆነ ቃል ሲገቡ ከርመዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ በተወሰዱ ተጨባጭ እና አዎንታዊ እርምጃዎች ተስፋችን ፍሬ እያፈራ ህልማችን እውን እየሆነ የመጣ የመሰለን ኢትዮጵያውያን  ቁጥር እልፍ አእላፍ ነበርን።
ይሁንና  በቡራዩ የተካሄደውን እልቂት አስከትሎ ወንጀለኞችና ተባባሪዎችን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ለተፈናቃዮች መሸሸጊያ በሰጡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የጅምላ እስር እየተካሄ ነው። ይህ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት ከዶክተር አብይ አስተዳደር የማይጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለማመን የሚያስቸግር አስደንጋጭ ክስተት ነው። ከሁሉ በላይ ግን ነገሩን አሳዛኝ የሚያደርገው :-
1.  በቡራዩ ህግና ስርአት የማስከበረ ግዴታ የነበረበት የመንግስት አካል እስካሁን ተጠያቂ አልሆነም።
2. የቡራዩን ጭፍጨፋ ለማጣፋት በሳሪስና መርካቶ 43 ኦሮሞዎች ተገድለዋል (በገጹ ላይ ወደ 60 አሳድጎታል) ብሎ የሀሰት ዜና የፈበረከው ጀዋር መሀመድ እስካሁን ተጠያቂ አልሆነም።
3. በቡራዩ ጭፍጨፋና ውድመት ፈጽመው በኩራት ሰልፊ ፎቶግራፍ ማህበራዊ ሚድያ ላይ የለጠፉ ወጣቶች (ስለሰሩት ወንጀል የጠየቃቸው አካል ባለመኖሩ) እስካሁኗ ደቂቃ ኦንላይን ይገኛሉ።
እነዚህ ሁሉ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሀላፊነታቸውን ያልተወጡና ሆን ብለው ጠብ የሚጭሩ (የሀሰት መረጃ እየፈበረኩ ህዝብ ከህዝብ የሚያጋጩ) አካላት ባልተጠየቁበት ሁኔታ የአዲስ አበባ ወጣቶችን እያሳደዱና በጅምላ እያፈሱ ለእስር መዳረግ ችግሮችን ያባብሳል እንጂ መፍትሄ ሊሆን አይችልም።  ይህ የተለመደ ኢህአዴጋዊ አንባገነንነትና ጸረ አዲስ አበባ አቋም በማንኛውም ጤነኛ ዜጋ መወገዝ አለበት!!
በተጨማሪ በዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ዙሪያ የዶክተር አብይ አገዛዝ  በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህዝብ ማብራሪያና መፍትሄ ካልተሰጠ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢህአዴግ አፋኝነቱን ይቀይራልን ? ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን።
Filed in: Amharic