>
11:31 am - Sunday May 22, 2022

ጠ/ሚ አብይ ሆይ – ከአዲስ አበባ ወጣት ላይ እጅህን አንሣ!!! (እሰፋ ሀይሉ)

ጠ/ሚ አብይ ሆይ – ከአዲስ አበባ ወጣት ላይ እጅህን አንሣ!!!
እሰፋ ሀይሉ
የአዲስ አበባ ልጅ ቡራዩ ላይ እንዳየናቸው አንዳንድ የቄሮ ነውጠኞች ፥  የሰው ቤት ሰብሮ የሰው ነፍስ የሚያጠፋ ወጣት አይደለም፡፡ ሠርቶ ለፍቶ ፥  ከሁሉም ተስማምቶ ኗሪ ነው !!
 
የአዲስ አበባ ወጣት ፥ ፎቅ ቤት ሠርተህ ሥጠኝ አላለም!! ተወኝ ልሸቅልበት ፥  ተዉን  ኑሮአችንን እንኑርበት ባለ እንደ ሽብርተኛ ጅምላ እስር ለምን? ግን ለምን?
የአዲስ አበባ ወጣት ፥ እንግዳ ተቀብሎ ማስተናገድ የሚያውቅ ፥ እንኳን የናንተን ቄሮዎች ፥ የጠላትነት ስሜት ሊሰማው ይችላል ተብሎ የሚጠበቀውን ፥  የያኔዎቹን የወያኔና ሻዕቢያ ፀጉራቸውን ያንጨበረሩ ታጋዮችም ፥ አስፋልት ላይ ወጥቶ ፥ ኑ ግቡ እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ ተቀብሎ ሽንፈቱንም እንግዶቹንም በሠላምና በትዕግስት ያስተናገደ ፥ ታላቅ ጨዋ ሕዝብ ነው፡፡
ይህ የአዲስ አበባ ወጣት ፥ አህያ እየነዱ ፥ ተዋጊ በሬ እየነዱ ፥ ወይም አትክልትና አጣና አሸክመው ፥ በከተማ መኪኖች መሐል የሚርመሰመሱ የአዲስ አበባ ዙሪያ ገጠሬ ነዋሪዎችን ራሱ ፥ ባላገርነታቸው ግር ሣያሰኘው ፥ ከተሜነቱ ግር ሣያሰኛቸው ፥ በሠላም ተከባብሮ ፥ በሠላም ተቀብሎ በሠላም የሚሸኝ ፥ ጨዋ ሰው አክባሪ ወጣት ነው የአዲስ አበባ ወጣት፡፡
የአዲስ አበባ ወጣት ፥ ወንዱን ሴቱን አክባሪ ፥ የ3.2 ሚሊየን ዓመት ዕድሜ ያላትን የአፋሯን ሉሲንም አክብሮ ተቀብሎ በጉያው የሚያኖር ፥ የ2 ወር ዕድሜ ያላትን የሣዑዲዋን ሶፊያንም ከመጣችበት ሀገር በሠላም ተቀብሎ በሠላም የሚሸኝ ፥ የቴዲ አፍሮን ባለቤትም ፥ የአብይ አህመድን ባለቤትም ፥ የጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሣለኝን ባለቤትም ፥ የሼህ አላሙዲንን ባለቤቶችም ፥  ሌላ ቀርቶ የጠ/ሚ መለስ ዜናዊን ባለቤትም ፥  ሁሉንም በታላቅ ፍቅርና አክብሮት ተቀብሎ ፥ ቀዳማይት እመቤት እያለ በሠላም በፍቅር የሚያስተናግድ ፥  ሰው አክባሪ ፥  ከሁሉም ጋር መስሎ ኗሪ ፥  እውነተኛ የኢትዮጵያ የአራዳ ልጅ ፥  ነቄ ኢትዮጵያዊ ፥  ሕብረብሔራዊ ሕዝብ ነው የአዲስ አበባ ወጣት!!!
እና ይሄን ወጣት ፥  ምን አድርግ ነው የምትሉት??!! የእናንተን ቄሮዎች ለምን አበባ ይዞ ወጥቶ ናጋ-ቡልተን ብሎ አልተቀበለም ብላችሁ ፥ የንግሥናችን ክብር ተነካ ብላችሁ ፥ ጊዜ በሠጣችሁ ፖሊስና ወታደር ፥ ጊዜ በሠጣችሁ ሥልጣንና የፀጥታ ኃይል ተጠቅማችሁ እያፈሣችሁ ማሠር ታላቅ ቁምነገር ፥  ታላቅ የሥልጣን ማንነት መገለጫ አድርጋችሁ ወሰዳችሁት ማለት ነው??!! ተዉ ተመከሩ!!! የአዲስ አበባ ወጣት ላይ የዘረጋችሁትን የንቀትና የጉልበት እጅ ሰብስቡ!!! የጅምላ እስራችሁንና ማሸማቀቃችሁን አቁሙ!!!
ብዙዎቻችን እንደምናየው ፥ ጠዋት ማታ ስንኖር እንደነበርነው ፥  እንደምንመሠክረው ፥ የአዲስ አበባ ወጣት ማንም ላይ አልደረሰም ፥  ደርሶምም አያውቅም፡፡ በፍቅር የመጡበትን በፍቅር አስተናግዶ ፥  በፀብ የመጡበትን እዚያው በዚያው የሆነ ፥ ከዚያም ዕለቱን የማያልፍ የአራዳ ልጅ ፀብ ተጣልቶ የሚያሣልፍ ‹‹የአሁን›› ዘመን ወጣት ነው፡፡ ለምን ከኛ ቄሮዎች ጋር ተጣላ ነው? ከሆነ ተጣልቶ ዕለቱን አሣልፎታል፡፡ ረስቶታል፡፡ ከዚያ ወደ ‹‹ሙድ››ና ቀልድ ነው የሚሸጋገረው፡፡ የአዲ አበባን ወጣት እኛ ስናውቀው ፥  እናንተ ምን ፍጠር ነው የምትሉት??!!
የአዲስ አበባ ልጅ እንደ አንዳንዶቹ ፥ ቡራዩ ላይ እንዳየናቸው አንዳንድ የቄሮ ነውጠኞች ፥  የሰው ቤት ሰብሮ የሰው ነፍስ የሚያጠፋ ወጣት አይደለም፡፡ ሠርቶ ለፍቶ ፥  ከሁሉም ተስማምቶ ኗሪ ነው ፥  የአዲስ አበባ ወጣት!!
ለዚህ ከድንቅነሽ ሉሲ እስከ ሮቦቷ ሶፊያ ህያው ምስክር ናቸው፡፡ እንግዳ ተቀባዩን ፥  ሰው አክባሪውን የአዲስ አበባ ወጣት ፥ ለቄሮ አጉል አጋርነትን ለማሣየት ሲባል ፥  ያለህግ በጅምላ ማፈስ ፥ ማዋከብ ፥  ማሸበር ፥ ማሠር ፥  ማሸማቀቅ ፥ የአዲስ አበባ ወጣት ፥ ተስፋ ከጣለበት ፥  እና አብይ አብይ እያለ ለውጡን እየዘመረ አደባባይ ከወጣለት ፥  ከጠ/ሚ አብይ አህመድ የሚጠብቀው ድርጊት አይደለም!!!
እና አብይ ሆይ ፥ ልብ ግዛ፡፡ የወያኔን ድርጊት በአካል በአምሳል በስመ ቄሮ አትድገም፡፡ ህዝብህን አክብር፡፡ በሠላም የተቀመጠን ወጣት ፥  በመከባበር የሚኖርን ሕዝብ ፥  ጉልበት አለኝ ብለህ አትነካካ፡፡ አታሸብረን፡፡ ምራን፡፡ እንወድሃለን፡፡ እናከብርሃለን፡፡ ውደደን፡፡ አክብረን፡፡ ከጎንህ ነን፡፡ ምን ባጠፋን ነው እንደ ጅምላ አሸባሪ በጅምላ የምንታፈሰው?!! ተው ከመነሻህ ግፍን አታብዛ!!! ሰዎችህን አለዝብ!! ወገኖችህን ምከር!!! ነውጠኞችህን አነውር!!! ህዝቦችህን በፍቅር ምራ!!! እኛን ደግሞ ፥ ለቀቅ አድርገን!!!
የአዲስ አበባ ወጣት ፥ ፎቅ ቤት ሠርተህ ሥጠኝ አላለም!! ተወኝ ልሸቅልበት ፥  ተዉን  ኑሮአችንን እንኑርበት፥  ለቀቅ አርጉን ፥ አትረብሹ ፥ ረሃ ሆነን ፥ ከፋችም ለማችም ያቺን የለመድናት ኑሮአችንን  በሠላም እንኑርራት – እንኑርበት ፥ ተዉን ፥ ነው ያለው!! ነው ያልነው! እና እባክህ ተለመነን ፥ በሠላም የሚኖረውን ወጣት ወንድማችንን ተወው፡፡ ታናናሾቻችን ናቸው፡፡ ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ እጅህን ከወንድሞቻችን ላይ አንሣ!!!!
ሠላም ለአዲስ አበባችን !! ሠላም ለኢትዮጵያ!!! ሠላም ለአፍሪካ!! ሠላም ለዓለም ሁሉ ይሁን!!! አምላካችን ኢትዮጵያ ሀገራችንን አብዝቶ ይባርክ፡፡ የብዙሃን እናት – እምዬ ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም – በፍቅር – ትኑር!!! የሸገር ልጅ ፥ ውሎ ይግባ!!! መልካም ቀዳሚት ሰንበት!!!!
Filed in: Amharic