>

አዲስ አበባን በአክራሪው ቡድን እጅ የወደቀች እለት ጨዋታው ያበቃል!!! (መሳይ መኮንን)

አዲስ አበባን በአክራሪው ቡድን እጅ የወደቀች እለት ጨዋታው ያበቃል!!!
መሳይ መኮንን
* በቴዲ አፍሮ ለቡራዩ ተፈናቃዮች የተሰጠው አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለሚመለከታቸው እንዳይደርስ የተደረገበት ምክንያት ግራ የሚያጋባ ነው።
*  ከ30 በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች ለቡራዩ ተፈናቃዮች እርዳታ አድርሰው ሲመለሱ ታፍሰው እስር ቤት ገብተዋል።
* የቡራዩን ዕልቂት ከአዲስ አበባ በመጡ ሰዎች የተፈጸመ ነው የሚለው ጩሀት የበረከተው ለምንድን ነው? 
አዲስ አበባ የኢትዮጵያን ፖለቲካ 70በመቶ የተሸከመች ናት። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚም ከ60 በመቶ በላይ የተቆጣጠረች ለመሆኗ ግርድፍ መረጃዎች ያሳያሉ። አዲስ አበባ ላይ የበላይነት ያለው አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ግዢ አስተሳሰብ ይሆናል። አዲስ አበባን መያዝ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ደምስር መቆጣጠር ማለት ነው። ህወሀት ከትግራይ ውጭ ድርጅታዊ መዋቅሩን  ዘርግቶ ጠንካራ የህወሀት ዞን የተከለው አዲስ አበባ ላይ መሆኑ ያለምክንያት አልነበረም። አዲስ አበባ ላይ ሲመታ የሀገሪቱን ማስተር ቁልፍ ተነጠቀና ወደመቀሌ አፈግፍጎ የጥፋት ሃይል ሆኖ አረፈው።
ተረኛው የአክራሪው ቡድን የቅድሚያ ትኩረት አዲስ አበባ መሆኑ ስትራቴጂክ አካሄድ ነው። የአዲስ አበባን የቤት ስራ አስቀድሞ ለመጨረስ አቅዷል። የኦህዴድን መዋቅር በመጠቀም አዲስ አበባን እየናጣት ነው። የአንድነት ሃይል የሆነውን ክፍል ማወላለቅ የተጀመረ ይመስላል። የባለፈው ለኦነግ መሪ የተደረገው አቀባበል መልዕክቱ ግልጽ ነበር። ሰሞኑን በስፋት እየተካሄደ ያለው አፈሳ የአንድነት ሃይሉን አቅም ለማሳሳት፡ ድምፁንም ለማጥፋት የሚካሄድ ስለመሆኑ ምልክቶች እያየን ነው። በግልፅ ህዝብን ከህዝብ በሚያጋጩ ቅስቀሳዎችና ድርጊቶች ላይ የተጠመዱ ግለሰቦች ያለገደብ በነፃነት እየተንፏለሉ፡ በአንፃሩ የአዲስ አበባ ወጣቶች ኢትዮጵያዊ አጀንዳን በማራገባቸው ብቻ የሚታሰሩ ከሆነ አንዳች ፖለቲካዊ ቁማር እንዳለ ይሸተን ጀምሯል።
 የህግ የበላይነት ትርጉሙን እንዳያጣም ያሰጋል። የህወሀትን ዘመን የሚመስሉ አንዳንድ እርምጃዎች እየታዩ ነው። የእነብርሃኑ ተክለያሬድ የጨለማ ቤት እስርና በመርማሪዎች የቀረቡላቸው ጥያቄዎች ጥርጣሬን የሚጭሩ ናቸው። በቴዲ አፍሮ ለቡራዩ ተፈናቃዮች የተሰጠው አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለሚመለከታቸው እንዳይደርስ የተደረገበት ምክንያት ግራ የሚያጋባ ነው። ከ30 በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች ለቡራዩ ተፈናቃዮች እርዳታ አድርሰው ሲመለሱ ታፍሰው እስር ቤት ገብተዋል። የቡራዩን ዕልቂት ከአዲስ አበባ በመጡ ሰዎች የተፈጸመ ነው የሚለው ጩሀት የበረከተው ለምንድን ነው? የአክራሪው ቡድን የቴሌቪዥን ተቋም 24 ሰዓት የሚያላዝነው የክተት ጥሪ ዓላማውስ ምን ይሆን? እውን አዲስ አበባ ላይ የሚፈልጠውና የሚቆርጠው ሃይል ማን ነው?
አዲስ አበባ ላይ እንደጆፌ አሞራ አንዣቦ ያለው የዘር ፖለቲካ አቀንቃኝ ቡድን ደረቱን ነፍቶ “እናንተ ጩሁ እኛ ሀገር ግንባታ ላይ ነን” ዓይነት ንግግር እያሰማ መሆኑን የብሽሽቅ ፖለቲካ አካል ነው ብለን ብቻ የምንተወው አይደለም። አንዳንድ የዋህ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን አጀንዳ ወደፊት ማምጣት ይከፋፍላል፡ የተጀመረውንም ለውጥ ያደናቅፋል በሚል አፋችንን እንድንይዝ ይመክሩናል። ዝምታን ምክንያታዊ፡ የበሰለ የፖለቲካ አካሄድ አድርገውም ሰከን በሉ እያሉን እነሱ ተዝናንተው ተቀምጠዋል። የአብይ መንግስት ላይ ፍጽም መተማመን ያለው ይሀው የዝምታን ፖለቲካ የመረጠው አካል የ4ኪሎን ቤተመንግስት እርምጃ ብቸኛው መዳኛ አድርጎ በተስፋ መጠበቁን መርጧል። ለጊዜው የጠ/ሚር አብይ አህመድ መንግስት በህዝብ ግንኙነት ላይ ያተኮረው “የጥፋት ሃይሎች ሴራ ከጀመርነው የለውጥ ጉዞ አይገታንም” መልዕክትና መፈክር መሬት ላይ ካለው የአክራሪው ቡድን እንቅስቃሴ ጋር የሚመጣጠን አልሆነም።
አዲስ አበባ ኢትዮጵያዊ ቀለሟን ካጣች ነገር አለሙ ያከትማል። የአክራሪው ቡድን እያደረገ ባለው ተጽዕኖ የመፍጠር እንቅስቃሴው ከቀጠለና የሚያስቆመው ሃይል ካልመጣ ጨዋታው ያበቃል ማለት ነው። እንደስትራቴጂ አዲስ አበባን ከአራቱም አቅጣጫ በመናጥ፡ የአንድነቱን ሃይል አየር ላይ አንሳፎ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አውታሩን በመቆናጠጥ በፍጹም የበላይነት ሀገሪቱን በመዳፋቸው ስር ለማድረግ እየሰሩበት እንደሆነ በድፍረት ሁሉ መናገር ጀምረዋል።
በጠ/ሚር አብይ አህመድ አስተዳደር ተስፋ አለመቁረጥ ይቻላል። እኔም አሁንም ተስፈኛ ነኝ። ነገር ግን ነጻ የግልቢያ መንገድ የተተወለት አክራሪው ቡድን የአዲስ አበባን ዕድል እጣ ፈንታ በእጁ አስገብቶ የወደፊቱን ፖለቲካ ሊቀርጽ እየተሯሯጠ መሆኑን በአደባባይ እያዩ በዝምታ መቀመጥ ፖለቲካዊ ብስለት ነው የሚል እምነት የለኝም። ይህ አክራሪ ቡድን እየሄደበት ያለውን አደገኛ መንገድ ”የትም አይደርስም” በሚል የምንተወው ከሆነ ታሪካዊ ስህተት ላይ መውደቃችን አይቀርም። የአክራሪው ቡድን አባላት በአዲስ አበባ ላይ አተኩረው በየክልሉ መሰል ጽንፈኛ የወጣት ቡድኖችን ከማዋቀር በግልጽ ድጋፍ እስከመስጠት በመድረስ አቅማችንን ለመከፋፈልና ትኩረታችንን ለመበታተን ቆርጠው ተነስተዋል።
የጠ/ሚር አብይ መንግስት በእነዚህ አክራሪ ቡድን አባላት ላይ ዝምታን መምረጡ ለጊዜው ምርጫ የሌለው ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ሀገሪቱን በዘር ግጭት አኬልዳማ ለማድረግ ያሰፈሰፉትን እነዚህ አደገኛ ቡድኖች መናደፍ ትልቅ ፖለቲካዊ ኪሳራ እንደሚሆን ይገመታል። አንዳች እርምጃ ለመውሰድና አደብ ሊያስገዛቸው እየመከረ ከሆነ በእርግጥ እሰየው ነው። ግን እንዳይረፍድ እሰጋለሁ። እነዚህ ሃይሎች ከማይመለሱበት ፌርማታ ከደረሱ በኋላ እርምጃ መውሰዱም ከባድ ሊሆን ይችላል። የማይቀለበስ ውጤት ላይ ከደረሱ በኋላ ማልቀሱ ትርጉም አይኖረውም። የኦሮሞን ፖለቲካ ወደ መሀል በማምጣትና በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ በማስገባት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የሚሰሩ የኦሮሞ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ድምጻቸው መሳሳቱም ያሳስባል። ሰማይ ምድሩን እያደነቆረ ያለው የጥቂት አክራሪ ቡድኑ ጩሀት በተለይም አዲስ አበባ ላይ ያነጣጠረውን አካሄዳቸውን በብርቱ ልንመረምረው የሚገባ ጉዳይ ነው።
በዝምታና ይሉኝታ የተቀፈደደው የአንድነት ሃይል ቁማሩን ተበልቶ ለባለተረኛ አክራሪ የዘር አቀንቃኝ ቡድን ሀገሩን አስረክቦ ሌላ የመከራ ዘመን ከመቁጠር ከወዲሁ በጥፍሩ ቆሞም ቢሆን መገዳደር መቻል ይኖርበታል። አዲስ አበባን የወቅቱ የውጊያ ሜዳ እንዲሆን በአክራሪው ቡድን ተፈልጓል። የቅድሚያ ትኩረት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ይሁን የሚለው የጠ/ሚር አብይና የአንድነት ሃይሉ አቋም በእነዚህ አክራሪዎች እንደጅልነት ተቆጥሮ እየተደበደበ ነው። እናም ሳይረፍድ መንቀሳቀስ የጊዜው አንገብጋቢ እርምጃ ነው። አዲስ አበባን ካጣህ ጨዋታው አበቃ!
Filed in: Amharic