>
5:29 pm - Saturday October 10, 1514

ይድረስ ለሀገሬ ወጣቶች! ነገን የተሻለ ቀን ለማድረግ፤ ዛሬ ነው መተባበር!!! (ሉሉ ከበደ)

ይድረስ ለሀገሬ ወጣቶች! ነገን የተሻለ ቀን ለማድረግ፤ ዛሬ ነው መተባበር!!!
ሉሉ ከበደ
ከዘር ማንነታችን በፊት ሰብአዊ ሰውነታችን፤ ከጎጠኝነታችን በፊት ኢትዮጵያዊነታችን፤ ከሸፍጥ፤ ከተንኮል፤ ከመሰሪነታንችን በፊት ቅንነታችን፤ ከፍርሀታችን በፊት ድፍረታችን፤ እርስ በርስ ከመጠራጠራችን በፊት መተማመናችን፤ ከመፍረክረካችን በፊት በጽናት መቆማችን፤ ከልዩነታችን በፊት አንድነታችን፤ ወያኔ  ኢትዮጵያውያንን ከከተተበት መቀመቅ ውስጥ የሚያወጣን ብቸኛ መፍትሄ ከላይ የደረደርኩት ነገር ብቻ ይመስለኛል።
ነጻ አውጭ ነን የሚሉ የዘር ፖለቲከኞች፤  ህዝብ መክሮ ዘክሮ ከዚህ ዘር ነጥሉን፤ ከዚያ ዘር ለያዩን፤ ነጻ አውጡን፤ ብሎ ባይመርጣቸውም፤  በስራቸው ለማሰባሰብ ለፈለጉት ህዝብ ታሪክ እየፈጠሩ መስበካቸው እንዳለ ሆኖ፤  የቡድን የበላይነት ለመፍጠር እንዲዋጋላቸው፤ እንዲታገልላቸው ሲያደርጉም የዚያኑ ያህል የውሸት ተስፋ እየመገቡም ነው። ለምሳሌ በትግሉ ዘመን የሻእቢያ ካድሬዎችና ፕሮፓጋንዳ ሰራተኞች ዘወትር ህዝቡን ሲሰብኩ፤
ኤርትራ ነጻነቷን ስታገኝ እያንዳንዱ ኤርትራዊ ዜጋ ምንም ስራ ሳይሰራ ከወደቦች በሚገኝ ገቢ ብቻ በቀን ከሰላሳ እስከ አርባ ብር ገቢ ይኖረዋል እያሉ ይሰብኩ ነበር።  ከነጻነት በኋላ ኤርትራ የምስራቅ አፍሪካ ሲንጋፑር ትሆናለች ይሉ ነበር። እነሆ ነጻነቱ ሀያ ሰባት አመታትን አስቆጠረ፤ የኤርትራ ህዝብ በቀን ሰላሳ ብር በነፍስ ወከፍ እየታደለው ነው? ኦሮሞን ነጻ እናወጣለን የሚሉትን ሰዎች ብትሰሟቸው ወርቁ፤ ቡናው፤ ማእድኑ የብቻቸው እንደሚሆንና ከነጻነት በኋላ እንደሚበለጽጉ ነው የሚቀባዥሩት።
 ኦጋዴንን ነጻ እናወጣለን የሚሉትን ሶማሌዎች ብትሰሟቸው ጋዙ፤ ነዳጁ የብቻችን ይሆናል ከነጻነት በኋላ እያንዳንዱ ሰው ይበለጽጋል ነው የሚሉት። የብቻ ተጠቃሚነት ቅዥት፤ ስግብግብነት፤ ራስ ወዳድነት፤ በነጻነት ስም የቡድን ጥቅም የስልጣን ምኞት ቅዥት።
አንድ ህዝብ አንድ ቋንቋ ስለተናገረ፤ አንድ ባህል ስለተጋራ፤ ባንድ አካባቢ ስለኖረ፤ ምንጊዜም አብሮ በሰላም ይኖራል ማለት አይደለም። ርእዮተ አለም፤ ሀይማኖት፤ ጥቅም፤ ስልጣን፤ ንኡስ ነገድ፤ የአካባቢ ልዩነት፤ በሰው ልጆች መካከል ግጭትና አለመግባባትን፤ ብሎም ጦርነትና ፍጅትን ለመፍጠርም ሆነ ለማስነሳት በቂ ሀይል አላቸው። ሶማሌዎች አንድ ቋንቋ፤ አንድ ባህል፤ አንድ መልካምድር የሚጋሩ ናቸው።ለምንድነው አብረው መኖር ተስኖአቸው መንግስት አልባ ሆነው የቀሩት?
ታዲያ ለዚህ ትውልድ እየመሸ ነው እየነጋ? ለዚህች አገር እየመሸ ነው እየነጋ ? የጥቂት ህውሀት መሪዎችና ቅጥረኞቻቸው ህይወትና እድል እየለመለመና እያማረ ሲሄድ፤ የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ህይወት እየጨለመና እያሽቆለቆለ ሲሄድ፤ የመላው ኢትዮጵያ ወጣቶች የነገ ህይወት ጸሊም ተስፋ ተጋርዶበት፤ አስፈሪውን መጪ ጊዜ ሁላችንም እያየነው አንድ ሆነን አንድ ነገር ማድረግ የተሳነን ለምን ይሆን?
 በሚሊዮኖች ለሚቆጠረው ወጣት ትውልድ በዚህ ዘረኛ ገዢ ቡድን ምክንያት ህይወት ጭለማ ከሆነችበት፤ የተፈጥሮ መብቱን፤ የዜግነት መብቱን በጥቂት ማፊያ ቡድን ካስነጠቀ፤ የወደፊት ህይወቱን፤ እድሉን፤ የጋራ ሀገሩን ለዚህ አጥፍቶ ጠፊ የዘረኞች ቡድን መቆመሪያ አሳልፎ ከሰጠ፤ ይህ ወጣት እንዴት ለሀገሩና ለወገኑ መድህን ሊሆን ይችላል? ወጣትነት ለውጥ ፈላጊነት ነው። ወጣትነት አዲስ ነገር ናፋቂነት ነው። ወጣትነት የሀገር ተረካቢ ባላደራነት ነው።
Filed in: Amharic