>

እንደ ኢትዮጵያዊ ኖረን እንደብሔረሰብ  እየሞትን ነው!!! (በድሉ ዋቅጅራ) 

እንደኢትዮጵያዊ ኖረን እንደብሔረሰብ
 እየሞትን ነው!!!
.
በድሉ ዋቅጅራ፣ 
.
* ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ – ግልባጭ ለቲም ለማ
 
የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ አሁን ሀገራችን ውስጥ ያለውን ዝብርቅርቅ የህዝብ ስሜት፣ የፍቅርንና የመደመርን ተስፋ፣ የጥላቻንና የመበተንን ስጋት ስመለከት፣ የተቀመጡበትን መንበር ሰይጣን እንኳን ይመኘዋል ብዬ አላስብም፡፡ በመሆኑም ለሀገርዎና ለወገንዎ ሲሉ ራስዎን ከሚናወጠው ማእበል ውስጥ ጨምረው፣ ከዚህ የጥፋት ማዕበል ህዝቡን ይዘው ለመውጣት ለሚያደርጉት ደፋ ቀና ባለእዳዎ ነን፡፡
.
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የግማሽ ምዕተዓመት እድሜን ያሳለፍኩት በአምባገነን መንግስታት ጭቆናና በህዝቦች የአልገዛም ባይነት በምትናጥ ሀገር ውስጥ ነው፡፡ ወጣቶች ላልተማረው ህዝባቸው ነጻነት ሲሉ መፈክር ይዘው፣ አምባገነንነትን ሲቃወሙ በየጎዳናው ወድቀዋል፡፡ የአጼ ሀይለስላሴን ንጉሳዊ አገዛዝ የተቃወሙ ወጣቶች፣ ‹‹መሬት ላራሹን›› እየዘመሩ፣ ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው በየጎዳናው ሞተዋል፤ በወታደራዊው ደርግ ጨካኝ አምባገነን ስርአትም እንዲሁ፣ ‹‹የዲሞክራሲን›› ጥያቄ ያነገቡ ወጣቶች የቀይ ሽብር ሰለባ ሆነዋል፡፡ በቀደም በእኔና በእርስዎ ዘመን፣ በኢትዮጵያ ታሪክ አስጎምጅቶን የቀረውን የ1997 ምርጫ ውጤት መጭበርበር ተከትሎ፣ ወጣቶች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች መስዋእትነት ከፍለዋል፤ በየእስርቤቱ የዘግናኝ ቶርቸር ሰለባ ሆነዋል፤ሀገራቸውን ጥለው ሲሰደዱ የተሳካላቸው ውቅያኖሱን ተሻግረው፣ ያልተሳካላቸው የባህር ሲሳይ ሆነዋል፤ በአይሲኤስ የታረዱ ወገኖቻችንን ላይ የደረሰው በኢትዮጵያ ታሪክ በአምባገነን መሪዎቻችን የደረሰብን ጥቃት ቁንጮ እንደሆነ ለዘመናት እንዲቆይ፣ ከዚያ የከፋ በደል እንዳይደርስብን ምኞቴ ነው፡፡
ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከላይ የዘረዘርኳቸው ወጣቶች ኢትዮጵያውያን ሆነው በኖሩባት ሀገር ኢትዮጵያዊ ሆነው የተሰዉ ናቸው፡፡ ‹‹መሬት ላራሹ›› ለኢትዮጵያውያን ነበር፡፡ ‹‹ህዝባዊ መንግስት››ና የዲሞክራሲ ጥያቄ ለኢትዮጵያውያን ነበር፡፡ ‹በ1997ቱ› ምርጫ የተከፈለው መስዋእትነትም ለኢትዮጵያውያን ነበር፡፡ በቀደም ቄሮዎች፣ ፋኖዎችና ሌሎች የከፈሉት መስዋእትነትም፣ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው! ኢትዮጵያዊነት ሲያሻን የምንበትነው ገበያ አይደለም!›› በሚለው ቲም ለማ እየተመራ ለኢትዮጵያውያን የተከፈለ መስዋእትነት ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ለዘመናት ለኢትዮጵያውያን በተከፈለ መስዋእትነት፣ በእርስዎ፣ በቲም ለማና በገዱ በሚመራው የብአዲን አመራር ቆራጥ ትግልና መሪነት፣ ከሁለት አስርት በማትዘል ቀሪ እድሜዬ (ያውም ካደላት) አየዋለሁ ብዬ ያልጠበቅኩት ለውጥ አካል ለመሆን በቅቻለሁ፡፡
.
ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በኢትዮጵያ ታሪክ በህዝብ መስዋእትነት የተገኘ ለውጥ፣ ሌላ አምባገነን እግር ስር ሲገባ በተደጋጋሚ ተመልክተናል፡፡ በ66 መስዋእት ሆኖ አብዮትን ያፈነዳው ወጣት፣ ለውጡን ለደርግ አሳልፎ አስፋልት ላይ ቀርቷል፡፡ በ1983 እምቢ ብሎ ደርግን የጣለው ትውልድ፣ ‹‹ደርግን እኔ ነኝ የጣልኩት›› ለሚለው ተጋዳላይ ምቾትና ልእልና አገልጋይ ሆኖ ሃያ ሰባት አመት ኖሯል፡፡ አሁን በቄሮ፣ በፋኖና በህዝብ ትግል የተገኘው ለውጥም መርዶና ብስራቱ እየተደባለቀ፤ በፈገግታ ነቅተን፣ ሲመሽ በሳግ እናንቀላፋለን፡፡ የጀመርነው ህልም ቅዠት ሆኖ ያልቃል፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች ሰዎች እየሞቱ ነው፡፡ ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ላለፉት ሶስትና አራት ወራት የሀገራችን ፀሀይ ያለሞት ወጥታ የጠለቀችበት ጊዜ መኖሩን እንጃ፡፡ የዛሬ እናቶች ልጆቻቸው ፊታቸው ሲገደሉ ያያሉ፤ ህፃናት ወላጆቻቸው ሲገደሉ ያያሉ፡፡ የሚያሳዝነው በዚህ ለኢትዮጵያውያን ለውጥ በተከፈለ መስዋእትነት በተገኘ ለውጥ እየሞቱ ያሉ ሰዎች፣ ኢትዮጵያዊ ሆነው በኖሩበት እድር፣ ብሔረሰብ ሆነው መሞታቸው ነው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ መቼም ኢትዮጵያዊ ሆኖ መኖር ምን ማለት እንደሆነ፣ ከልቤ ነው የምልዎት፣ ከእርስዎና ከቲም ለማ በላይ የሚያውቅ የለም፤ ‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን›› ማለትስ ይኸው አይደል! ኢትዮጵያዊ ሆኖ መኖር ማለት እንደእኔ ክስታኔ ሆኖ፣ ኦሮሚያ እምብርት አሰላ ተወልዶ ማደግ ነው፡፡ አባቴ የጡት ልጅ ነበረው – ወንድማችን፡፡ ክርስቲያኗ እናቴ የአርሲዎቹን ፈጫሳ ትፈጭስ ነበር፡፡ ሙስሊሞቹ የጎረቤታችን ኦሮሞዎች መስቀልን ከእኛ ጋር ለማክበር ሲጓጉ ለጉድ ነው፡፡ … ያ ነው እንደኢትዮጵያዊ መኖር፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መኖር ሱማሌ ክልል – ጂጂጋ ላይ ኦሮሞዎችና አማሮቹ ከሱማሌዎቹ ጋር ‹‹አበሽ!›› እና ‹‹ዋሪያ›› እየተባባሉ ይኖሩት የነበረው ኑሮ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሆኖ መኖር ማለት አዋሳ ላይ ሲዳማዎችና ወላይታዎች በአንድ እድር ስር፣ የታመመ እየጠየቁ፣ የተቸገረ እየረዱ፣ የሞተ እየቀበሩ ‹‹ዳኤ ቡሽ›› እና ‹‹ሎ ዳይኤ›› እየተባባሉ የኖሩት ኑሮ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መኖር ማለት እዚህ አዲስ አበባ ጠርዝ ላይ፣ አሸዋ ሜዳ ጋሞዎችና ኦሮሞዎች ቡና እየተጠራሩ፣ ያንዱን ልጅ አንደኛው እየቀጣ – ልጆቻቸውን በጋራ ያሳድጉበት የነበረው ኑሮ ነው፡፡
.
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እነዚህ ኢትዮጵያዊ ሆነው የኖሩ ዜጎች ኢትዮጵያዊ ሆነው አልሞቱም፡፡ ጅጅጋ ላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው የኖሩት ኦሮሞዎች – ኦሮሞ ብቻ ሆነው ሞቱ፡፡ ቤንሻንጉል ላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው የኖሩ አማሮች አማራ ብቻ ሆነው ሞቱ፡፡ አዋሳ ላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው የኖሩ ወላይታዎች ወላይታ ብቻ ሆነው ሞቱ፡፡ አሸዋ ሜዳ ላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው የኖሩ ጋሞዎች፣ ሲልጤዎችና ጉራጌዎች ብሄረሰብ ሆነው ሞቱ፡፡ ጉጂ ላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው የኖሩ ጌዴኦዎች ጌዴኦ ብቻ ሆነው ሞቱ፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እንኳን ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለመሞት፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለመስደድም መንገድ ጠፋ፡፡ ሶማሌ ክልል ጥሪት አፍርተው፣ ወልደው ከብደው የኖሩ ኢትዮጵያውያን ኦሮሞ ሆነው ተሰደዱ፡፡ ቤንሻንጉል የኖሩ ኢትዮጵያውያን አማራ፣ አዋሳ የኖሩ ኢትዮጵያውያን ወላይታ… ሆነው ነው የተሰደዱት፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆነን ኖረን ብሔረሰብ ሆነን እየሞትን፣ እየተሰደድን ነው፡፡
.
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በጎሳ መጋዝ ለሀያ ሰባት አመታት በተበጣጠሰች ሀገር፣ በአመጽ የመጣን ለውጥ፣ ጠመንጃ ሳይሆን ፍቅርና ይቅርታን፣ ጥላቻን ሳይሆን መደመርን ይዞ፣ ከግብ ማድረስ እጅግ ከባድ ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህ ሃላፊነት ደግሞ ከእርስዎና ከቲም ለማ በቀር ቁርጠኛና ዝግጁ መሪ አልነበረም፡፡ ህወሀት-ኢህአዴግ ለሃያ ሰባት ዓመታት በመሰሪ የጎሳ ፖለቲካ ሸንሽኖ፣ እንደኢትዮጵያዊ እንዳንኖር ብዙ ሞክሯል፡፡ የብሔር ብሔረሰብም መብታችን ቢሆን ለእሱ ባለን አዎንታዊና አሉታዊ አመለካከት እየተሰፈረ የሚሰጠን እንጂ የሰብአዊ መብታችንን፣ የብሄረሰባዊ ድርሻችንን ያህል አልነበረም፡፡ ህወሃት-ኢህአዴግ ለሃያ ሰባት ዓመት በጥላቻና መከፋፈል የተለወሰ የብሔር ፖለቲካ አላማ በልዩነታችን ደምቀን፣ በፍቅር ተቃቅፈን ኢትዮጵያዊ ሆነን እንዳንኖር ለማድረግ ነበር፡፡ አልተሳካለትም፡፡ ይሁን እንጂ እንደኢትዮጵያዊ እንዳንኖር ማድረጉ ባይሳካለትም፣ እንደኢትዮጵያዊ እንዳንሞት አድርጎናል፤ እንደብሔረሰብ ገዳይና ሟች እየሆንን ነው፡፡
.
ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በሀገራችን ታሪክ እንደእርስዎ ህዝብ የተቀበለው መሪ አላየሁም፡፡ በ1997 የመረጠውን መሪ የተነጠቀው ህዝብ፣ አሁን ህዝብን መርጦ የመጣ መሪ አግኝቶ ሲነሳ ለምን አይደሰትም!? እንደሚያውቁት የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅር ባይ ነው፤ የአንደበትን ብቻ ሳይሆን የውስጥን ሞራ ያነባል፡፡ እርስዎን የተከተልዎት ሞራዎን አንብቦ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቃል አንድም በግብር ይገዝፋል፤ አንድም ቧልት ሆኖ ይጠፋል፡፡ በዚህ በኩል እርስዎ ቃልዎን ህያው ሊያደርጉ ተግባር – ነፍስ እፍ ሲሉበት፣ በሌላ በኩል ዝርፊያ፣ ግድያና መፈናቀል ቃልዎን ገድሎ ለመቅበር ጸረ ለውጥ ሀይሎች ጉድጓድ ይቆፍራሉ፡፡
.
ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይህ ለውጥ እንዲጠለፍ ወይም እንዲጨነግፍ በፍፁም አይፈልግም፡፡ የሚሆነው ግን ከፍላጎታችን ተቃራኒነቱ እየጠነከረ ነው፡፡ እኔም ‹‹ሾላ በድፍን›› ቢበዛ፣ ቀና ያለ አንገቴ በትካዜ እያዘነበለብኝ ተቸገርኩ፡፡ ‹‹ምን እየሆነ ነው ያለው? ፖሊሶች በቆሙበት እንዴት ሰዎች ይገደላሉ? ይቃጠላሉ? ይሰቀላሉ? የለውጡ ሀይል ያልሆነ (ያልተደመረ) ፖሊስ አለ? ኢትዮጵያዊነት የልብ ነው የከንፈር? . . . . በርካታ ጥያቄዎች ይመጡብኛል፡፡ ከህሊናዬ በምክንያት ሳባርራቸው፣ ምክንያት ከማይደርስበት ልቦናዬ ይሸነቀራሉ፡፡ እኔ ፊደል የቆጠርኩት መጠራጠር በወለደው መብሰልሰል ስወጠር፣ ያልተማሩ ወገኖቼ፣‹‹እየሞትን አንደመርም›› ብለው፣ አዲስ አበባን በሰላማዊ ሰልፍ አጨናነቋት፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ነገ፣ ከነገ ወዲያ ምን ይመጣል? በፍፁም ይህን ማሰብ አልፈልግም፡፡
.
ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የሀገሬን ሰው ለውድቀት ከሚያመቻቹት መጥፎ ባህላችን አንዱ ስም ጠርቶ መሸለም እንጂ፣ ስም ጠርቶ መርገም አለመቻላችን ነው፡፡ አንዳንዴም ቢሆን ጥሩ የሰራን በስሙ ጠርተን፣ አሞካሽተን እንሸልማለን፤ መጥፎ የሰራን ግን ስም ጠርተን አንረግምም፤ እድር አቁመን፣ ስብሰባ ጠርተን፣ ‹‹አንዳንድ ሰዎች፣ አንዳንዶቻችሁ›› እያልን ለወንጀለኛና ለግፈኛ ምሽግ ሆነን ነው የምንኖረው፡፡ ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እባክዎን በጎ የሰራን መሸለሙን ጋብ አድርገን፣ አጥፊዎቻችን በስም ጠርተን ሸንጎ አቁመን እንርገም፡፡ ይህ ህዝቡን ከጥርጣሬ፣ ለውጡን ከውጣ ውረድ ለማውጣት ይረዳል፡፡
.
ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር፡- ይህ በህይወቴ የተመለከትኩት – የተሳተፍኩበት እውነተኛ ለውጥ ነው፡፡ እንዲቀለበስ አልሻም፡፡ ለልጆቼ ፍሬውን እፈልገዋለሁ፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊም ከዚህ የተለየ ፍላጎት እንደሌለው እርግጠኛ ነው፡፡ በመሆኑም የሚከተሉትን ሀሳቦች ከግምት ያስገቡልኝ ዘንድ ከህዝቡ መሀል ቆሜ በክብር እጠይቅዎታለሁ፡፡
1ኛ. ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ የነበረው ለውጡን የመቆጣጠርና የመምራት ሙሉ አቅምዎን ይቀጥሉ፡፡ አንዳንድ ቦታዎች የሚታየው ግድያና ዝርፊያ፣ ፖሊስ ባለበት የሚፈፀም በመሆኑ፣ ለውጡን የመቆጣጠር አቅም እንደሌለዎ፣ ህዝቡ እየተጠራጠረ ነው፡፡ ይህን ስሜት በጨቅላው ለመቅጨት፣ የህግ የበላይነትን ያረጋግጡ፡፡ የአራት ወር ምክርና ዝክር ለሰለጠነ ሰው ከበቂ በላይ ነው፡፡ ምክር ያልገራውን አውሬያዊ ባህሪ በህግ መታረቅ አለበት፤ ለህዝቦች ሰላምና ለለውጡ ስኬት ሲባል፡፡
.
2ኛ. ስም ጠርተን መሸለም ብቻ ሳይሆን፣ ስም ጠርተን መርገም – መጠየቅ እንጀምር፡፡ እንደሚያውቁት ለዚህ ለውጥ ሲታገሉ የኖሩ ጀግኖቻችንን ስም እየጠራን፣ ባንዲራ እያውለበለብን፣ በአደባባይ ጉንጉን አበባ አጥልቀንላቸዋል፡፡ ልክ እንዲሁ ምክርና ዝክር ያላረማቸውን፣ የህዝብ ልጆች የተሰዉለትን ለውጥ ለመቀልበስ፣ በወገንና በሀገር ላይ የተነሱትን ስም ጠርተን እንርገም፤ ፋይል ከፍተን ለህግ እናቅርብ፡፡ በእንዲህ ያለው የለውጥ ሂደት ጉንጉን አበባ የሚጠልቅላቸው ጀግኖች ብቻ ሳይሆኑ፣ ካቴና የሚጠልቅባቸው የለውጥ አደናቃፊዎች መኖራቸው ተፈጥሮአዊ የአብዮታዊ ለውጥ አካል ነው፡፡ እነማን ከየቦታው ሰዎችን አፈናቀሉ? እነማን አዋሳ ላይ ገደሉ፣ አቃጠሉ? እነማን ሻሸመኔ ላይ ሰቀሉ? እነማን አሸዋ ሜዳ በተፈጸመው ተጠርጥረው ታሰሩ? እውነት ከየአንዳንዱ ጥቃት ጀርባ እንደሚባለው በገንዘብ ሽብሩን የሚደግፉ ሰዎች፣ ወይም ቡድኖች አሉ? ካሉ እነማን ናቸው?
.
ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በህይወት ዘመኔ እንዲህ ለቤተመንግስት የመቅረብ ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ እርስዎ ብቻ አይደሉም፣ ወደታች ወደህዝቡ የመጡት ህዝቡም በእርስዎ ውስጥ አድሮ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነ ያህል ነው የሚሰማው፡፡ እና ይበርቱ! ከጎንዎ ነን፡፡ ይህን ለውጥ ከግብ ከማድረስ ውጪ እርስዎም ሆኑ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሌላ ምርጫ የለንም፡፡ ሰነባብቼ ደግሞ ወደ አንጎሌ የመጣውን፣ ውቃቢዬ የፈቀደውን ከመፃፍ አልቦዝንም፡፡ እስከዚው ባሰቡት፣ በወጠኑትና በጀመሩት ሁሉ ፈጣሪ ይርዳዎ፡፡
አክባሪዎ በድሉ ዋቅጅራ
ከስድስት ኪሎ
Filed in: Amharic