>

አገሬ ዛሬም ጀግኖቿን ለይታ አላወቀችም!!! (ደገፋ አስረስ)

አገሬ ዛሬም ጀግኖቿን ለይታ አላወቀችም!!!
ደገፋ አስረስ
ኦሮሞ አይደለሁም። ስለኦሮሞ ሳስብ ግን ጀጋማ ኬሎ፣ አብዲሳ አጋ፣ ገረሱ ዱኪ፣ አበበ ቢቂላ፣ ፈይሳ ሌሊሳ … ይመጡብኛል። ኢትዮጵያ ያፈራቻቸው ኦሮሞ ጀግኖች ወይም ኦሮሞ የወለዳቸው ኢትዮጵያዊ ጀግኖች ተቆጥረው አያልቁም። ስራቸውን እዚህ ገልጨ ልጨርሰው ይቅርና የያንዳንዱን ጀግና በርካታ ፊልሞች ተርከው አይጨርሱትም። ጃጋማን በ15 አመቱ ጣልያንን እንዲወጋ ያነሳሳው ምንድነው? አምስት ሺ ጣልያን በአንዴ የመማረክ እውቀት ከየት አመጣ? አብዲሳ በተማረከበት አገር የማያውቃቸውን ሰዎች መርቶ በማያውቀው መሬት ጣልያንን በምድሩ ድል መንሳት ማን የሚሉት ጀግንነት ነው? ፈይሳ እጅ ማጣመርን እንዴት ከወርቅ አስበልጦ ከአለም ህዝብ ከግማሹ ለሚበልጠው ባንዴ አሳየ? ይሄ ኦሮሞነትና ኢትዮጵያዊነት ሳይነጣጠል በምን ይገለፃል?
ለነዚህ ጀግኖች በበቂው አልዘፈንላቸውም፣ አልተተረከላቸውም። የዛሬ እንባችንም ውለታቸውን ካለመክፈል የመጣ ይመስለኛል። ከመሀላችን ለገዘፉት ክብር አልሰጠንም።
በዘመኑ ደግሞ ፊትአውራሪ መሆን የሚገባው መረራ ወደኋላ ስንገፋው አገሬ ዛሬም ጀግኖቿን ለይታ አላወቀችም እላለሁ። አብይን ከደፈቅነው፣ ለማን ካልሰማነውና መረራን ከነሱ ጎን አርገን ከፍ ካላደረግነው ዋርካዎቹን እንቆርጣለን። ከነሱ ባነሰ ለሚጠቅሙን ቦታውን እናስረክባለን። ይህን በማድረጋችን የሚመክነው የኦሮሞ አመራር ብቻ ነው ብየ አላምንም። የሚመክነው ጋሞም፣ ጋምቤላም፣ ሱማሌም … ጭምር ነው። የአገርነት ታላቅ ራዕይ ይመክናል። በአንፃሩ ጀግኖችን የማምከን ልምዳችን ይለመልማል።
ወደዘር ሽንሸና ስሄድ ካሉኝ ልጆች ሁለቱ 50% የኦሮሞ ደም አላቸው። ቡራዩ የተጠቁት አብዛኞቹ በደም 100% ከኔ ጋር ናቸው። በዚህ ክስተት ኦሮሞ ጋሞን አጠቃ ብየ አላምንም አልወስንም አላስብም።
በቤቴ ውስጥ ያለችው 100% ኦሮሞዋ ሚስቴ ከዚህ ክስተት በኋላ በየቀኑ ከኔ በላይ የተንሰቀሰቀችው ለጋሞዎቹ ነው። ቡራዩ የተጠቁት ኦሮሞ ቢሆኑ፣ ኦሮሞ ስለሆነች፣ ከጋሞዎቹ በላይ አታለቅስላቸውም። ጥግህን ያዝ የተባለ ቢመስልም ከዘር የሚበልጥ ሰውነት ባገሪቱ ውስጥ አለ። ይህን ሰውነትን(ሰው መሆን) እንዲጎላ ከሚያደርጉልኝ ድንቅ ሰዎች አንዱ መረራ ነው። እድሜው ይርዘም! አንተ ማለቴ ከፍቅርና ከክብር ነው።
Filed in: Amharic