>
4:42 pm - Tuesday January 18, 3927

ለውጡን እደግፋለሁ ግን ...... (ግን የለም! !) ሞሀመድ እድሪስ

ለውጡን እደግፋለሁ ግን …… (ግን የለም! !)
ሞሀመድ እድሪስ
ሁሉም እራሱን ለውጥ ፈላጊ አድርጎ ያቀርባል። ከሰሞኑ ደግሞ ሁለት ቅኔ መሳይ ነገሮች ይነገራሉ። የመጀመሪያው በተግባር ለውጡን እና የህዝቡን ሰላም እያመሱ በፕሮፓጋንዳ ዋነኛ የለውጡ አጋር መስሎ መቅረብ ነው። ይህንን ስልት ብዙሀኑ ባያስተውለውም በተጨባጭ ታስቦበት እየተሰራበት ነው። ሁለተኛው “ለውጡን እደግፋለሁ ግን ….” የምትል ፈሊጥ መነሳት መጀመሩ ነው። ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ባዶ ቃል አይደሉም። ተግባር ሊያስከትሉ ይጠበቃል። በእርግጥ ለውጥን መቃወምም ሆነ መተቸት መብት ነው። ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ ተግባራቸውን በተገቢው መስመር እስካደረጉት ድረስም የፖለቲካ ሀይሎች በአሸናፊና ተሸናፊ ሲለዩ ሀገር ግን ከሁለቱም አትርፋ ታሸንፋለች።
ከአንባገነን አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ በሚደረግ ሽግግር የቀድሞ አፋኝ መዋቅሮችና ታፍነው የተለቀቁ ዜጎችን አስታርቆ ለመሄድ የሚደረገውን ጉዞ የተቃና የሚያደርጉት ሁለት ዘዴዎች አሉ። ተስፋን መዝራት እና ውጥረትን መቀነስ ናቸው። የዶክተር አብይ መንግስት ባልተጠበቀ እና ከዚህ በፊት አምሳያ በሌለው አካሄድ የመጀመሪያውን መንገድ ውጤታማ በሆነ መልኩ ተጠቅሞ ህዝብን ከጎኑ ማሰለፍ ችሏል። የተስፋ እና ይቅርታ እጁም ረዝሞ ስለህይወታቸው ይሰጉ የነበሩትን ስለሀገራቸው እንዲያስቡ ተስፋ ዘርቶባቸዋል። በማካቬሊ አገላለፅ ህይወት ሰጥቷቸዋል።
ሁለተኛውን መንገድ ምናልባትም ለአጠቃላይ ለለውጡና ለዶክተር አብይ መንግስት ወደ ስልጣን መምጣት ትልቅ ሚና የተጫወተውን ዘዴ ግን ቤተ መንግስት በር ላይ ተጥሎ የተገባ ይመስላል። ወይንም ደግሞ ያስጣሉ አካላት አሉ። ይህ የተረሳ (የተቀማ) መንገድ ውጥረትን የመቀነስ ዘዴ ነው።
ኢህአዴግ ጥልቅ ተሀድሶ እያደረግሁ ነው በሚልበት ወቅትም ሆነ በኢህአዴግ ውስጥ ክፍፍል ተፈጠረ በሚባልበት ወቅት ለለውጥ ሀይሉ አሳሳቢው ጉዳይ ከውጭ የሚመጣን ውጥረት መቀነስ ነበር። ያስቸኳይ ግዜ አዋጅ አንዲነሳ ጫና ሲደረግና የፓርላማው መከፋፈል የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው። የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ውስጥ የሚለው አጀንዳ በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረበት ወቅት ለውጡን ሳይወለድ ማጨናገፍ በሚችልበት ወቅት ነበር። የለውጥ ሀይሉ ሁሉንም ያስተናገደበት ጥበብ ግን ዛሬ ስለምናወራው ሪፎርም አብቅቶናል። የዶክተር አብይ በፓርላማ አለመገኘት፣ የአዲስ አበባ ጉዳይን ‘ ለወቅቱ የማይገባ ‘ በሚል ወደ ሁዋላ ለመሳብ የተወሰነው ውሳኔ የኦህዴድንም የለውጥ ሀይሉንም ብስለት የሚያሳይ ነበር። እነዚህ ውጥረት ፈጣሪ አጀንዳዎችን መሻገር በመቻሉ ነው የዛሬ የአዲሱ ውጥረት የሁለት ጫፍ ተዋንያን መድረክ ያገኙት።
ዛሬም ገና በእግሩ ባልቆመ የለውጥ ሂደት ውስጥ ነን። ለውጡ የሚጠይቃቸው የህግ ማሻሻያ እና ተቋማዊ ጉዳዮች ብቻ ሙሉ ትኩረት የሚሹ ብሎም ለሌሎች መፍትሄዎች መደላደል የሚፈጥሩ ናቸው። ዛሬም ውጥረት ፈጣሪ አጀንዳዎችን ማቅረብ ለውጡን ካለመፈለግ ተለይቶ አይታይም። ዛሬም ብናዘገያቸው የትም የማይሄዱ ሲንከባለሉ የኖሩ ጥያቄዎቹን ለማዘግየት አለመፍቀድ ለውጡ እንዲቀጥል ካለመፍቀድ አይለይም። ውጥረቱን በመጠቀም በወጉ መሰረት ካልያዘው የለውጥ ሀይል ሲንከባለሉ የቆዩ የፖለቲካ ጥያቄዎችን በማዋከብ ማስፈፀም መሞከር በተዘዋዋሪ መንገድ የለውጥ ተቃራኒ መሆን ነው። ይህን የለውጥ ተቃራኒ አቋም በፕሮፓጋንዳ ብዛት መሸፈን ጥቂት ቢሰራ እንጂ ህዝብ እውነታውን መረዳቱ አይቀርም። የባንዲራ እና የአዲስ አበባም ጉዳይ የተለየ አይደለም!!
የግርጌ ማስታወሻ: አዲስ አበባ የሁላችንም ናት። ስለ አዲስ አበባም ዝም የምንል አይደለንም። ልዩነታችን በህግ የበላይነትና በህዝብ ድምፅ ማመናችን ነው። በአዲስ አበባ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ተከራካሪዎችም ሆኑ የአዲስ አበባን የመጨረሻ ምሽግነት በእጅ ጥምዘዛ እናስከብር ለሚሉት “ጉዳዩ የሀገር ሉአላዊነት ጉዳይ ባለመሆኑና አሁን ላይ ከለውጡ አይበልጥምና ቅድሚያ መቀመጫ ሀገራችንን” እንላቸዋለን!!!
Filed in: Amharic