>

ከአንተ በፊት አባ ገዳ ነግሮኛል !  (ዮሀንስ መኮንን - ክፍል 2)

ከአንተ በፊት አባ ገዳ ነግሮኛል ! 
ክፍል ሁለት
ዮሀንስ መኮንን
ዛሬ ሀገሬ ቀን ጥሏት አንተን የመሰለ እሾህ አበቀለችና ታሪክ ተገልብጦ በፈረንጅ ሀገር የምትንከራተተው ስደተኛው አንተ “ባለሀገር” ሆንክ:: ሀገር ጠባቂው እኔ ደግሞ “ሠፋሪ” ተባልኩ!
****
እናቴ ጆርጌ ቶሎሳ እና ወሎዬዋ አያቴ ፋንታዬ
ይህችውልህ ደግሞ እናቴ !
ባለፈው ጽሑፌ በኦሮሞ ምድር የኦሮሞ ቤተሰብ ሆኖ ስለኖረው ስለ መንዜው አባቴ እና ባልቻ ሄርጳ ስለተባለው ኦሮማራ አጎቴ እውግቼህ በቀጣዩ ጽሑፌ ስለእናቴ እንደምጽፍልህ ቀጠሮ ነበረን:: እነሆ በቀጠሮዬ መሠረት ተመልሻለሁ:: በትእግስት ተከተለኝ::
ቢቂላ ጉደታ ኦዶ (Biqilaa Guddataa Oddoo) የተባለ ጦረኛ የቦረና ኦሮሞ የወራሪውን የጣልያንን ጦር ለመውጋት ከአጼ ምኒልክ ጦር ጋር አድዋ ዘምቶ የሀገርን ዳር ድንበር አስከብሮ ሲመለስ ከነጦሩ ምእራብ ሸዋ ላይ የአሪሮ ጎሳ ባላባት ሆኖ ኑሮውን ይመሠርታል:: ቢቂላም አያቴን ቶሎሳን ይወልዳል:: ቶሎሳ ልበብርሃን እና ትምህርት ወዳጅ ስለነበር ጎጃም እና ጎንደር ተዟዙሮ የቤተክህነቱን ትምህርት ተምሯል:: ታዲያ የቦረናው ሰው ቶሎሳ ቢቂላ ከአማሮች ምድር ፊደል ብቻ ሳይሆን ወለዬዋን ፋንታዬንም አብሮ ቀጽሎ (ተምሮ) ኖሮ የእኔን እናት ጆርጌን ወለዱ:: አናቴ ጆርጌ አያቷ በጦርነት ላይ አገጩን በጥይት ተመትቶ እንደነበረ ሳይቀር እያስታወሰች ስለ ጀግንነቱ እና ሀገር ወዳድነቱ አውግታኛለች::
እናቴ ጆርጌ ከኦሮሞዎቹ ወላጆቿ ጋር ብዙም አልኖረችም:: ይልቁኑም ነፍጠኛው አማራ ፊታውራሪ መልሴ አጥናፉ አያቴን ኦቦ ቶሎሳን ለምነው በማደጎ እናቴ ጆርጌን ይወስዳሉ:: ኦሮሞዋ እናቴም ስሟ ጆርጌ ቶሎሳ መሆኑ ቀርቶ አሳዳጊዋ ባወጡላት ስም “ፀሐይ መልሴ አጥናፉ” ተብላ ነፍጠኛ አማራ ሆና አደገች:: አማራው አሳዳጊዋም ከልጆቹ እኩል ሀብት ሲያወርሳት ምእራብ ሸዋ ላይ አራት ጋሻ የእርሻ መሬት እና አዲስ አበባ ጉለሌ ላይ ደግሞ ግማሽ ጋሻ መሬት ይሰጣታል::
ይሄውልህ እንግዲህ አኔ የኦሮሞ ባህል ውስጥ ኖሮ በፈቃዱ ኦሮሞ ከሆነው አማራው አባቴ እና በአማራ ቤተሰብ ውስጥ አድጋ በፈቃድዋ አማራ ከሆነችው ኦሮሞ እናቴ ተገኘሁ:: መንዜው አባቴ ኦሮሚፋ አቀላጥፎ ሲናገር አማራነቱን ትጠራጠረዋለህ:: ኦሮሞዋ እናቴ ደግሞ አማርኛዋ ጎጃሜውን ያስንቃል:: ማንነቴን ብታውቅ ኖሮ እንኳንስ “ሠፋሪ” ብለህ ልትሰድበኝ ቀና ብለህ አታየኝም ነበር:: ምክንያቱም እኔ ጣልያንን አባርሮ ድንበር ያስከበረ የቦረና ኦሮሞ ባላባት ልጅ ነኛ ! ሀገርና ወገንን መውደድን ለኢትዮጵያ ድንበር መውደቅን ኦሮሞው ቅድመ አያቴ በወሬ ሳይሆን በተግባር አስተምሮ ኢትዮጵያን በአደራ አስረክቦኛል:: ይብላኝ ላንተ! አደራህን በልተህ ቅድመ አያቴ አዋርዶ ካባረራቸው ባእዳኖች ለቁራሽ ጉርሻ ደጅ መጥናትህ ሳያስ ለጎሳ ፖለቲካህ እንዲመችህ እኔን እና ወንድሞቼን ታባላናለህ::
ዛሬ ሀገሬ ቀን ጥሏት አንተን የመሰለ እሾህ አበቀለችና ታሪክ ተገልብጦ በፈረንጅ ሀገር የምትንከራተተው ስደተኛው አንተ “ባለሀገር” ሆንክ:: ሀገር ጠባቂው እኔ ደግሞ “ሠፋሪ” ተባልኩ:: አዲስ አበባ ላይ የግማሽ ጋሻ መሬት ወራሽ የሆንኩት እኔ ዛሬ በኪራይ ቤት ኑሮዬን መግፋቴ ሳያንሰኝ አንተ በሀበሻነትህ አፍረህ ከፈረንጅ ዜግነት የተቀበልከው የባህር ማዶ ሰው “መጤ” እያልክ በሀገሬ ከወገኔ ጋር የምኖረውን እኔን ትሰድበኛለህ:: አንተ ምንታደርግ! ድንጋይ እንዲሰብሩ ጊዚ የሰጣቸው ቅሎች ሕገመንግስት ብለው መዝገብ ሲያበጁ የእኔ ቢጤ ሠርገኛ ጤፍ ኢትዮጵያዊን የዜግነት ክብር እንኳን አልሰጡንም:: እነርሱ በሰፉት የጎሳ ከረጢት መግባት ሳይቻለኝ ስለቀረ ሀገሬ እንደዜጋም ረስታኛለች:: በዘር ሀረጉ ደሙ “ንጹህ” ለሆነው ባለጊዜ እንጂ የእኔ ቢጤ ቅይጡ ኦሮማራ በአያት ቅድመአያቶቹ ምድር መጻተኛ እና ባይተዋር ነው::
ወዲህ አንደኛው እብድ አለህ ደግሞ:: አንተኛው “ኦሮሞ ጠል” ነኝ (Oromofobic) ነኝ ባዩ ጎረምሳ! አንተን ደግሞ ነፍጠኛው አያቴ እድሜ ሰጥቶት ከዚህ ዘመን ደርሶ አውቆህ ቢሆን ኖሮ “ጥቁር ውሻ ውለድ” ብሎ ይረግምህ ነበር:: ኦሮሞዋን እናቴን ፍጹም ልጁ አድርጎ አሳድጏልና::
ቅድመአያቶቻችን በሞጋሳ እና በማደጎ ተፋቅረው አብረው ኖረው, ጋሻ መሬት ተካፍለው, ጠላት ሲመጣባቸው አብረው ዘምተው, ሀገር እቅንተው አብረው ሲኖሩ “ኦሮማራዎቹ” እኔና አንተ በአሥር አመት ወረፋ በተገኘ በኪራይ ቤት እየኖርን ድንጋይ መወራወራችን መቼም ድንቅ ስላቅ ነው:: “ይህቺም ቡናቁርስ ሆና ሚጥሚጣ በዛባት” እንዲሉ !
 
3) ኦሮማራው ‹‹እኔ›› – ከባንቱ ጂማ እስከ አብነት ሸገር
ስለ ኦሮሞ ሞጋሳ (Moggaasa) የጻፍኩት አጭር ማስታወሻ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ግለታክ አካል ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቼ መልእክቱን ተጋርተውታል:: ስለ አባቴ በመተረክ የጀመርኩት ጽሑፍ የእናቴን ደግሞ እንድተርክ ገፋፍቶኛል፡፡ አሁን ደግሞ የራሴን ግለታሪክ ላካፍል ነው::
በፌስቡክ ገጽ የሚጋራ ጽሑፍ በጠባዩ አብዛኛው አንባቢ በሞባይሉ ገጽ (Screen) ስለሚያነበው ከሚገባው በላይ አጭር በመሆኑ ብዙ ጠቃሚ ታሪኮችን ቆርጦ ለመጣል ያስገድዳል፡፡ ይህንን ግለታሪክ ግን ያለቅጥ ክማሳጠር ይልቅ ባይሆን በሦስት ክፍል ላቀርበው ወስኛለሁ:: ክፍል አንድ እነሆ!
“””””””””
ቀደም ብዬ እንዳጫወትኩህ አናት እና አባቴ ከአዲስ አበባ በስተምእራብ (ጅማ መሥመር) 83 ኪሜ አካባቢ ምዕራብ ሸዋ በቶሌ ወረዳ ባንቱ የተባለች ትንሽዬ የገጠር ከተማ (ጥጊያ መንገድ እንኳን ባልነበራት) በኦሮሞ ምድር ወልደው ከብደዋል፡፡ እኔ ለቤተሰቤ 12ተኛ ልጅ መሆኔ ነው፡፡ (አራት ታናናሾች እንዳሉኝ ሳትረሳ)፡፡
ንፋስ በነበርኩበት የልጅነቴ ወራት ከአባገዳ ልጆች ጋር ከብት እንጠብቅ ነበር፡፡ ኦሮማራ የሆንን እረኞች (እኔ እና ጓደኞቼ) ከብት ስንጠብቅ ውለን ፀሐይዋ መግረር ስትጀምር ከብቶቻችንን ከመስኩ ላይ አሳርፈን እኛ ደግሞ በአባገዳ ዋርካ ጥላ ሥር ምሳችንን እየተሸማን በጋራ እንበላ ነበር፡፡ የእሸት ወራት ሲሆን ደግሞ አቤት ደስታችን ! ከማሳዎቻችን የስንዴ ነዶ አጨድ አጨድ አድርገን እንቁጦ (በእሳት የተለበለበ እሸት) ቃም ቃም እያደረግን እነርሱ አያቶቻቸው ያቆዩላቸውን ሂቦ (Hibboo የኦሮሞ ሥነቃል) ሲያጫውቱኝ እኔ ደግሞ የመንዞቹን አያቶቼን ‹‹እንቆቅልሽ›› እየነገርኳቸው አስፈነድቃቸው ነበር፡፡ (የአባ ገዳ ልጆች በልጅነቴ ነግረውኝ እስከዛሬም ልረሳው ያልቻልኩት ሂቦ በተጠየቅ አንዲህ ይላል (Ejarsaa waaritu – Sinbirti hin qaaritu – ትርጓሜው የምሽቱን ወይራ ወፍ ብትበርር አትዘለውም) መልሱ ‹‹እግዚአብሔር›› ማለት ነው)
አባቴ ጥብቅ ክርስቲያን ስለነበር ልጆቹን በሙሉ ክርስትና ሲያስነሳን ለታቦት ነው የሰጠን፡፡ ስለዚህ የክርስትና አባት እና እናት ማናችንም የለንም፡፡ ባይሆን የዓይን እናት እና አባት ሆነው የተዛመዱን የአባገዳ ልጆች ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የእኔ የዓይን አባቴ ቦንሳ ረጋሳ ሲሆኑ ለዓመት በዓል ለልጆቻቸው ልብስ ሲገዙ ለእኔም ይገዙልኝ ነበር፡፡
በዚህች ጭው ባለች ትንሽ የገጠር ቀበሌ ውስጥ በልጅነት ልቤ እንደነፍሴ ስምወዳቸው ጓደኞቼ ላጫውትህማ፡፡ አንደኛው ሶሎሞን ሚርከና ጫሊ ነው፡፡ ሚርከና በደርግ ዘመን ወታደር ሆኖ ኤርትራ የዘመተ ኦሮሞ ሲሆን ከዘመቻ ሲመለስ ኤርትራዊት ሚስቱን እና አራት (?) ልጆቹን ይዞ ቀበሌያችን ይመጣል:: ከኦሮሞ አባት እና ከኤርትራዊት እናት ከተወለዱት ልጆች ትንሹ ሶሎሞን ሲሆን ጥፍጥ ያለ ኮልታፋ አማርኛውን ለመስማት ስል ጏደኛዬ አደረኩት:: እኔ “ኦሮማራ” ሶሎሞን “ኦሮግሬ”! (ኦሮሞ +ትግሬ) አቤት ስንዋደድ:: የሚያሳዝነው ኦሮግሬው ሶሎሞን አሁን የት እንዳለ እንኳን አላውቅም:: እህቶቹ ስለ ኤርትራ ባህር ይነግሩን ስለነበር ባላየነው ቀይባህር ወደባችን በዓይነ ህሊናችን እየሳልን በደስታ እንፍነከነክ ነበር::
ሁለተኛው የልጅነት ጏደኛዬ ደግሞ ሠይፉ ይባላል:: ሠይፉ የትምህርትቤታችን እውቅ የሒሳብ መምህር የባጫ ጭሪ ሠፋቶ (Baacaa Cirri Safaato) ልጅ ነው:: ሠይፉን በሁለት ምክንያት ልቤ እስኪጠፋ እወደው ነበር:: አንደኛ ጸጉሩ ሉጫ ስለነበር ሲሆን (ይሄኔ እኮ አሁን ተመልጦ ይሆናል!) ሁለተኛው በትምህርቱ ጎበዝ ስለነበር ነው:: (በነገራችን ላይ አብረን ይተማርነው 1ኛ ክፍልን ብቻ ነው) እንደ እርሱ በትምህርት ጎበዝ ለመሆን የጀመርኩት መንገድ ሰምሮልኝ ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ስማር አንድ ጊዜም ሁለተኛ ወጥቼ አላውቅም:: ሁሉንም አንደኛ ደረጃ ተማሪ ነበርኩ! እድሜ ለሠይፉ:: ዛሬ ሠይፉ ባጫ ጎበዝ ሐኪም (specialist) እንደሆነ እና ባሌ ጎባ ሆስፒታል ይሠራ እንደነበር ሰምቻለሁ:: (ይህን ጽሑፍ ያነበው ይሆን?)
በገጠር ቀበሌ ሁሉም ልጅ ክረምት ላይ እረኛ ይሆናል:: ትምህርት ቤት ሲከፈት ግን ክብት ጠባቂዎች በሁለት ብር ወርሃዊ ክፍያ ከብቶቻችንን ስለሚጠብቁልን እኛን ያሳርፉን ነበር:: ታዲያ በጠዋት ማልደን ተነስተን ከብቶቻችንን ለጠባቂዎች እስረክበን በእሸት ማሳዎች መሀል በሩጫ አቆራርጠን ደወል ሳይደወል ወደ ትምህርት ቤት መድረስ ይጠበቅብን ነበር:: የትምህርት ቤታችንን ደወልን በልጅነቴ በአድናቆት እመለከተው ነበር:: ሳድግና ሳውቀው የመኪና ጎማ ቸርኬ ኖሯል ዛፍ ላይ ሰቅለውልን በማረሻ ብረት “የሚደውሉልን:: የእኛ ከብት ጠባቂዎች የእነ አዲቾ ጉርሜሳ ቤተሰቦች ነበሩ:: (አዲቾ በኦሮሚፋ ፀአዳ ወይንም ነጭ ማለት ነው) ታዲያ አንዳንዴ ከብቶቼን ላደርስ በሄድኩበት የአዲቾ እናት የጥቁር ጤፍ ቂጣ በወተት ስለሚሰጡኝ ትምህርት ቤት መሄዱን እየርሳሁ እዚያው እየዋልኩ ፈተና ሁሉ እምልጦኝ ያውቃል::
አባቴ ቆፍጣና ገበሬ ስለነበር ከእርሻ በተጨማሪ የገጠር ሆቴል ነበረን:: የገጠር ሆቴል ምን እንደሚመስል ታውቃለህ? አራት የሽቦ አልጋ የተዘረጋባቸው ሁለት ክፍል አልቤርጎዎች እና ስድስት አግዳሚ መቀመጫ ያለው ማለት ነው:: ስለዚህ እንግዶች እኛ “ሆቴል” ያርፉ ነበር:: ከማልረሳቸው የሆቴላችን ደምበኞች ወዳጆቼን ትግራዋዮቹን እነ ተጫነ ዓለሙን እና እነ በየነን አስታውሳቸዋለሁ:: የስፖርት አስተማሪያችን ትግሬው መኮንንስ እንዴት ይረሳል? ተጫነ ሥራው ፖሊስ ሲሆን እነበየነ የግብርና ሠራተኞች ነበሩ:: አንዳንዴ ለትግሬው ተጫነ ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ የኦሮሚፋ አስተርጏሚ እሆናለሁ:: (ያው ከገበሬዎቹ በኦሮሚፋ አናግሬ ሁለት ብር ጉቦ እቀበልለት ነበር ልልህ ብዬ ምሥጢር ማውጣት እንዳይሆንብኝ ተውኩት) እርሱ ደግሞ ቤት ሲመጣ ትግርኛ ያስተምረን ነበር:: “ንሽተይ ንሽተይ” ለመስማት ታህል የምትሆን ትግርኛ ያወቅሁት ያኔ ነው:: ያኔ የጀመረችው አንደኛዋ እህቴ ግን አሁንም ትግርኛን በደምብ አቀላጥፋ ስለምታንበለብለው ለማያውቋት “ተጋሩ” ነው የምትመስላቸው::
አንድ ብር የመክፈል አቅም ያለውን የመንደራችንን ሰው መሀመድ የተባለ ጉራጌ (ሙስሊም) ፎቶግራፈር ባልሳሳት በዓመት ሁለት ጊዜ ወደገጠር ከተማችን መጥቶ በጥቁር እና ነጭ (black and white) ፎቶ ያነሳን ነበር:: መሀመድ ሲመጣ ከተማ ውስጥ ካልነበርክ ፎቶ አመለጠህ ማሉት ነው:: ፎቶ መነሳት ካማረህ በቃ መበሳጨት አያስፈልግህም:: በቶሎ ይመለሳል … ስድስት ወር ብቻ ታግሰህ ትጠብቃለህ!
ይህን ሁሉ የተረኩልህ እስከ ስምንት ዓመቴ የነበረውን ታሪኬን ነው:: በስምንተኛው ዓመቴ አዲስ አበባ ገባሁና እሳት የላስኩ አጭቤ የአብነት ሠፈር ልጅ ሆንኩ::
የትም ተወለድ ሸገር ላይ እደግ !!!
Filed in: Amharic