>
9:56 pm - Tuesday August 16, 2022

የመደመር ሙድ እና የጃዋር ካልኩሌተር (ክንፉ አሰፋ)

የመደመር ሙድ እና የጃዋር ካልኩሌተር*

ክንፉ አሰፋ

  • ከኢትዮጲስ ጋዜጣ የመጀመርያ እትም ላይ የተወሰደ

 

“ካልኩሌተሩን የሰራነው እኛ ነን!” ብሎናል ጃዋር መሓመድ፣

“ለመሆኑ አንተስ ተደምረሃል?” ተብሎ ለተወረወረበት ጥያቄ ሲመልስ።

ሁለት አማራጭ ብቻ ያላት ቀላል ጥያቄ ነበረች። ጃዋር ግን ለጥያቄዋ ቀጥተኛ መልስ መስጠት አልፈለገም።  “እኛ” የምትለዋን የብዝህነት ሃረግ ለግዜው ወደ ጎን እንተዋት። ግን፤ እንዲያው በደፈናው “ሁሉም ነገር በእኔ ሆነ – አንዳችም ያለእኔ የሆነ ነገር የለም!” ብሎ እየነገረን ያለው ጃዋር የካልኩሌተርዋ ፈጣሪ ስለመሆኑ የሚያቀርብልን አንዳች ማስረጃ ይኖር ይሆን?  ለድምሩ ፖለቲካ የተሰራችው ይህች ካልኩሌተር እርግጥም የጃዋር የምህንድስና ውጤት ከሆነች “አደጋ አለው!” ልንል ነው። መሬት ላይ ባለ ሁነታ ሳይሆን ይልቁንም በስሜት እንደሚቀያየረው የጃዋር አቋም፤ ማሽኑ የሚያዋዥቅ አባዜ ባይይዘው ነው የሚደንቀን።

ጃዋር ስታየል የመደመር ቀመር ከቲም ለማ እሳቤ የተለየ ስለመሆኑ የሰሞኑ ቃለ-ምልልሶቹ ብቻ ይመሰክሩልናል። “ችግሩን በፈጠረው አሰተሳሰብ፣  ችግርን መፍታት አይቻልም” ያለን ማን ነበር? አዎ፣ አልበርት አንስታይን ነበር። ዶ/ር ዐብይ አሕመድ (ዲራአዝ) “እርካብና መንበር” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሃፋቸው ጠቅሰውታል። (የዚህን አስገራሚ መጽሃፍ ቅኝት በሚቀጥለው ጽሁፌ እመለስበታለሁ)

ተራራ መሆን ባትችል፣ ተራራውን ተደገፍ እንዲሉ ሶማሌዎች፤ በለውጡ ሞተር በተገኘ ድል ላይ፤ ደጋፊ ሳይሆን ተደጋፊ ሆኖ፤  የአንበሳውን ድርሻ መሻት ትንሽ ይሰቀጥጣል። በአብይ መንግስት የመደመር ቅላጼ ሳይሆን፤ ይልቁንም ጃዋር እየነገረን ባለው “በቄሮ መንግስት” አተያይ የቃሉ ትርጓሜ  ምን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም የሱ ቨርሽን የሆነውን ሕልም ለግዜው ያዝ ማድረጉ ሳይበጅ አይቀርም። በ”እንገንጠል” የተቃኘው የአዕምሮ አጥር ሳይፈርስ፤ እውነተኛው የመደመር ህልም ከቶውንም ዘላቂ ሊሆን አይችልም። ዛሬ ህልም የመሰለን የተዛባ ነገር፤ ትንሽ ከርሞ ቅዠትም ሊሆን ይችላል። እውነተኛ ህልም መሽቶ ሲነጋ እንደ ጉም አይበተንም።

በኢትዮጵያዊነት የሚያፍሩ እና ኢትዮጵያዊ መሆን ወንጀል እንደሆነ ሲሰብኩ ለነበሩ ሁሉ፤ ከወዲህኛው ጫፍ የተነሱ ጀግኖች፤  “እንደውም ሱስ ነው” በማለታቸው ነው የለውጡ መንገድ እንዲጠረግ ያደረጉት። በሃገሪቱ ጠልሎ የነበረው ጥቁር ደመና እና የጥላቻ ቁርሾ በጣና ኬኛ ፖለቲካ፤ በኢትዮጵያ ኬኛ ቅኝት ባይደረምሱት ኖሮ የሶማሊያን ታሪክ እንደግመው ነበር። …እነሱ እየነገሩን ያሉት መደመር ይህንን መሰለኝ!

ካልኩለተሩ የሚተፋው ፤ “የቄሮ መንግስት እና የአብይ መንግስት!” መሆኑን ስንሰማ መሃንዲሶቹ ገና ለአስተሳሰብም ሆነ ለአመለካከት ለውጥ ዝግጁ እንዳልሆኑ እንረዳለን። በመደመር ሙድ ውግዘቱ እና ጡዘቱ በረድ ስላለ እንጂ ይህ ብዙ የሚያስብል ንግግር ነበር። አንድነትን ሳይሆን መከፋፈልን እየሰበኩ ከመጡ ሰዎች የተሰራ ካልኩለተር ለችግራችን መፍትሄ አይሆንም። “ችግሩን በፈጠረው አሰተሳሰብ፣  ችግርን መፍታት አይቻልም”

መደመር ማለት ግን ምን ማለት ነው?

እንዲሁ በግርድፉ ካያነው የአንድ ወቅት መፈክር ይመስላል። ከጥሬ አገላለጹ ወጥተን ስንትረጉመው እርግጥ “መደመር” ሃሳብ ነው። አንዳንድ ሃሳብን በቃላት መግለጽ ይከብዳል። የዚህ አዲስ ሃሳብ ትርጉም በደንብ ተብራርቶ ባለመቅረቡ ብዙዎችን ግራ ማጋባቱ ግልጽ ነው።

“የሚያዋጣን መደመርና መደመር ብቻ ነው!” የሚል መፈክር ከሁሉም አቅጣጫ፤ ከሁሉም ወገን ይሰማል። ቁጥሩ በዛ ያለ እድምተኛም “መደመር” የሚል ቃል የተጻፈባቸው ቲ ሸርቶችን ለብሶ ወደ ግቢው ይተምማል። በእርግጥ  ትርጉሙ ገብቷቸው ወይንም የቃሉ ጉልበት ገዝቷቸው ላይሆን ይችላል። በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን እንዲሉ ከሳጥን ውጭ የሆነ፤ የተለየ እና አዲስ ሃሳብ ስለመሆኑ ግን ሁሉም ይስማማል።

በዚህ ሞቅታ ውስጥ ከዚህ የተለየ ነገር የሚያወራ ወይንም ከዚህ ሙድ በተቃራኒው የሚቆም ቢኖር ክፉኛ ቢወገዝ ምንም አይደንቅም። በአመክንዮ ሳይሆን ይልቁንም በስሜት ብቻ ከሚነዳን ሕዝብ ፊት ለፊት ቆሞ የሚዳፈር ይኖር ይሆን?

የሰሜን አሜሪካው የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌስቲቫል ከወትሮው ሞቅ፤ ደመቅ ብሎ በዳላስ – ቴክሳስ ላይ እየተከበረ ነው። ሰኔ ወር 2018። ወሬው ሁሉ አብይ፤ መፈክሩም መደመር፤  በሆነበት በዚያ ፌስቲቫል ላይ ከአንድ አቅጣጫ የሚመጣ ድምጽ ቀልባችንን መሳቡ አልቀረም። “…አንደመርም! አንደመርም!” የሚል ድምጽ! ይህንን “ታቡ” ነገር ለማየት ወደ ተናጋሪው ድንኳን አመራን።

መፈክሩ እየተነገረ የነበረው “ኢህአፓ” ከሚል ድንኳን ውስጥ  ነበር። እርግጥ ወቅቱ ይህን የሚያስብል አልነበረም። የህሊና እስረኞች ተለቅቀዋል።  የ”ቀን” ጅቦችም ከፖለቲካ መድረኩ እያፈተለኩ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጥሪ እየተደረገላቸው ነው። … አምልኮተ አብይ በሚመስል መልኩ የ”አብይ-ማንያ” ስነልቦና በሕዝብ ልብ ውስጥ ክፉኛ ታንጿል።   በዚያ አፍላ የጫጉላ ሰዓት – ከብዙሃኑ አመለካከት ለየት ያለ ድምጽ ከወዲያኛው ጫፍ መስማቱ ፍጹም እንግዳ ቢሆንም፤ ምክንያቱን ማወቁ ግን አይጎዳም።

የድምጽ ማጉያውን የያዘው ተናጋሪ መፈክሩን ቀጠለ። “በትግራይ ጉድጓድ ውስጥ ታስረው ያሉ የኢህአፓ አባላት እስካልተፈቱ ድረስ አንደመርም!…”

በባዶ ስድስት ማጎርያ ውስጥ አሉ ስለሚባሉት እስረኞች ጉዳይ ምንም ማለት አይቻልም። መረጃው ያላቸው፤ ምስጢሩንም የሚያውቁት እነሱው ናቸውና። እነዚያ ወገኖች ከመደመር በፊት እያቀረቡ ያሉት መቋጫ የሌለው ቅድመ ሁኔታ ግን በወዲያኛው ምዕተ-ዓመት እንኳ ሊሟላ እንደማይችል ሳያውቁት ቀርተው ነው ለማለት ይከብዳል።

አንድ ነገር ግን ግልጽ ይመስላል። መደመር የሚለው አዲስ የፖለቲካ እሳቤ አብዛኞቻችንን ግራ እንዳጋባን ግልጽ ነው። ኢህአፓ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እድሜው 50 ነክቷል። ከአንጋፋነቱም አልፎ ቅርስ የሆነ ፓርቲ ነው።  የመደመር ሃሳብ ለእነሱ ካልገባ ታዲያ ለማን ይገባው ይሆን? የሚል ጥያቄ በሰሚው አእምሮ ውስጥ መጫሩ ታዲያ እንግዳ አይሆንም።

“መደመር” ማለት ከዶ/ር አብይ ፓርቲ (ከኢህአዴግ) ጋር አንድ መሆን የሚመስላቸው ሰዎች ቁጥር ጥቂት አይደለም። መደመር ማለት ሁሉም ወደ አንድ ፓርቲ ተዱሎ አውራ ፓርቲ መመስረት የሚመስለው ሰውም እጅግ ብዙ ነው። የትጥቅ ትግልን አቁሞ ወደ ሃገር ቤት መግባት፣  ዶ/ር አብይን ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ መደገፍ፣ ሲኖዶሱን እና መጅሊሱን አንድ ማድረግ… ወዘተ ሁሉም ለቃሉ የየራሱ ትርጉም አለው። አንዳንዱ ደግሞ የዶ/ር አብይን ወይንም የለማ መገርሳን እጅ መጨበጥ እንደ መደመር ይቆጥረዋል። እጅግ የሚያሳዝነው ግን በሞብ ተደራጅቶ አናርኪዝም እና ፎኮይዝምን ማራመድም እንደ መደመር መወሰዱ ነው።

 ትርጓሜው ትክክልም ነው። ትክክልም አይደለም። የኢህአዴግን ካባ መልበስ እንደማይሆን ግን ግልጽ ነው።  “የሚሄድበትን የማያውቅ ሰው፤ ማንኛውም መንገድ ይወስደዋል።” እንዲሉ የመደመር ትርጉሙ ያልገባው ሰው ቃሉን እንዳሰኘው ሊተረጉመው ይችላል።

ስፓንሾች አንድ አባባል አላቸው፣ “የምንወድደውን ማግኘት ባንችልም፡ ለማግኘት የምንመኘውን እንውደድ” ይለሉ። አዲስ ነገር ሲመጣ በደስታ ከሚቀበለው ይልቅ የሚጠራጠረው ይበልጣል። ይህ ደግሞ እንግዳ አይደለም። አዲስ ነገር አዲስ ነው። የነበረ እና የተለመደ ነገር ተቃራኒ ስለሆነ። ምንም እንኳን መልካም ቢሆን፤ እስኪለመድ ድረስ ግዜ ይጠይቃል። ቃሉ በራሱ የሁሉንም ሃሳብ የማሸነፍ ጉልበት እና ሃይል ባይኖረውም በተግባር ተፈትኖ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ሊዘገይ ይችላል። ግራም ነፈሰ ቀኝ መቋጫው የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ነው ሚሆነው።  

እኔ እንደገባኝ “መደመር”  ማለት የአንድ መሪ ህልም ነው። የዶ/ር ዐብይ አሕመድ ህልም።  እንደፈቺው ያማይተረጎም አንድ ወጥ የሆነ ህልም። ማርቲን ሉተር ኪንግ ለጥቁሮች ነጻነት እና እኩልነት በተነሳ ግዜ፣  “ሕልም አለኝ” ሲል ሕልሙን በአዳባባይ ይፋ አድርጎት ነበር። ጥቁር ሕዝብ ከነጩ ሕዝብ ጋር እኩል የሚሆኑባትን “አንዲት ቀን” አልሞ ተናግሯል። አፍሪካ-አሜሪካውያን ለነጮች ብቻ በተሰራው ዋይት ሃውስ ውስጥ ሲገቡ፣ ይህ መሪ ቃል፤ ይህ ህልም ዘመን ተሻግሮበባራክ ኦባማ እውን ሆኗል። በከፊልም ቢሆን።

እንደ ማርቲን ሉተር፤ ዶ/ር አብይም ራዕይ ይኖራቸዋል። ራዕይ የሌለው ሰው እና የመስኖ ውሃ አንድ ናቸው። ሁለቱም በተቀደደላቸው አቅጣጫ ሁሉ ይፈስሳሉ።  

 ዛሬ የመደመር ፍልስፍና በስፋት ይነገራል። “እርካብ እና መንበር” መጽሃፍ ውስጥ ይህንን እሳቤ የሚገልጽ ሃረግ አለ። ጸሃፊው አዲስን ነገር በህዝብ ስነልቦና ውስጥ እንዲሰርጽ መድረጉን ሲገልጹ … “ለየት ያለ ሃሳብ ሲኖርህ እነዚህን ሃሳቦች እውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ ሚዲያዎችን ተጠቀምባቸው” (ገጽ 83) ይላሉ። የመደመር እሳቤ በደንብ ስላልተብራራ እንጂ ። መደመር አንድ አዲስ የፖለቲካ ፍልስፍና ነው። ለብዙዎች የሚጠቅም የአንድ ስው ራዕይ እና አዲስ ሃሳብ!  በሂደት ውስጥ ሊመጣ የሚችል የአስተሳሰብ ለውጥ። መዳረሻውም ፤ በታላቅዋ ኢትዮጵያ ውስጥ በፍቅር እና በአብሮነት መተሳሰር ነው። አንዱ ትልቅ ሌላው ትንሽ፤ አንዱ ሲበላ ሌላው ተመልካች የሆነበትን ድልድይ አፍርሶ በይቅርታ መሻገር።

“ግንቡን እናፍርስ፤ ድልድዩን እንገንባ” የሚለው የእርቅ ቃል “በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር” በሚል መፈክር ታጅቦ በአዲሱ አመት ታውጇል። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይህንን ከምን ግዜውም በላይ ትሻለች። ለሰላምና ፍትህ ለእድገታችን አይነተኛ የሽግግር ድልድዮች ናቸው።  

ችግሩ ያለው እና ወደፊትም ሊኖር የሚችለው ሕዝቡን እንመራለን ብለው በሚነሱ ግለሰቦች እንጂ በሕዝቡ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጸብ እንጂ ለይቅርታም ቅርብ ነው። ጁነዲን ሳዶን በአበባ ጉንጉን የተቀበለ ሕዝብ ነው። ኢሳያስ አፈወርቂን በቀይ ምንጣፍ የተቀበለ፣ ታምራት ላይኔን የክብር ካባ ያለበሰ ሕዝብ ነው። ነገ አቦይ ስብሃት አደባባይ ወጥተው “በድያችኋለሁ፤ ይቅር በሉኝ” ብለው ቢናገሩ፤ የምህረት እጁን የሚዘረጋ ሕዝብ ነው።

ይህ ሕዝብ ቂምን የሚረሳ ሕዝብ ነው ብቻ ብለን በደለኛውን ዝም ማለቱ ግን ለጽድቅ ይሆን ይሆናል እንጂ ፖለቲካዊ ፋይዳ አይኖረውም። ወገን በእጅጉ ቆስሏል። የጉዳቱን መጠን እና የቁስሉን ህመም ሊረዳ የሚችለው ደግሞ የተነካ ብቻ ነው። በግፉ ዘመን አብረው ያላለቀሱ፤ በይቅርታው ዘመን አብረው ለመደሰት መሻት ምን ያህል እንደሚያም ሊገባቸው የሚችለው ተበዳዮቹ ብቻ ናቸው።  “ይቅር እንባባል፣ ለምህረት እጃችንን እንዘርጋ!” በሚለው እንስማማ። ከዚያ በፊት ግን በደሉ ሁሉ በአደባባይ ወጥቶ ይሰጣ፣ በዳዮችም ከምሽግ ወጥተው ይናዘዙ። በደቡብ አፍሪካም የሆነው ይኸው ነበር። ይህ ካልሆነ ግን በይቅርታ የመሻገሩ ነገር ተደባብሶ “ቂም ይዞ ጉዞ” እንዳይሆን ያሰጋል።

Filed in: Amharic